28 JUNE 2015 ተጻፈ በ 

በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ሰኔ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በተለያዩ አገሮች ባደረጉት የተቃውሞ ሠልፍ፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራውን የኤርትራ አስተዳደር በማውገዝና ሕጋዊ የሆነ መንግሥት

የማያስተዳድራት አገር የአፍሪካ ኅብረት አባል መሆን እንደማትችል በመግለጽ፣ ኤርትራ ከኅብረቱ አባልነት እንድትሰረዝ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ቁጥራቸው ከ1,000 የሚበልጡ ስደተኛ ኤርትራውያን ባሰሙት ተቃውሞ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ኤርትራን በሚመለከት ያወጣውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሪፖርትን ደግፈዋል፡፡ ‹‹ኢሳያስ አፈወርቂ ከሥልጣን መውረድ አለበት፤›› የሚለውንና ሌሎችንም መፈክሮች በማሰማት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ መንግሥት በተለይ በኤርትራውያን ወጣቶች ላይ እየፈጸመው የሚገኘውን ስቃይ፣ በደልና ሌሎች በዝርዝር ያቀረባቸውን ሪፖርቶች ኅብረቱ እንዲያፀድቀው ጠይቀዋል፡፡

ሕጋዊነት የሌለው መንግሥት የኅብረቱ አባል ሆኖ መቀጠል እንደሌለበት የጠቆሙት ኤርትራውያኑ፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው እንዲወገዱ ኅብረቱ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ለአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤትም ተመሳሳይ ደብዳቤ አስገብተዋል፡፡

የቀይ ባህር አፋር ነፃ አውጭ በሚባለው ድርጅት በተዘጋጀው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ቁጥራቸው ከ30 ሺሕ በላይ የሆኑ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ፣ በሰመራ፣ በዱብቲ፣ በበራ ኃይሌ ካምፕ መገኘታቸው ሲታወቅ፣ በውጭ አገሮች በኒውዮርክና በጄኔቭም የተቃውሞ ሠልፉ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሠልፍ በማድረግ ለአፍሪካ ኅብረት ያቀረቡትን ደብዳቤ፣ የዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ጸሐፊ ተቀብለው፣ ሊቀመንበሯ አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጧቸው ነግረዋቸዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ኤርትራን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በእርስ በርስ ጦርነት እየወደመች ከምትገኘው ሶሪያ ቀጥላ ወጣት ዜጐቿ ወደ ስደት የሚጐርፉባት አገር መሆኗን ገልጿል፡፡

የኤርትራ ሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን በቀጥታ ኤርትራ ውስጥ ሆኖ በአገሪቱ ዜጐች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መከታተልና መመራመር ባይችልም፣ ከ550 በላይ ስደተኛ ኤርትራውያንን በማነጋገርና የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ 484 ገጾች ያሉት ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 24ኛ ዓመት የነፃነት ቀኗን በቅርቡ ያከበረችው ኤርትራ ላለፉት 24 ዓመታት ዜጐቿ የስቃይ፣ የሞትና የእስራት ሰለባ መሆናቸውን ሪፖርቱ አካቷል፡፡ የሚፈጸሙባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ሆን ተብሎና ታስቦበት የሚደረጉና የዘር ማጥፋትን የሚያካትቱ መሆናቸውን ሪፖርቱ እንደሚያስረዳ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

Leave a Reply