Wednesday, 01 July 2015 13:3

 በአማራ ክልል ከአስር በላይ አባሎቼና የዞን አመራሮች 

ለእስር ተዳርገዋል
መኢአድ

 

በይርጋ አበበ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የፓርቲው ዋና ጸሀፊ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን እና ዋና ሰብሳቢውን መምህር ስማቸው ምንይችልን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው የዞንና የወረዳ አመራሮች እና የፓርቲው አባላት ለእስርና ለአፈና መዳረጋቸውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አስታወቀ። በዞኑ የፓርቲውን አመራሮች ጨምሮ ሌሎች ከአስር በላይ አባሎች ለእስር መዳረጋቸውን የመኢአድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙሉጌታ አበበ ለሰንደቅ በስልክ እንደገለጹት መቶ አለቃ ጌታቸው ከአራት ወራት የማዕከላዊ ምርመራ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ይገኛሉ። በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ መምህር የሆኑት አቶ ስማቸው ምንይችል ደግሞ ከሰኔ 18 ጀምሮ ከመኖሪያ ቤታቸው ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በአሁኑ ሰዓት የት እንዳሉ አይታወቅም።
በቡሬ ከተማ የወረዳው የፓርቲው ኃላፊ አቶ አበባው አያሌው ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከአንድ የፓርቲው አባል እና ሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በሚዝናኑበት ወቅት በከተማው የጸጥታ ሀይል ተይዘው ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። በቡሬ ወረዳ ቡሬ ከተማ ፓርቲያቸውን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት አቶ አበባው አያሌው በቡሬ ዙሪያ ሸዳ ወረዳ በመንግስት ስራ የሚተዳደሩና የሶስት ልጆች አባት መሆናቸውን የገለጹት የመኢአድ ስራ አስፈጻሚ አባል “ከቡሬ ወደ ባህርዳር ከተወሰዱ በኋላ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው በፖሊስ ጥያቄ ብቻ እስከ ሃምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ እስር ወርደዋል” ብለዋል። የግለሰቡ የስነ ምግባርና የስራ ቦታ ሁኔታ ምን ይመስላል ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ “ግለሰቡ በጸጥታ ሀይሎች በግፍ እስከተያዘበት እለት ድረስ በስራውም ሆነ በማህበራዊ ህይወቱ ጤናማ እና ታታሪ ነው። ለእስር የተዳረገው በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብሮ ለሰንደቅ እንዳስታወቁት የፓርቲያቸው አባል እና በ2007 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ አበረ ሙሉ ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም በቡሬ ከተማ ወረዳ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል። አቶ ተሻለ ሰብሮ የኢራፓ አባሉ ከመታሰራቸው በፊት በተጠቀሰው ቀን ምሽት ቤታቸው በስምንት የወረዳው የጸጥታ ሀይሎች ተከብቦ እና ግለሰቡም በሀይል እንደተያዘ ገልጸዋል።
የኢራፓ አባሉ አቶ አበረ ሙሉ በአሁኑ ሰዓት በባህር ዳር ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ተሻለ “አባላችን ለፓርቲያቸው ታማኝና በስራቸውም የተመሰገኑ ናቸው። በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ነው ለእስር የተዳረጉት” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን የሁለቱን ፓርቲዎች ቅሬታ እንዲመልሱልን ወደ ቡሬ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አየለ ቡሬቲ ደውለን ነበር። ኢንስፔክተር አየለ ቡሬቲ “ማንነቱን በአካል ቀርቦ ለማይገልጽ ግለሰብ መረጃ የመስጠት ግዴታ የለብኝም” ካሉ በኋላ “ታሰሩ ስለተባሉት ግለሰቦችም ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። የወረዳው የወንጀል ምርመራ ኃላፊ እንደመሆኔ እኔ ሳላውቀው የሚታሰር ግለሰብ የለም” ብለዋል።
መኢአድና ኢራፓ ታሰሩብን ያሏቸው አባሎች በተለያየ ቦታ የሚኖሩ ቢሆንም ከመቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን ውጭ ያሉት ሌሎቹ የሁለቱ ፓርቲ አባላት በጸጥታ ሀይሎች የተያዙት ግን በተመሳሳይ እለት ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም መሆኑን ገልጸዋል።

Leave a Reply