አምስት መቶ አርባ ሰባቱ በደም የጨቀዩ ወንበሮች
ኢህአዴግ/ወያኔ የዛሬው 100% አሸነፍኩ የሚል የቅጥፈት ንግግር ላይ ለመድረስ ያበቃው እና ለጊዜው የቆመ ያስመሰለው ያፈሰሰው የደም ብዛት ነው።በያዝነው ወር ብቻ ብንመለከት የአረናውን ታደሰ አብርሃ ተሰቅለው ተገደሉ፣የሰማያዊ ፓርቲ ጠበቃ ሳሙኤል በስለት እና በዱላ ተገደለ።
በደቡብ ክልልም የመድረኩ አባል እንዲሁ ሕይወታቸው ተቀጠፈ። እነኝህ ለናሙና ቀረቡ እንጂ ሌሎች አያሌዎች ከገጠር እስከ ከተማ ተገድለዋል።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ባፈሰሰው ደም ጨቅይቶ እና ተረማምዶ ነው እንግዲህ ስርዓቱ አምስት መቶ አርባ ሰባቱ ወንበሮች በኢህአዴግ/ወያኔ መሞላቱ ዛሬ የተነገረን።ወዮ! በደም ለጨቀዩ አምስት መቶ አርባ ሰባቱ ወንበሮች።ቤቱ በራሱ በሺህ የሚቆጠሩ በእስር ቤት የሚማቅቁ ዜጎች እሪታም ጭምር የተሞላ ነውና። የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸውን የማያውቁ አያሌዎች በማዕከላዊ መታሰራቸው ይነገራል።
የህክምና ዶክተሮች፣ፓይለቶች፣ኤሌክትሪሻኖች፣ጋዜጠኞች፣ተማሪዎች ወዘተ ቤተሰብ የት እንዳሉ ሳያውቅ በእስር የሚገኙ እና በእዚህም ዘመናት ያስቆጠሩ ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው።አንድ ቀን የእዚህ ሁሉ ግፍ አድራጊዎች ለፍርድ ሲቀርቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታው ይገለጣል።በእስረኞች ሰቆቃ፣በግፍ በተገደሉት ንፁሃን ደም፣በስደት በሚማቅቁት ወገኖቻችን እና በህሊና እስረኞች ስቃይ ላይ ተረማምዶ አምስት መቶ አርባ ሰባት ወንበሮች የደረደረው የኢህአዴግ/ወያኔ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሕዝብ በምንም መስፈርት የህዝብ ተወካይ ወንበሮች ሊባሉ አይችሉም።በደም የጨቀዩ ወንበሮች ስብስብ ግን ሊባል ይችላል።በሐሰት ተጠንስሶ በሕዝብ ደም ለጨቀየ ወንበር ለመቀመጥ መስከረምን የሚናፍቁ ምንኛ ህሊናቸውን የሸጡ ናቸው? እንዴት የሳሙኤል ደም፣የታደሰ አብርሃ ስቅላት፣የአብርሃ ደስታ፣የእስክንድር፣የርእዮት እና ሌሎችም ስቃይ፣የአንዳርጋቸው ፅጌ ሰቆቃ፣በአረብ ሀገር ከሰው ልጅ ክብር በታች የተዋረዱት እህቶች ዋይታ፣በሀገር ቤት የጥቂቶችን ቅምጥል ሕይወት እየተመለከተ በችግር የሚገረፈው ኢትዮጵያዊ መከራ አልታያቸው አለ? ለምን በደም ለጨቀየ ወንበር ተንገበገቡ? የሕዝብ ማዕበል ለሚፈነግለው የደም ወንበር ለምን ተንሰፈሰፉለት? የስርዓቱ አሽቃባጮችስ በንፁሃን ደም ባደፈ እጃቸው፣በሐሰት በረከሰ አንደበታቸው እና ይሉኝታ ባልቃኘው ህሊናቸው 547 በደም የጨቀዩ ወንበሮች በሐሰት አሸነፍን ለማለት እንዴት ተደፋፈሩ?
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሰኔ 16/2007 ዓም (ጁን 23/2015)