ጀበርቲ እና ወርጂ
ጸሓፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
—–
“ጀበርቲ” በአንድ ዘመን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በሙሉ በወል የሚጠሩበት ስም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ራሳቸውን “ጀበርቲ” እያሉ የሚጠሩ የሙስሊም ማህበረሰቦች እስከ አሁን ድረስ አሉ፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች በብዛት የሚገኙት በሰሜን ኢትዮጵያና ምዕራብ ኢትዮጵያ (ጎንደር፤ ትግራይ፤ ጎጃም፤ ወለጋ ወዘተ) እንዲሁም በኤርትራና በሶማሊያ ነው፡፡ እነዚህ ጀበርቲዎች በነጃሺ ዘመን በስደት ወደ አክሱም መጥተው የነበሩት ሰሐባዎች (የነቢዩ ሙሐመድ ባልደረቦች) ተወላጆች ናቸው ይባላል፡፡ የታሪክና የአንትሮፖሎጂ ምሁራን ግን የጀበርቲ ማህበረሰብን አነሳስ የሚገልጹት ከዚህ በተለየ መንገድ ነው፡፡
እስልምና ወደ አሁኗ ኢትዮጵያ የገባው በሰሐቦች (በነቢዩ ባልደረቦች) ዘመን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ሃይማኖቱ መስፋፋት የጀመረው ከ8ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ ነው። ይህም ለንግድ ከዐረቢያ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ በሚመላለሱ ነጋዴዎችና በሀይማኖቱ ምሁራን (ዑለማ) ሲከወን የኖረ ነው። በተለይ ግን ከ9ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ታዋቂ ዑለማ (ምሁራን) ወደ ሀገራችን እየመጡ ስለ እስላማዊው እምነትና ስለ ሌሎችም እውቀቶች ህዝቡን ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በርካታ ህዝብም በነርሱ አማካኝነት እስልምናን ተቀብሏል። በዚህ ፈለግ ገድላቸው በታሪክ ድርሳናትና በምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች ትውፊት በስፋት ከሚነገርላቸው ምሁራን መካከል በቀዳሚነት የሚወሱ ሁለት ወንድማማቾች አሉ፡፡ አንደኛው ሼኽ ሙሐመድ አል-ጀበርቲ ይባላሉ፡፡ ሁለተኛው ዓሊም ደግሞ ሼኽ ዒስማኢል አል-ጀበርቲ ይባላሉ፡፡
እነዚህ ሁለት ዑለማ የተወለዱት በዐረቢያ ነው ይባላል፡፡ የዘር ሀረጋቸውም ከነቢዩ ሙሐመድ ቤተሰቦች እንደሚመዘዝ ይነገራል። ወንድማማቾቹ በአስረኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ከዐረቢያ ወደ ዘይላ እንደመጡ በልዩ ልዩ ድርሳናት ተመዝግቧል። ሼኾቹ በዘይላ አካባቢ ከነበሩት የጎሳ መሪዎች ጋር በጋብቻ ከተሳሰሩ በኋላ መቀመጫቸውን በዚያው አደረጉ። እነዚህ ዑለማ በዘመናቸው በርካታ ተማሪዎችን ከማፍራታቸውም በላይ መስጂዶችንም አሳንጸዋል። እነርሱ ያስተማሯቸው ደረሳዎች (ተማሪዎች) በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በጅቡቲ ውስጥ በስፋት ተሰራጭተው እስልምናን አስተምረዋል። በኋላ ላይ ግን ሙሐመድ ወደ መሃል ኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ በኢፋት አካባቢ ከትመዋል፡፡ ዒስማኢል ግን እዚያው ዘይላ አካባቢ ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ በዚያችው ከተማ አርፈው “ሀደፍቲሞ” በተሰኘ ቀበሌ ውስጥ ተቀብረዋል፡፡
እነዚህ ሁለት ዑለማ ዛሬ ጀበርቲ ለሚባለው ማህበረሰብ መነሻ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ሆኖም በጀበርቲ ስም የሚጠሩት ማህበረሰቦች ሲደመሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በመሆናቸው ሁላቸውም ከሁለቱ ዓሊሞች የዘር ሀረግ የተገኙ ናቸው ለማለት አይቻልም። ከሁለቱ የጀበርቲ ሼኾች የተገኙ ዝርያዎች መኖራቸው ቢታመንም በጀበርቲ ስም የሚጠሩት ሁሉም ማህበረሰቦች የአንድ ቤተሰብ ተወላጅ ናቸው ማለቱ ብዙም አያራምድም፡፡ ጀበርቲዎቹ ራሳቸው የዘር ሐረጋቸውን ሲቆጥሩ በብዙ መልኩ የሚለያዩ መሆናቸው ሁላቸውም ከአንድ ግንድ አለመገኘታቸውን የሚያሳይ ፍንጭ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ “ጀበርቲ” እየተባሉ የሚጠሩት በርካታ ማህበረሰቦች እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ.?.. አሁንም የታሪክ ምሁራንን ዋቢ በማድረግ ትረካችንን እንቀጥል፡፡
*****
“ጀበርታ” የሚለውን ስም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመዘገበው የዐረቢያው የጂኦግራፊ ምሁር ኢብን ሰዒድ (1214-1287) ነው፡፡ ኢብን ሰዒድ ስለዚህ ስም የጻፈው “የኢፋት ሱልጣኔት ከዋናው ስም በተጨማሪ ጀበርታ ይባላል” በማለት ነው፡፡ በአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የኖረው ግብጻዊው ተቂኡዲን አል-መቅሪዚም ስሙን በመጽሐፉ ውስጥ በመጥቀስ “ክልሉ ጀበርታ የተባለው በጣም ሞቃታማ በመሆኑ ነው” የሚል ማብራሪያ አክሏል፡፡ እነዚህ የዐረብ ጸሐፊያን እንዳሉት በዚህ ስም በቅድሚያ የተጠራው የዘይላ ከተማ የምትገኝበት መሬት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት የአካባቢው ነዋሪዎች “ጀበርቲ” በሚለው የዐረቢኛ ቅጽል ታወቁ፡፡ የኢፋት ሱልጣኔት በ13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ወደ ምዕራብና ደቡብ ሲስፋፋ “ጀበርቲ” ከዘይላ ነዋሪዎች በተጨማሪ ሌሎች የኢፋት ነዋሪዎችንም የሚያመለክት ስያሜ ሆነ፡፡ ኢፋት የሁሉም እስላማዊ ሱልጣኔቶች ፖለቲካዊና መንፈሳዊ መሪ ሆኖ ሲወጣ ደግሞ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ሙስሊሞችንም “ጀበርቲ” እያሉ መጥራት ተለመደ፡፡ ከአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊም ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የነበራቸው ሚና እየጎላ ሲመጣም “ጀበርቲ” የሚለው ስም ከነርሱ ጋር በብርቱ የተቆራኘ ሆኖ ቀረ፡፡
የ“ጀበርቲ” ታሪካዊ መነሻ ይህንን ይመስላል፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ጀበርቲ የማህበረሰብ ስያሜ እንጂ በብሄረሰብ ወይም በብሄር ደረጃ የሚታይ ህዝብ አለመሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው “ጀበርቲ” ነው ከተባለ “ሰውዬው ሙስሊም ነው” እንደማለት ነው፡፡ እነዚህን ሙስሊም ማህበረሰቦች ከሚኖሩበት አካባቢ ካለው ህዝብ ለይቶ የማየቱ ሁኔታ የተፈጠረው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ ጀበርቲዎቹ በሚኖሩባቸው ክልሎች በሙሉ አናሳ (minority) ነበሩ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በጥንቱ ዘመን በነበረው አድሎአዊ ህግ መሰረት መሬትን በቋሚ ርስትነት መያዝ አይፈቀድላቸውም ነበረ፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ በንግዱ ላይ ነበር የተሰማሩት፡፡ በነዚህ ሁለት ምክንያቶች ነው ከሚኖሩበት ማህበረ ህዝብ የተለዩ ተደርገው ሲቆጠሩ የኖሩት፡፡
*****
በኢትዮጵያ ውስጥ ከጀበርቲ ማህበረሰብ ጋር በኢኮኖሚ ተዋስኦው የሚመሳሰል ሌላ ህዝብ አለ፡፡ ይህ ህዝብ “ወርጂ” ይባላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “ትግሪ ወርጂ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ህዝብ ንግድን የኢኮኖሚ መሰረቱ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተዋጣለት የነጋዴ ማህበረሰብ የሚባልበትን ቅጽል ለመጎናጸፍ ችሏል፡፡ ወርጂ በኢኮኖሚ ስምሪቱ ከጀበርቲ ጋር ከመመሳሰሉ የተነሳ በርካቶች የጀበርቲ ማህበረሰብ አካል በማድረግ ሲቆጥሩት ይታያል፡፡ በኔ ጥናት መሰረት ግን ወርጂና ጀበርቲ የተለያዩ ነገሮችን ነው የሚወክሉት፡፡
ጀበርቲ ማለት በጥቅሉ ሲታይ “ኢትዮጵያዊ ሙስሊም” እንደማለት ነው፡፡ ስያሜው በይበልጥ ነጥሮ ሲታይ ደግሞ ደግሞ በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያና በኤርትራ የሚኖሩ ሙስሊም ማህበረሰቦችን ነው የሚወክለው፡፡ ከዚያ ወረድ ብሎ ሲታይ ደግሞ ጀበርቲ ትውልዱ ከሼኽ ዒስማኢል ጀበርቲ እና ከሼኽ ሙሐመድ አል-ጀበርቲ ቤተሰቦች የተገኘ እንደማለት ነው፡፡ “ወርጂ” ግን ከጥንት ጀምሮ እንደ አንድ ብሄረሰብ ይታወቅ የነበረ ህዝብ ነው፡፡ የአጼ አምደ-ጽዮን ገድል በተጻፈበት ዘመን የወርጂ ህዝብ በታችኛው አዋሽ እና በአዳል መካከል ተስፋፍቶ ይኖር ነበረ፡፡ እነዚህ ወርጂዎች በዚያ ዘመን ከብት አርቢዎች ነበሩ፡፡ በአጼ አምደ-ጽዮን ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት በማመጻቸው አጼው ከፍተኛ የቅጣት እርምጃዎችን እንደወሰደባቸው የአጼው ገድል በስፋት ያስረዳል፡፡
ግብጻዊው አል-መቅሪዚ በበኩሉ (1400-1444) ስለ ኢትዮጵያ ሱልጣኔቶች ታሪክ ሲጽፍ “ወርጂ” የሚባል አርብቶ አደር ህዝብ በኢፋት ሱልጣኔት ይኖር እንደነበረ ነግሮናል፡፡ ይህ ህዝብ እስከ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ዘመን ድረስ ከየረር ተራራ በስተምስራቅ ጀምሮ እስከ ዛሬው የአፋር ክልል ምዕራባዊ ክፍል ድረስ ይኖር ነበር፡፡ ማህበረሰቡ በኢማም አሕመድ ዘመን ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አራሽነት እየተቀየረም ሄዷል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰቱት ታላላቅ ክስተቶች ግን የመላውን የምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች ዲሞግራፊያዊ ተዋጽኦ ከስረ-መሰረቱ ቀየሩት፡፡ በዚህም መሰረት ከፊሉ የወርጂ ህዝብ በአፋር ህዝብ ተዋጠ፡፡ ከፊሉ ግን ከየረር ተራራ አቅራቢያ መኖሩን ቀጠለ፡፡ ይህኛው ክፍል እያደር ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በጋብቻና በሞጋሳ ስልት እየተዛመደ ራሱን የኦሮሞ ህዝብ አንድ አካል አድርጎ መቁጠር ጀመረ፡፡
የአጼ ምኒልክ አያት የነበሩት ንጉሥ ሣህለ ስላሤ ወደ ደቡብ መስፋፋት በጀመሩበት ጊዜ በቅድሚያ ከወጓቸው ማህበረሰቦች መካከል አንዱ ይህ የወርጂ ህዝብ ነው፡፡ የዘመኑ ሙስሊሞች ርስት መያዝ አይፈቀድላቸውም በሚለው የሰለሞናዊያን ህግ መሰረትም ወርጂ መሬቱን አጣ፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ሌሎች ስፍራዎች እየፈለሰ በንግድ ስራ ላይ መሰማራት ጀመረ፡፡
የወርጂ ማህበረሰብ ከታሪክ ሰነዶች ከታወቀበት ዘመን ጀምሮ በእስልምና ሃይማኖት ተከታይነቱ ነው የሚታወቀው፡፡ ጥንት ይኖርበት የነበረው መሬትም በተለያዩ ዘመናት የተነሱት የሸዋ፣ የኢፋት እና የአዳል እስላማዊ ሱልጣኔቶች አካል ሆኖ ነበረ፡፡ ይሁንና የህዝቡ መነሻ ከዐረቢያ ነው እየተባለ አልፎ አልፎ የሚነገረውን ታሪክ ከሰነዶች ለማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡
*****
ከላይ እንደገለጽኩት የወርጂ ህዝብ በጥንተ መሰረቱ እንደ አንድ ብሄረሰብ ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ህዝቡ የራሱ ቋንቋ የነበረው ለመሆኑ በተጨባጭ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እኔ ጸሐፊው “ወርጂ በጥንተ መሰረቱ እንደ ብሄረሰብ ሊታይ ይችላል” የምለው የጥንቱ ሰነዶች ከሌሎች ህዝቦች የተለየ አንድ ራሱን የቻለ ህዝብ አድርገው ስለሚቆጥሩት ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወርጂ የኦሮሞ ህዝብ አካል ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋውም ቢሆን ኦሮምኛ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ በብዙ የኦሮሞ ጎሳዎች ውስጥ “ወርጂ” እየተባለ የሚጠራ ንዑስ ጎሳ አለ፡፡
እንደዚያም ሆኖ ግን የወርጂ ህዝብ ከሌሎች ኦሮሞዎች የሚለይበትን አንዳንድ መለያዎች ለማስጠበቅ የቻለ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ወርጂ የሚኖረው በሸዋ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ በክፍለ ሀገሩ ከሚኖሩት በርካታ የኦሮሞ ማህበረሰቦች መካከል ሙሉ በሙሉ ሙስሊም የሆነው ወርጂ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ወርጂዎች የትም ሆነው በኦሮምኛ ሲነጋገሩ በድምጽ አወጣጥ ስልታቸው በቀላሉ ሊለዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በኦሮምኛ “dhufe” ከተባለ “መጣ” ማለት ነው፡፡ ወርጂዎች በኦሮምኛ ሲናገሩ ግን “ufe” ነው የሚሉት እንጂ dhufe አይሉም፡፡ በብዙ ስፍራዎች የገጠሙኝ የወርጂ ተወላጆች “dh” የተሰኘውን የኦሮምኛ ድምጽ በ“a” ስልት ነው የሚያስኬዱት፡፡ ይህ ለየት ያለ የአነጋገር ዘይቤ እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ አንድ ተመራማሪ በዚህ ዙሪያ ጥናት ቢያደርግ አዲስ ነገር ሊያሳውቀን እንደሚችል አምናለሁ፡፡
*****
ጀበርቲ እና ወርጂ በጨረፍታ ሲታዩ ከላይ የቀረበውን ይመስላሉ፡፡ ይህንን ጽሑፍ የከተብኩት ከልዩ ልዩ አንባቢዎች ሲቀርቡልኝ የነበሩ ጥያቄዎችን በትንሹም ቢሆን ልመልስ ብዬ ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረጃና ማስረጃ ያላቸው ወገኖቻችን ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንጠብቃለን፡፡
ሰላም ብያለሁ!!
አፈንዲ ሙተቂ
ሰኔ 23/2007
ሀረር-ምሥራቅ ኢትዮጵያ
*****
የመረጃ ምንጮች
—
1. አፈንዲ ሙተቂ፤ “አዳል-ስመ ገናናው ሱልጣኔት እና የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አል-ጋዚ ዘመቻዎች”፤ (ለህትመት የተዘጋጀ መጽሐፍ)
2. አሕመዲን ጀበል፤ “ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች”፤ 2003፤ አዲስ አበባ
3. Johon S. Triminghamm: Islam in Ethiopia: 1952
4. Ulrich Braukamper: Islamic History and Culture in Southern Ethiopia: 2003
5. ልዩ ልዩ ቃለ-ምልልሶች
አፈንዲ ሙተቂ/Afendi Muteki- Ethnographic Researcher and Author