Wednesday, 17 June 2015 16:14

     “ሕጉ አለ ብለን እንቅልፍ እንዲወስደን ነበር፣ ነገር ግን ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግልን አልቻለም። ምክንያቱም ከሰዋዊ ሥልጣን አልተላቀቅንም መሆንም አልቻለም። በሕግ መመራት ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎች ሕግ እያወጡ ተከተለኝ የሚሉት የሰው አመራር ነው ያለው”
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
በአንድ ወቅት በመኢአድ ጽ/ቤት ያደረጉት ንግግር

 

 

ባሳለፍነው ሳምንት “የዳኛቸው ሐሳቦች” በሚል ርዕስ አንድ መጽሐፍ ለገበያ በቅቷል። ጋዜጠኛ መሐመድ ሀሰን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሸገር ሬዲዮ፣ ከ“ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” አዘጋጆች ጋር ያደረጉትን ውይይት ወይም ቃለ ምልልስ እንዲሁም በአዲስ ነገር ጋዜጣ፣ በሮዝ መጽሄት፣ በዘ-ፕሬስ፣ በአዲስ ጉዳይ፣ ላይ ያሰፈሯቸውን ጽሁፎች አሰባስቦ ለአንባቢዎች በሚመች መልኩ ፍሰታቸውን ጠብቀው ለማቅረብ ሞክሯል።
ጋዜጠኛ መሐመድ በግሉ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ያደረጋቸውን ውይይቶች እና ዶ/ሩን አናግሮ ለጋዜጣ ሕትመት ያዘጋጃቸውን ጽሁፎች በመጽሐፍ ጥራዙ ውስጥ አካቷቸዋል። አቀራረቡ ቀላል ለንባብ የሚጋብዝ ነው። አጠቃላይ የመጸሐፉ ማጠንጠኛ የዶክተር ዳኛቸውን አንድ የአመክንዮ ኅልዮት መገለጫ ብቻ የሚያሳይ ከነባራዊ ምልከታቸው የሚጣረስ ከመሆኑም በላይ ውዳሴና ከንፈር መሳም እንደመለኮት የበዛበት ፍፁም የሆኑ ሰው ናቸው፣ ይሄው ተቀበሉኝ የሚል አስመስሎበታል።
ጋዜጠኛ መሐመድ “በምስጋና ገጽ” ላይ ስለ ዶ/ር ዳኛቸው ምክንያታዊነት እንዲህ ሲል አስፍሯል። “አንድ ቀን ስራውን የማየት እድል ያልገጠመህ፣ ነገር ግን እየሰራሁ እንደሆነ በአደባባይ ሆነ በግል ጭውውታችን ወቅት ሳነሳ ቅንጣት ታህል የጥርጣሬ ስሜት ያላስተዋልኩብህ፣ እንዴት ለምን መቼ.. የሚሉ ጥያቄዎችን ለአንድም ቀን ያልሰነዘርከው፣ በዚህች ያልጠና እድሜዬ እንደ ወዳጅ ስላየኸኝ ብቻ ሳይሆን ስላወቅኩህም ኩራትና ክብር ይሰማኛል።”
በርግጥ ጋዜጠኛ መሐመድ “መለዮ ዓልባው ምሁር” በሚል ርዕስ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ለቀረበ ጽሁፍ ምላሽ በኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ሲሰጥ፣ የዶክተር ዳኛቸውን የአደባባይ ጽሁፎች እና ንግሮች በማሰባሰብ ለሕትመት እንደሚያበቃ ጠቆም ማድረጉን አስታውሳለሁ። በአደባባይ ለተናገረው ቃል ታምኖ ይሄው የዶክተር ዳኛቸውን አስተሳሰቦች በተረዳው መልኩ አለፍ አለፍ እያለ መረዳቱን እየጨመረ ለንባብ አበቃው።
ዕለተ ቅዳሜ ግን አስደጋጭ ጉድ ይዛ ብቅ አለች። በዕለተ ቅዳሜ ለሕትመት የሚበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ሃሳቤን ተዘርፌያለሁ ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው ክስ ሊመሠርቱ ነው” በሚል የዜና ርዕስ አዲስ ነገር ይዛ ብቅ አለች። ከዜናው አትኩሮቴን የሳበው ዶ/ር ዳኛቸው “እኔ ሣላውቅ በስሜ በታተመ መፅሐፍ ሃሳቤን ተዘርፌያለው…መብቴን ለማስከበር በፍርድ ቤት ክስ እመሰርታለሁ” ማለታቸው ነበር። አያይዘውም “ከህግ ባለሙያዎች ጋር ተማክሬ በፍ/ቤት ካሣ እጠይቅበታለሁ፤ ይህን መሰል የሃሳብ ዝርፊያ እንዳይፈጸምም ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግራ ያጋባውና ለጽሁፉ መነሻም የሆነው ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በኢትዮጵያ ባለው የሕግ ስርዓት ላይ በሚጋበዙበት እንዲሁም በአንዳንድ መጫወቻ ቦታዎች አካባቢ የሚሰጡት ሙሁራዊ ዳሰሳና የግል እምነትና አስተያየታቸውን ጨምሮ ከግምት ሲወስድ እንዴት ዶ/ር ዳኛቸው አሁን ያለውን የሕግ ስርዓት ፍትህ ያጎናጽፈኛል ብለው አምነው በፍርድ ቤት ይቆማሉ ብሎ ለማሰብ አዳጋች ይሆንበታል። ከዚህም በላይ ትንግርት ሆኖበታል።
ከላይ ለሰፈረው አግራሞት አስረጂ የሚሆነንን እንመልከተው። ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ወቅት በመኢአድ ጽ/ቤት ተገኝተው “ዛሬ ከ21 ዓመታት በኋላ” የሚል የጥናት ወረቀት  አቅርበው ነበር። በዚሁ የጥናት ወረቀታቸው ላይ “ነፃነትና ሕግ” ባሉት ንዑስ ርዕስ ስር የተረዳሁት እውነት ባለፉት 21 ዓመታት በዚሁ ስርዓት ውስጥ ያላቸው አንደምታን እና ጠቅላይ መደምደሚያቸውን በማስፈር ታዳሚውን አስደምመው ከፍተኛ አድናቆትም አትርፈው ከመኢአድ ጽ/ቤት መውጣታቸውን ነው። የተበረከተላቸውን አድናቆት በይገባኛል መንፈስ መቀበላቸውንም ብዙዎች የሚመሰክሩት እውነታ ነው።
ዶክተር ዳኛቸው በመኢአድ ጽ/ቤት ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ እንዲህ ነበር ያሰፈሩት፤ “አሁን ሕግ፣ መብት፣ ፍትህ የሚለው ቀርቶ ሰዎች አንድ ቦታ ተሰብስበው የሚያወጡት ትእዛዝ ሆነ፤ እነእገሌ… አሸባሪ ናቸው እየተባለ ሕግ ይወጣል። የውጭውን መሬት ሸጬ ጨርሻለሁ፣ አሁን ደግሞ የግቢህን እሸጣለሁ የሚል ሕግ ይወጣል፤ የሃያ አራት ወይም የሃያ አምስት ዓመት ወጣት ርዕዮት የምትባል ትንሽ ልጅ አነበበች ነው ምናምን ተብሎ አስራ አራት አመት ሽብርተኛ ተብላ ይፈረድባታል። ታዲያ ይሄ ሕግ ፍትህ አለው?’’ ሲሉ መጠይቅ ሰንዝረው በመደምደሚያ አገላለጽ “በሀገራችን ላይ ሕግና ነፃነት የተራራቁ ሆነዋል” ብለዋል።
በግርምታቸው ላይ ዶ/ሩ አክለው “ሕጉ አለ ብለን እንቅልፍ እንዲወስደን ነበር። ነገር ግን ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግልን አልቻለም። ምክንያቱም ከሰዋዊ ሥልጣን አልተላቀቅንም፤ መሆንም አልቻለም። በሕግ መመራት ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎች ሕግ እያወጡ ተከተለኝ የሚሉት የሰው አመራር ነው፣ በዚህ ስርዓት ውስጥ ያለው” ሲሉ ስርዓቱ በሕግ በላይነት የሚመራ ሳይሆን ሕግ እያወጡ ሕዝቡን እንደሚገዙ በመኢአድ ጽ/ቤት ለነበረው ታዳሚ አስረድተዋል።
የዚህ ጽሁፍ ጥያቄም “ስርዓቱ በሕግ የበላይነት የሚመራ ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎች ሕግ እያወጡ ሕዝቡን እንደሚገዙ” ትንታኔ ያቀረቡት ዶክተር ዳኛቸው በራሳቸው ጉዳይ ላይ ሲሆን “ሃሳቤን ተዘርፌያለሁ፣ ክስ እመሰርታለሁ” ሲሉ መደመጣቸው ቀደም ሲል ከሚያራምዱት አቋም ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ቢፈጥር ብዙ አያስገርም ይሆናል። እሳቸው በየመድረኩ እየቀደዱ የሚሰፉት የህግ ስርዓት በምን መልኩ ፍትህ ያጎናጽፈኛል ብለው ወደ ፍርድ ቤት አቀናለሁ ማለታቸው፣ ዶክተሩ ሌላ አዲስ መለዮ ይዘው ብቅ ብለው ይሆን ስንል ጠየቅን። በርግጥም ዶ/ር ዳኛቸው የአመክንዮ መጠይቅን እንደሚወዱ ትምህርታቸውም እንደሚያስገድዳቸው በአደባባይ ሲናገሩ ይደመጣሉና በዚህ መጠይቅ ቅር አይላቸውም ተብሎ ይገመታል።
ዶክተር ዳኛቸው ባለፉት 21 ዓመታት የህግ የበላይነት (Rule of law) ሳይሆን ሕግ እያወጡ ሕዝብን የሚገዙ (Rule by law) የውስን ሰዎች ስርዓት መሆኑን በመኢአድ ጽ/ቤት ካስረዱ በኋላ፣ ዛሬ ላይ “ሃሳቦቼ ተዘረፉብኝ” በሚል ክስ ለመመስረት ያነሳሳቸው በ22ኛ ወይም በ23ኛው ወይም በ24ኛው እድሜ ውስጥ ስርዓቱ ወደ ሕግ የበላይነት ስርዓት በመለወጡ ነው፤ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄደው ብለው ካስረዱን መከራከሪያ ነጥባቸውን ለመስማት ሁላችንም ዝግጁዎች ነን። ወይም በደፈናው ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ መሰረታዊ የህግ ስርዓት ለውጥ አለ ብዬ አምኜ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅናት የወሰንኩት ካሉም አንድ ነገር ነው። ምላሹ የሚሆነው የዶ/ሩ የራሳቸው ነው።

 

ከላይ ለሰፈሩት መከራከሪያዎች አጋዥ የሆነ አንድ የቆየ አጋጣሚ ትዝ አለኝ። ይሄውም፣ አባ በደብራቸው እየሰበኩ ነው። ባለቤታቸውም አውደ ምህረቱ ላይ ተገኝተው ሰብከታቸውን ይከታተላሉ። የትምህርቱ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሌሎችን መርዳት ያለውን መንፈሳዊ ዋጋ የሚመለከት ሲሆን፤ “ሁለት ኮት ያለው አንዱን ለሌላው ለተቸገረ ይስጥ” እያሉ አስተማሩ።

ትምህርቱ አልቆ ህዝቡ ተበተነና አባ ቤታቸው ደርሰው “እስቲ ያንን ኮቴን አምጪ በረደኝ” ቢሉ ባለቤታቸው “ለኔቢጤ ሰጠሁት” ሲሉ መለሱ። “ማን ስጭ አለሽ?!” አሉ አባ ተቆጥተው። “ቅድም ቤተክርስቲያን ሲያስተምሩ ሁለት ኮት ያለው አንዱን ይስጥ ብለው ሲያስተምሩ ሰምቼ ነዋ።” ቢሏቸው “ታዲያ እኔ ህዝቡን አልኩ እንጂ አንቺን መች አልኩ” ሲሉ አባ በቁጣ መለሱ።

ዶ/ር ዳኛቸውም በአደባባይ ፍትህ የለም ሕግ የለም ሲሉ ከርመው እርስዎ ታዲያ እንዴት ፍ/ቤት እሄዳለሁ አሉ ቢባሉ “ታዲያ እኔ ህዝቡን እንጂ መች እኔን አልኩ” ሳይሉ ይቀራሉ?

ከዚህም በተጨማሪ የገጣሚ እንዳለ ዓለም ግጥምን ዶክተር ዳኛቸው ቢመለከቱት ብዙ ገጽ ፍሬ ነገሮች ያገኙበታል ብዬ በማሰብ ይሄው ብያለሁ፣

“በውሸት ያቆምኩት – እውነቴ ቢናጋ

የእውነት ደከምኩኝ – ምስክር ፍለጋ”

እንደመውጫ ግን የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሃሳቦች እሳቸው እንደሚሉት ከፈቃዳቸው ውጪ ተሰብስበው ተጠርዘው ለገበያ መብቃታቸው ቢያንስ ከሞራልም አንፃር ተቀባይነት ያለው ተግባር ተደርጐ አይወሰድም። አይገባምም።

Leave a Reply