01 JULY 2015 ተጻፈ በ 

በተለያዩ ዓረብ አገሮች በተለይም በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ከደረሰውን አሰቃቂ ግድያ፣ አካል ማጉደልና እንግልት በኋላ፣ መንግሥት ዜጎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንዳይሄዱ ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመሄድ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ በአገሪቱ መንግሥት እንዲወጡ የተሰጣቸውን የጊዜ ገደብ ባላከበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ይታሳቃል፡፡ በዜጎች ላይ የደረሰው ሞት፣ እንግልትንና አካል መጉደል መላው ኢትዮጵያውያንና ዓለምን ካነጋገረ በኋላ መንግሥት በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ዜጎች እንዳይሄዱ ዕግድ ሲጥል፣ በአጭር ጊዜ ወደ ውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች እንዴት መሄድ እንደሚገባቸውና ከመሄዳቸው በፊት ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርቶች በሚመለከት አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያቀርብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተናግረው ነበር፡፡

የውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎችም፣ ዜጎችን በምን ዓይነት መንገድ መመልመል እንደሚገባቸውና ማሟላት ያለባቸው መሥፈርት ምን ምን እንደሆነ በሚመለከተው አካል እስከሚገለጽላቸው ድረስ ዜጎችን ለሥራ ወደ ውጭ መላክ እንዳይችሉ ታግደዋል፡፡ በተለይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ማለትም በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያና በዚምባቡዌ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ በሱዳን፣ በሊቢያ፣ በኒጀርና በማልታ አድርገው ወደ ጣሊያን፣ ግሪክና እስራኤል፣ በፑንትላንድ (ቦሳሶ ከተማ) በሶማሊያና በጂቡቲ አድርገው ወደ የመን በሕገወጥ መንገድ በሕገወጥ ደላሎች የሚላኩ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ችግር በመጋለጣቸው፣ መንግሥት አስቸኳይ ጥናት በማድረግ መፍትሔ እንደሚሰጥም ገልጾ ነበር፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራና ለዜጎችም ይሁን ለአገር የማይጠቅም በመሆኑ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚሠራ፣ ሁሉም ክልሎችና አብዛኛዎቹ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ማለትም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የደኅንነትና ኢሚግሬሸን፣ የሕፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች ሚኒስቴር ወዘተ የተካተቱበት ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቁሟል፡፡

ምክር ቤቱ በየስድስት ወራት እየተገናኘ በየክልሎች ስላለው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሠራውን ሥራ በመገምገምና መሻሻል ያለባቸውን እንዲሻሻሉ ሐሳብ በመስጠት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ከርሟል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውንና ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ሲገልጹ ከርመዋል፡፡ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር እየተሰበሰበ ክልሎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሠሩትን ሪፖርት ከማዳመጥ ባለፈ፣ በተግባር ተፈጽሞ የታየ ወይም ለሕዝብ ይፋ የተደረገ ነገር የለም፡፡

እንዲያውም መንግሥት የጣለውን ዕግድ ተከትሎ ሕገወጥ ስደቱ እየተባባሰና በየጊዜው በዜጎች ላይ እየደረሰ የሚታየው ሰቆቃ ተባብሶ መቀጠሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጉዳዩ በዋናነት የሚመለከተው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዕግዱ ከተጣለ አንድ ዓመት ቆይታ በኋላ፣ በ2001 ዓ.ም. ወጥቶ ሥራ ላይ የነበረውን የሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001ን የሚተካ ረቂቅ አዋጅ በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ ውይይት የተካሄደበት ቢሆንም እስካሁን አልፀደቀም፡፡

መንግሥት በሕጋዊ መንገድ የሚሄዱትን ጭምር ያገደ ቢሆንም፣ ዜጎች ግን እስካሁን በተለያዩ መንገዶች በሕገወጥ ደላሎች አማካይነት ከመሄድ አለመገታታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አደጋውም በዚያው ልክ እየደረሰ ነው፡፡ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አይኤስ የተባለው የሽብር ቡድን ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግድያ፣ ዓለምን ጭምር ያሳዘነ ድርጊት መሆኑ ይታወሳል፡፡ አሰቃቂ ግድያው የተፈጸመባቸው ወጣት ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሊቢያ የተጓዙት በሕገወጥ መንገድ ዜጎች እንዳይሄዱ መንግሥት ዕግድ ከጣለ በኋላ ነበር፡፡ በወጣቶቹ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ግድያ ለጊዜው የሁሉንም ልብ የነካና አሳዛኝ ከመሆኑ አንፃር ሕገወጥ ስደቱ ጋብ ያለ ቢመስልም፣ መልሶ ማገርሸቱን የተለያዩ ተቋማት ሪፖርት እያደረጉ ነው፡፡

በመንገድ ላይ ያለው ረቂቅ ሕግ ትኩረት ተሰጥቶትና ዜጎችን በሚጠቅም መንገድ ውይይት ተደርጎበት ተግባር ላይ ካልዋለ፣ ሕገወጥ ስደቱ እየባሰበት እንደሚሄድ በተለያዩ ወገኖች አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው የመን በኩል የሚደረገው ሕገወጥ ጉዞ ጋብ ከማለቱ በስተቀር፣ በቅርቡ በአሰቃቂ ሁኔታ አንገታቸውን በተቀሉባት አገር ሊቢያ ጭምር ዜጎች እየሄዱ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሕጉን ለማፅደቅ ለጉዳዩ አስተማማኝ እልባት እንዲሰጠው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በሕጋዊ መንገድ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተውና ከ3,000 በላይ ሠራተኞችን ቀጥረው በመሥራት ላይ የነበሩ ከ400 በላይ የውጭ ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች አደጋ ውስጥ መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የሠራተኛ ደመወዝና የቤት ኪራይ ላለፉት ሁለት ዓመታት በመክፈል ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ሴክተሩን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ከፈለገ ሊያሳውቃቸው ሲገባ፣ ከነገ ዛሬ አዋጅ እንደሚፀድቅ ተስፋ እየሰጣቸው ለኪሳራ መዳረጋቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ ‹‹አዋጁ አሠራንም አላሠራን ተግባራዊ ሆኖ ለማየት ብንፈልግም የውኃ ሽታ መሆኑ እኛንም አገርንም እየጎዳ ነው፤›› ያሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአንድ ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊ ላቸው፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ሕገወጥ ደላሎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ይናገራል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉትንና በውጭ አገር ሆነው ከፍተኛ ሕገወጥ የድለላ ሥራ የሚሠሩትን ደላሎች በኢንተርፖል አማካይነት ወደ አገር ውስጥ እያስመጣ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርምራ ዘርፍ ዲቪዚዮን በኢንተርፖል በኩል ከተለያዩ አገሮች ወደ አገር ቤት ካስመጣቸው ሕገወጥ ደላሎች በምርመራ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በቅርቡ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሕገወጥ ደላሎችን ከሰባት የአፍሪካ አገሮች ተላልፈው እንደሚሰጡ አስታውቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርምራ ዘርፍ ዲቪዚዮን ከዓለም አቀፍ ፖሊስ (ኢንተርፖል) ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት አማካይነት፣ ስምምነቱ ካላቸው አገሮች ተላልፈው ከተሰጡ ተጠርጣሪዎች በምርምራ ካገኘው መረጃ በመነሳት፣ በሰባት የአፍሪካ አገሮች ያሉ ሕገወጥ ደላሎች ተላልፈው እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን  ገልጿል፡፡

ሕገወጥ ደላሎቹ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካና የመን ውስጥ እንደሚገኙና ማንነታቸውና አድራሻቸው ተጣርቶ መታወቁም ተገልጿል፡፡

በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ የሚገኙት በአገር ውስጥ የነበሩና ከተለያዩ አገሮች ተላልፈው የተሰጡ ሕገወጥ ደላሎች፣ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሞትና መሰደድ ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን የሚጠቁመው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ በሊቢያ አይኤስ የተባለው የሽብር ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግድያ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ ስደቱ ጋብ ያለ ቢመስልም አሁን እየተባባሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በየመን በኩል የሚደረገው ሕገወጥ ጉዞ ጋብ ያለ ቢሆንም፣ ከመተማ ወደ ሱዳን የሚደረገው ሕገወጥ ጉዞ እየባሰበት መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ በአፋር አድርጎ በጂቡቲ በኩል ያለው እንደ ሌሎቹ የባሰ ባይሆንም አሁንም ዜጐች እየተሰደዱ ነው፡፡

የሕገወጥ ደላሎች ያላቋረጠ ሕገወጥ ተግባር ወደተለያዩ አገሮች የሚጓጓዙትን ኢትዮጵያውያን ሞት እያፋጠነ ቢሆንም፣ ሕጋዊ ቪዛ አግኝተው የሚወጡትም የሚገጥማቸው ዕድል ተመሳሳይ መሆኑን ዲቪዚዮኑ ገልጾ፣ በመንገድ ላይ ያሉትን ረቂቅ ሕጎች አፅድቆ ሕጋዊ መስመሩን ማስፋት ካልተቻለ የዜጎች ጉዳት ቀጣይነት እንደሚኖረው ሥጋቱን ገልጿል፡፡

አሁን ትልቁ ጥያቄ ሕገወጥ ስደትን የሚያስቀረውና ሕጋዊውን መንገድ ብቻ ያመቻቻል የተባለለት ረቂቅ ሕግ መቼ ተግባራዊ ይደረጋል የሚለው ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ያለውስ ቁርጠኝነት እንዴት ሊገልጽ ይችላል የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰንሰለት በርካታ የጥቅም ተጋሪዎች ስላሉበት እንዴት ሊበጠስ ይችላል ተብሎም ይጠየቃል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ናቸው የመንግሥት ቁርጠኝነት በተግባር እንዲታይ የሚገፋፉት፡፡

Leave a Reply