የሰማያዊ ፓርቲ አባሉን ገድለዋል ከተባሉ ተጠርጣሪዎች አንዱ በቁጥጥር ስር ዋለ

Wednesday, 17 June 2015 12:50

  • “ግድያው ከፖለቲካ አቋሙ ጋር የሚገናኝ አይደለም”

     የአማራ ክልል መንግሥት

 

 

በደብረማርቆስ ከተማ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰማያዊ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ሳሙኤል አወቀ በደረሰበት ድብደባ ከትናንት በስቲያ ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም ምሽት ህይወቱ ማለፉ ታወቀ። አቶ ሳሙኤል አወቀ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኑና በፖለቲካዊ አቋሙ ምክንያት የተለያዩ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች በተደጋጋሚ ይደርሱት እንደነበር የሚናገሩት የፓርቲው የህግ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ፤ ከዚህ ቀደምም በተፈፀመበት ድብደባ የአካል ጉዳት ከማጋጠሙም ባለፈ ታስሮ እንደነበር ተናግረዋል።

ሰንደቅ ጋዜጣ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ሟች የሰማያዊ ፓርቲ አባል ቢሆኑም ለሞት ያበቃቸው ክስተት ግን ግለሰባዊ ግጭት ነው ይላሉ። በጥብቅና ሞያቸው የስድስት ሺህ ብር ክፍያ ተቀብለው የያዙትን ጉዳይ በመረታታቸው በድጋሚ ይግባኝ እጠይቃለሁ በሚል ደንበኞቻቸውን ተጨማሪ ገንዘብ ጠይቀው ሰዎቹም ከብት ሽጠውና መሬት አስይዘው፤ የጠየቁት ገንዘብ ቢሰጧቸውም በድጋሚ በመረታታቸው ምክንያት በተበሳጩ ደንበኞቻቸው የተፈፀመ ግድያ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ወንጀሉን ፈፅመዋል የሚባሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ሲሆኑ አንደኛው በዞኑ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ በምርመራም ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል። የግጭታቸው ምክንያት በውል ባይገለፅም ከአቶ ሳሙኤል አወቀ የጥብቅና ሙያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ኃላፊው፤ ከፖሊስ የተገኘ ነው ያሉትን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።

በተለያዩ የማህበራዊ ድረ-ገፆች መንግስት በግድያው እጁ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሲመልሱ፤ “ግድያው ከሟች የፖለቲካ አቋም ጋር የሚገናኝ አይደለም፤ የመንግስትም እጅ የለበትም” ሲሉ አረጋግጠዋል።

በፖለቲካ አቋሙ የደረሰበት አንዳችም ተፅዕኖ እንዳልነበረና ተፅዕኖ ደርሶብኛል በሚል ለፖሊስ ያቀረበው አንዳችም መረጃ እንደማያውቁ ተናግረዋል። ፓርቲው በበኩሉ አባሉ አቶ ሳሙኤል አወቀ፤ ተደጋጋሚ ዛቻ ይደርስበት እንደነበር እንደሚያውቅ ቢናገርም ስለጉዳዩ በዝርዝር መረጃ ለመስጠት ጊዜው አይደለም ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ሰኞ ምሽት 2፡30 ሰዓት ላይ ወንጀሉን ሲፈፅሙ ሰዎች በቦታው ነበሩ፤ አንደኛው ተጠርጣሪ ወዲያው እንዲያዝም የአካባቢው ሰው ትብብር አድርጓል ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ሟች ወደቤቱ እየሄደ ባለበት መንገድ ላይ ከኋላ በባህር ዛፍ እንጨት ተመቶ እንደወደቀና በድጋሚም በድንጋይ እንደተደበደበ ከፖሊስ የተገኘውን መረጃ መነሻ አድርገው ያስረዳሉ።

ሟች ሳሙኤል አወቀ የህግ ምሩቅ ሲሆኑ፤ በደብረማርቆስ ከተማ የምስራቅ ጎጃም ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጥብቅና ሲሰሩ ቆይተዋል። ሰኞ ምሽት ድብደባው ከተፈፀመባቸው በኋላ በአፋጣኝ ወደደብረማርቆስ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። በትናንትናው እለትም የአስክሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላ ጎቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ወደሚገኙት ቤተሰቦቹ ዘንድ መሸኘቱ ታውቋል።

http://www.sendeknewspaper.com/news-sendek/item/2807-

Leave a Reply