
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ድምጻችን ይሰማ” የተባለው አካል እንዳለው ከሆነ፤ “ችሎቱን በሰላም ተከታትለን ወደመጣንበት እንመለሳለን” በማለት አሳስቧል። ትላንት ማታ የተለቀቀው መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ የሚከተለው ነው።
ሰላማዊነት – ስናስመሰክረው የቆየነው የትግላችን ባህሪ!
ችሎቱን በሰላም ተከታትለን ወደየመጣንበት እንመለሳለን!
ረቡእ ሰኔ 24/2007
ነገ በወኪሎቻችን ተወክለን በችሎት የምንቀርብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ችሎትም በአገሪቱ ውስጥ ውጤታቸው በጉጉት ከሚጠበቁ ታሪካዊ ገጠመኞች አንዱ ነው – እውነት ከሐሰት፣ ግፍ ከፍትሕ የሚተናነቁበት ታሪካዊ ገጠመኝ! በዚህ እጅግ አስፈላጊ ወቅት ሁላችንም በነቂስ ወጥተን ችሎቱን መከታተል የሚኖርብን ሲሆን የትግላችንን መሰረታዊ መገለጫዎች እና ባህሪዎች ቋሚነት አስጠብቆ መራመድም ከምንም በላይ አስፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡
በታሰበው መሰረት ከተካሄደ የዛሬውን ችሎት አስመልክቶ የሚኖሩ መረጃዎችን እና ዜናዎችን ይህንን ገጻችንን ጨምሮ ሁልጊዜም የተጣራ መረጃ ከሚያደርሱን የሕዝበ ሙስሊሙ የመረጃ ምንጮች ላይ ብቻ መውሰድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለችሎቱ ሂደት አስፈላጊ የሆነው መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረጉ ሂደት አንዳንድ አላስፈላጊ ግርግር መፍጠር በሚፈልጉ እና በትግሉ ሂደት እስካሁን በመረጃ አድራሽነት ያልታወቁ አካላትን መረጃ አምነን ከመቀበል ልንቆጠብ ይገባል፡፡ ሁኔታውን ሙስሊሙን ለማጥቂያነት እንደመልካም አጋጣሚ በሚቆጥሩ መሰሪ ካድሬዎች እና ደህንነቶች አማካኝነት ያልተጣሩ መረጃዎችን በመበተን ችግር ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን ማምከን የሚቻለውም ወትሮ በታማኝነት መረጃ ከሚያደርሱን ገጾች፣ አክቲቪስቶች እና የሚዲያ ተቋማት ውጭ የሚገኙ መረጃዎችን ሳያጣሩ ባለመቀበል እና በመጠንቀቅ ነው፡፡
የመንግስት ብይን የጠበቅነውም ሆነ ያልጠበቅነው ቢሆን እንደህዝብ ልንወስዳቸው የምንችላቸው እርምጃዎች እና ስነስርዓቶች በሙሉ እስከዛሬ እንደነበረው ሂደት ሁሉ በዚሁ ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ገጽ የሚገለጹ በመሆኑ ያልተፈለገ ድርጊት ውስጥ ከመግባት በእጅጉ እንድንቆጠብ አጥብቀን አደራ እንላለን፡፡ በነቂስ ወጥተን ችሎቱን ከተከታተልን በኋላም የኹከተኞችን ጥሪ ባለመመለስ በሰላም ወደየመጣንበት መመለስ ይኖርብናል፡፡ ኃይላችን አንድነታችን በመሆኑ እንደተለመደው የተናበበ አካሄዳችንን ጠብቀን እና አጥቂዎቻችን ወደሚመኙልን የኹከት አቅጣጫ ከመግባት ተቆጥበን አስፈላጊውን ሰላማዊ እርምጃ ልንራመድ ይገባል፡፡ ይህ ለሶስት ዓመታት የለፋንበት ሰላማዊ ትግል መና እንዳይቀር ልንወስደው የሚገባው የግዴታ ጥንቃቄ ነው! ይህንን ማሳሰቢያ ላልሰሙት ሁሉ በማሰማት የትግላችንን ሰላማዊ ባሕሪ አስጠብቀን ለመጓዝ እንረባረብ፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና! ኮሚቴዎችን በነጻ ከማሰናበት ያነሰ አንዳችም ብይን አንቀበልም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!