ቆዳችን ከውበት ባሻገር

Wednesday, 17 June 2015 16:54

አንድ ሰው የሰውነት ቆዳውን ለማስዋብ የሚጠቀምባቸው ነገሮች በተዘዋዋሪ ረጅም ዕድሜ እና የተሻለ ህይወት ለመኖር ከሚደረገው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ነው። ልክ እንደሌሎቹ የሰውነታችን ክፍሎች ሁሉ የቆዳችንን ጤንነት ለመጠበቅ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ ለፀሐይ እና ተያያዥነት ላላቸው ቆዳን ለሚጐዱ ነገሮች ከመጋለጥ ራስን መጠበቅ እንዲሁም ጥሩ የአመጋገብ ዘዴዎችን መከተል ናቸው። የቆዳ ጤንነት ሲነሳ ብዙዎቻችን በይፋ የሚታዩት የፊት፣ የእግር እና የእጅ ቆዳዎቻችን ብቻ ናቸው፤ ወደ አዕምሮአችን የሚመጣው። ነገር ግን አጠቃላይ የሰውነታችን ቆዳ ጤና መታወክ ለሰውነታችን ጤንነት መታወክ መንስኤ የሚሆንባቸው ጊዜያትም አይጠፉም።

በሰውነታችን ቆዳ ላይ የተመጣጠነ የአመጋገብ ዘዴን ባለመከተል፣ ከተለያዩ ነገሮች የሚመነጩ ኬሚካሎች እንዲሁም ከከባድ የፀሐይ ጨረር እና ጠንካራ ሳሙና የተነሳ የተለያዩ እንከኖች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በአብዛኛው በፊታችን ላይ የሚወጣው ብጉር ሲሆን፤ ፊታችንን ጨምሮ በሌሎች የሰውነት ቆዳዎቻችን ላይ ደግሞ እንደ ሽፍታ፣ ቀያይ እብጠቶች እንዲሁም የሚያሳክኩ እና አልፎ አልፎም የማበጥ እና ውሃ የመቋጠር ምልክት ያላቸው የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በመሆኑም እነዚህን በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ከተከሰቱ በኋላ ከችግሩ ለመውጣት የሚያግዙን ተፈጥሮአዊ ዘዴዎችን እንድናዘወትር ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።

አትክልትና ፍራፍሬ

አብዛኛዎቹ አትክልትና ፍራፍሬዎች ኃይለኛ የሆነ ቆዳን ከተለያዩ ኬሚካሎች የመከላከል አቅም አላቸው። አሜሪካን ሜዲካል ጆርናል እንዳስቀመጠው መረጃ፤ በተለይ ከሲጋራ፣ ከተለያዩ አየር በካይ ጋዞች እና ከፀሐይ ብርሃን የሚመነጩ እና ፍሪ ራዲካልስ ከሚባሉ አደገኛ ነገሮች ቆዳችንን የመከላከል አቅም አላቸው፤ አትክልትና ፍራፍሬ። እነዚህ ከተለያዩ ነገሮች የሚመነጩ አደገኛ ነገሮች በሰውነት ቆዳችን ላይ ሲያርፉ የተለያየ ቀለም ያላቸው ነጠብጣቦች እንዲፈጠሩ እና ቆዳችንም እንዲጨማደድ ያደርጋሉ። ይሄን ችግር ለመቋቋም በአትክልትና ፍራፍሬዎች ውስጥ የሚገኘው እና ቤታ ኬሮቲን የተባለው ንጥረ ነገር ወሳኝ ነው። ይህን ንጥረ ነገርም ከዱባ፣ ከስኳር ድንች፣ ከፓፓያ እንዲሁም ከቆስጣ እና ከመሳሰሉት የአትክልትና ፍራፍሬ ልናገኘው እንችላለን።

በቫይታሚን የበለፀጉ ምግቦች

ቫይታሚኖች በአጠቃላይ ለሰውነት ጤንነታችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፤ ለቆዳችን በተለይ በርካታ ጠቀሜታ ይሰጣል። ቫይታሚን ሲ የሰውነት ቆዳችን የሚያርፉበትን ነገሮች የመቋቋም አቅም እንዲያዳብር የማድረግ ጠቀሜታ አለው። ቫይታሚን “ሲ” ሰውነታችን በቆዳ ላይ የሚደርሰውን ችግር ሊቋቋም የሚችልባቸው ኢንዛይሞችን እንዲያመርት ያግዛል። በተጨማሪም ቆዳችን ለችግር ከተጋለጠ በኋላ በቀላሉ እና በፍጥነት እንዲያገግም ያደርጋሉ። በመሆኑም እንዲህ አይነት ጠቀሜታ የሚሰጡ ምግቦችን መመገብ ይመከራል። ይህን ቫይታሚን “ሲ” ልናገኝባቸው የምንችላቸው ምግቦችም ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ስኳር ድንች፣ እንጆሪ፣ አበባ ጐመን እንዲሁም ዘይቱን የመሳሰሉት ምግቦች ናቸው።

ሌላው ለቆዳችን ጤንነት አስፈላጊው ነገር በቫይታሚን “ኢ” የበለፀጉ ምግቦች ናቸው። በቫይታሚን “ኢ” ከበለፀጉ ምግቦች መካከል ሴሌኒየም የተባለው በተለይ በቆዳችን ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን የመከላከል ከፍተኛ ብቃት አለው። ይህ የመዓድን አይነት ቆዳ በተለያዩ ውጫዊ ነገሮች እንዳይጐዳ ከመከላከልም ባለፈ የቆዳ ካንሰርን የመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህን አይነቱን በቫይታሚን “ኢ” የበለፀገ ማዕድን ከተለያዩ ስራቸው ከሚበላ አትክልቶች የምናገኝ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከዓሣ፣ ከእንቁላል፣ ከቲማቲም እና አበባ ጐመን ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም እንደ አቮካዶ፣ ፈንድሻ እንዲሁም ሱፍ እና በቆሎ የቫይታሚን “ኢ” ምንጮች ናቸው።

በማዕድናት የበለፀጉ ምግቦች

ብዙዎቻችን በምንመገባቸው ምግቦች ውስጥ ከምናካትታቸው እና ብዙም ትኩረት ከማንሰጣቸው ነገሮች መካከል ማዕድናት ተጠቃሽ ናቸው። በዋናነት ለቆዳችን ጤንነት ከሚያስፈልጉ ማዕድናት መካከልም ዚንክ አንዱ ነው። ዚንክ በከፍተኛ ደረጃ ጨረር ቆዳችን ላይ ሲያርፍ ጉዳት እንዳያደርስብን የመከላከል አቅም አለው። በተጨማሪም የተጐዳ ቆዳን በቀላሉ እንዲያገግም፣ ቁስል ሲከሰት በቀላሉ እና ቶሎ እንዲድን የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በተጨማሪም ዚንክ ማዕድን ጉበታችን ለቆዳ ጤንነት ወሳኝ የሆነውን ቫይታሚን “ኤ” በበቂ ሁኔታ እና በአስፈላጊው ጊዜ እንዲያመነጭ የማድረግ አገልግሎት ይሰጣል። በፒትስበርግ ህክምና ማዕከል የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም የዚንክ ማዕድን በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ሽፍታዎችን፣ ብጉርን እና እብጠቶችን የመከላከል ጠቀሜታ ይሰጣል። ሰውነታችንም ከ200 በላይ ኢንዛይሞችን በቀላሉ ማመንጨት እንዲችሉ ያደርጋል። በዚህ በዚንክ ማዕድን ከበለፀጉ ምግቦች መካከል ዓሣ፣ ቀይ ስጋ፣ የዶሮ ስጋ፣ የዱባ ፍሬ፣ አጃ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ሌላው ለሰውነት ቆዳችን አስፈላጊው የማዕድን አይነት ሰልፈር ነው። ሰልፈር በሰውነታችን ውስጥ በስፋት ከሚገኙ ማዕድናት መካከል በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው። ይህ ማዕድን በብዛት ተከማችቶ የሚገኘውም በፀጉራችን፣ በቆዳችን እና በጥፍራችን ውስጥ ነው። በመሆኑም በምንመገበው ምግብ ውስጥ የዚንክ ማዕድን ማካተት በርካታ ጠቀሜታ አለው። ከእነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም ቆዳችን ላይ ባክቴሪያ እንዳይራባ የማድረግ እና ቆዳችንን የማፅዳት አገልግሎት ይሰጣል። በተጨማሪም የተጐዳ ቆዳን በቀላሉ እና በፍጥነት እንዲያገግም እና ጠባሳም እንዲሽር ያደርጋል። በሰልፈር ማዕድን ከበለፀጉ ምግቦች መካከልም ነጭ እና ቀይ ሽንኩርት (በተለይ የማቃጠል አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ የሽንኩርት ዘሮች)፣ እንቁላል፣ የበሬ እና የዶሮ ሥጋ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም ዝንጅብል፣ ሮዝመሪ፣ ወተት እና የወተት ውጤቶች እና ቃሪያ የቆዳችንን ጤንነት ለመጠበቅ በባለሙያዎች የሚመከሩ የተፈጥሮ ውጤቶች ናቸው።

ሲልካ ሌላው ለቆዳችን ጤንነት ጠቃሚ የሆነ ማዕድን ነው። ሲልካ በሰውነታችን ውስጥ ለቆዳችን አስፈላጊ የሆኑ ኢንዛይሞች በስፋት እንዲመረቱ የማድረግ አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህ ውጪም ቆዳችን ለስላሳ እና አንፀባራቂ እንዲሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው። በዚህ በሲልካ ማዕድን የበለፀጉ ምግቦች በአብዛኛው አትክልትና ፍራፍሬዎች ሲሆኑ፤ በተጨማሪም ኪያር፣ የፈረንጅ ቃሪያ፣ አተር እና ባቄላ እሸት የዚህ ማዕድን ምንጮች ናቸው።

Leave a Reply