እነወይንሸት

 

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

በእነ ወይንሸት ሞላ የክስ መዝገብ መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ በእስር ላይ የሚገኙት ወንይሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬና ቤትሄልየም አካለወርቅ ላይ ፖሊስ በድጋሜ ያቀረበውን የምርመራ መዝገብ ዳኞቹ አንቀበልም ብለዋል፡፡

እነ ወይንሸት ሰኔ 15/2007 ዓ.ም በቄራ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ቀርበው እንዲፈቱ ተወስኖ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ፖሊስ ከእስር ሲወጡ በር ላይ በድጋሜ አስሮ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዳቸው ይታወቃል፡፡

ዛሬ ሰኔ 18/2007 ዓ.ም ቀደም ብለው ተከሰውበት በነበረው ተመሳሳይ ‹ወንጀል› ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ይዞ ቀደም ብለው ውሳኔ ባገኙበት በተመሳሳይ ቄራ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበር ቢሆንም ዳኞቹ ‹‹እኛ ፈርደናል፤ እንዲለቀቁም ወስነናል፣ ከዚህ በኋላ ይህን ጉዳይ አናይም›› በሚል መዝገቡን እንደማያዩ ገልጸው መልሰዋቸዋል፡፡

ፖሊስ ፍርድ ቤቱ ክሱን እንደማያይ ከገለጸ በኋላ እነ ወይንሸትን ወደ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የመለሳቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ እንዲፈቱ የወሰነላቸው አራቱም እስረኞች ጉዳይ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አልታወቀም፡፡

ሜሮን አለማየሁ ለብይን ተቀጠረች

ከሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ሰልፍ ጋር በተያያዘ ክስ ከተመሰረተባቸው የሰማያዊ አባላት መካከል የሆነችው ሜሮን አለማየሁ ለሰኔ 24/2007 ዓ.ም ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቷታል፡፡

Meron Alemayehu

ሜሮን ዛሬ ሰኔ 17/2007 ዓ.ም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጎፋ ምድብ ችሎት የቀረበች ሲሆን፣ መከላከያ ምስክሮቿንም አቅርባ አሰምታለች፡፡ ከአንድ ወር በላይ ዋስ ተከልክላ በእስር ላይ ቆይታ ከቀናት በፊት በዋስ ወጥታ ጉዳዩዋን በውጭ ሆና እየተከታተለች ያለችው ሜሮን በቀረበባት ክስ ላይ ሰኔ 24/2007 ዓ.ም ብይን ይሰጥባታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ጠርቶት ከነበረው ሰልፍ ጋር በተያያዘ ክስ ከመሰረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መካከል እስካሁን በአራቱ ላይ የጥፋተኝነት ብይን በመስጠት ያሰረ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በእስር ላይ ሁነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

ወ/ሮ ንግስት ወንዲፍራው ተፈረደባት

ንግሥት ወንዲፍራው (የሰማያዊ ፓርቲ አባል)

መንግስት አይ ኤይ አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰረችው ወ/ሮ ንግስት ወንዲፍራው ዛሬ ሰኔ 17/2007 ዓ.ም ቄራ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርባ የ8 ወር እስራት ተፈርዶባታል፡፡
ንግስት ወንዲፍራው ግንቦት 19/2007 ዓ.ም ያለ ማዘዣ ከ3 አመት ልጇ ጋር በፖሊስና ደህንነቶች ተይዛ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስራ ቆይታለች፡፡

 

ምንጭ፡ ነገረ ኢትዮጵያ

Leave a Reply