Ethiopia refuse to bury Chinese workers who died in Addis

ይልቅ ወሬ ልንገርህ
ቁም ነገር መፅሔት 14ኛ ዓመት ቁጥር 206 ሰኔ 2007 

በአዲስ አበባ መቀበሪያ ስላጡት ቻይናውያን አስከሬን

የቻይናውያን ቁጥር በሀገራችን ስንት እንደደረሰ ታውቃለህ? እውነቱን ለመናገር እኔም አላውቅም፤ ግን ግን ከብዛታቸው አንፃር አንዳንድ ወሳኝ የሚባሉ ማህበራዊ ሁነቶችን መከወኛ ቦታዎች ሳያስፈልጋቸው አይቀርም ትላለህ?
ለምን መሰለህ? በቅርቡ ነው አሉ፤ ምን ሆነ መሰለህ? ሁለት ቻይናውያን በአዲስ አበባባ በሰሩት መንገድ ላይ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ሲበሩ ፍግም ይላሉ፡፡ ምን ይላሉ አልክ? ይሰዋሉ ለማለት ነው፡፡እሺ ከዛስ? ከዛማ የሚሰሩበት መ/ቤት ላሉ ቻይናውያን ሀላፊዎች ተነግሮ አስከሬናቸው ከምንሊክ ሆስፒታል ይወጣል፡፡ እናስ? እናማ አስከሬናቸውን ወደ ሀገራቸው ለመላክ ቢታሰብም የአስከሬን መጫኛ ካርጎ ከአዲስ አበባ ወደ ቻይና የለም፡፡ እናስ? እናማ በመንገደኞች ማጓጓዥያ አውሮፕላን ለመላክ ደግሞ ክፍያው ሰማይ የነካ ሆነ፡፡
እናስ? እናማ በዚህ መሀል ቤተሰቦቻቸው ጉዳዩ ተነግሯቸው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ መ/ቤቱም አስከሬኑን ወደ ቻይና ለመላክ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን የማይችል ከሆነ እዚሁ አንድ ነገር ይደረግ ይባላል፡፡ያው በኛ ሀገር ባህልና ወግ መሰረት ለቀብር ይዘገጃጃሉ፡፡ ቻይናዎቹ ይሰሩበት የነበረው ድርጅት የህግ አማካሪና ጠበቃ የሆነው ኢትዮጵያዊ ጉዳዩን በሚያውቀው ባህልና ወግ መሰረት ወደ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ሄዶ የቀብር ቦታ ሲጠይቅ ምን ቢሉት ጥሩ ነው? ‹መጀመሪያ ሀይማኖታቸው መታወቅ› አለበት፡፡
ለቤተሰቦቻቸው ጥያቄው ሲቀርብ ደግሞ ‹ቻይናዎቹ ሀይማኖት የላቸውም› ተባለ፡፡ ይህን ጊዜ የቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ‹ሀይማኖት የሌለው ሰውማ እዚህ እኛ ቤተክርስቲያን አይቀበርም፤ እንደዚህ አይነት ሰዎችን የሚቀብረው የመንግስት ተቋም ማዘጋጃ ወይም የባይተዋር መቃብር ቦታ ነው፡፡› ይላሉ፡፡ የሟች ቤተሰቦችና ጠበቃው ተነስተው የማዘጋጃ መቃብር ቦታ ወደተባለው ቦታ አስከሬኑን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ እዚያ የጠበቃቸው አንድ የስራ ሂደት መሪ ጉዳዩን ጠይቆ ከተረዳና የቀብር ስፍራውን መመሪያ ካነበበ በኋላ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹እዚህ ቦታ ላይ የሚቀበሩት ሰዎች ቤተሰብ የሌላቸውና ሞተው የተገኙ ሰዎች ብቻ ናቸው፤ቻይናዎቹ ግን ቤተሰብ ያላቸው ሟቾች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቦታው እነሱን ለማስተናገድ ይቸገራል › አሏቸው፡፡
እናስ? ምን ተሻላቸው ታዲያ? ከቻይናዎቹ መሀከል አንዱ አንድ ሀሳብ አመነጨ፤ ምን የሚል አትለኝም? ‹ለምን አይቃጠሉም!› ብትወድም ብትጠላም ለጊዜው የተገኘው መፍትሔ ይሄ ብቻ ነበር፡፡ እናስ? ቀጣዩ ጥያቄ ‹የት?› የሚል ነበር፡፡ በጉዳዩ ሲቸገሩ የተመለከተ አንድ ሰው አዲስ አባባ ያለው የህንድ ኤምባሲ ይጠቁማቸዋል፡፡ ለምን መሰለህ? እንድ ህንድ በአዲስ አበባ ሲሞት የሚቃጠልበት የራሳቸው ቦታ አላቸው አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ? አዎ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ፤እንደውም አዲስ አበባ ውስጥ፤ የት? አትቸኩል፤
እናስ? እናማ የህንድ ኤምባሲ ተጠይቆ ፍቃደኛ ይሆናል፡፡‹የማቃጠያው ቁሳቁሶችን ቻሉ እንጂ ምን ችግር አለው? › ይላል፡፡ እናስ? እናማ ጉዞ ወደ ጉለሌ የህንዶች አስከሬን ማቃጠያ ሆነ፡፡ እናስ? የሁለቱ ቻይናውያን አስከሬን ቤተሰቦቻቸው ባሉበት እንዳይሆን ሆነ እልሃለሁ፡ ፡ ጠበቃውስ ? ጠበቃውማ የህንድ ኤምባሲ ይሁንታ ከተገኘ በኋላ ጉዳዩን ለመመልከት አብሮ መሄድ አልቻለም፡፡ ‹ዘገነነኝና ከፒያሳ ተመለስኩ› ይላል እያማተበ፡፡ በል ቻዎ

Leave a Reply