- የአስተዳደር ሓላፊዎቹ÷ የተዛቡ መረጃዎችንና ያልተጨበጡ ወሬዎችን እየነዙ በተለይ በሒሳብ አሠራር፤ በቆጠራ አካሔድ፤ በኦዲት ክንውን፤ በንብረት አያያዝ እና በግዢ ሥርዐት ዙሪያ ሰበካው በተለያዩ ጊዜያት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና መመሪያዎችእንዳይተገበሩ አድርገዋል፡፡
- በፓትርያርኩ እና በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተሰጣቸው ተስፋ ከተግባር የራቀባቸው የሰበካ ጉባኤው አባላት፣ ከሚመለከታቸው የፍትሕ እና የጸጥታ አካላት ጋር እየመከሩበት ነው፡፡
- ‹‹ምእመኑን ጃኬት ለባሽ አይመራንም እያሉ የሚንቁት ጫንቃቸው ያበጠ እና ማሰቢያቸው የተደፈነ አማሳኞች÷ ዕጣን ቋጥሮ ግብር ሰፍሮ የሚሰጠውን አስተዋፅኦ እና የሚያስገባውን የሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ያለተጠያቂነት በየወሩ ከ70 – 80 ሺሕ ብር እየመዘበሩ የመሬት፣ የቤት እና የተሽከርካሪዎች ባለቤት የኾኑ ናቸው፡፡››
* * *
በማኅበረ ካህናት፣ በማኅበረ ምእመናን እና በሰንበት ት/ቤት ምልዓተ ጉባኤ ተመርጦ የገዳሟን የተከማቹ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የቆየው የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ÷ በአማሳኝ የጽ/ቤት እና የአስተዳደር ሓላፊዎች ሕገ ወጥ ርምጃ ታገደ፡፡
‹‹የሰበካ ጉባኤ የሥራ አባላት ማገድን ይመለከታል›› በሚል ርእስ በገዳሟ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ተጠምቀ መድኅን ገብረ ኢየሱስ ተፈርሞ የወጣው የእገዳ ደብዳቤው÷ የሰበካ ጉባኤው አባላት በአስተዳደሩ ጽ/ቤት፣ በገዳሟ ቅጽር እንዲኹም በተለያዩ ቦታዎች ስብሰባ ማድረግ እንደማይችሉ ያስታውቃል፤ አድርገው ቢገኙም ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ መኾናቸውን ያስጠነቅቃል፡፡
በደብዳቤው የተጠቀሱት የሕገ ወጡ እገዳ ምክንያቶች፣ ሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲውን መሠረት በማድረግ ካወጣቸው የመተዳደርያ ደንብ እና የአሠራር መመሪያዎች እንዲኹም የአስተዳደር ሓላፊዎቹ በኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን ህልውና እና የአባቶችን ክብር የሚነካ የስም ማጥፋት ተፈጽሞበታል›› ከሚሉት አንድ ዘገባ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ለዘረፋ፣ ለብክነት እንዲኹም ለሙስና የተመቻቸ ነው የተባለውን የቀድሞውን አሠራር በማስቀረት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፍናል የተባለው የሰበካ ጉባኤው ደንብ እና መመሪያዎች ረቂቅ፣ እንደ አስተዳደር ሓላፊዎቹ ግምገማ‹‹ከየት መጣ የማይባል፣ ለቤተ ክርስቲያኗ የማይጠቅም ወፍ ዘራሽ የካምፓኒ ድርጅት ውስጠ ደንብ እና መመሪያ›› ነው፡፡ ‹‹ገዳሟ ሥርዐት እንደሌላት የግድ መቀበል አለባችኹ›› በሚል ጭቅጭቅ በገዳሟ ሰላምና አንድነት ጠፍቶ የንትርክ አውድማ ኾናለች ብለዋል፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር፣ ‹‹በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ምርመራ እንዲካሔድ ተጠየቀ›› በሚል ርእስ የኢትዮ-ምኅዳርጋዜጣ÷ የፓትርያርኩ የኦዲት ክንውን ትእዛዝ ተፈጻሚ እንዲኾን፤ ሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲውን መሠረት አድርጎ ያወጣው ደንብ እና መመሪያዎች እንዲተገበሩ፤ ለውስጥ አገልግሎቱ እና ለአስተዳደሩ የገዳሟን ክብር የሚመጥን ብቃትና ታማኝነት ያለው የሰው ኃይል እንዲመደብ፤ በአምሳላቸው እንደተለወጡ በሚጠረጠሩ ጽላት ላይ ምርመራ እንዲካሔድ፤ የስእለት እና የስጦታ ቅርሶችንና ንዋያትን እየዘረፉ በሚሸጡ፤ በአስነዋሪ ተግባር ክብረ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስደፍሩ ካህናት ላይ ርምጃ እንዲወሰድ የሚያትት ዜና ቢያወጣም በአስተዳደር ሓላፊዎቹ ‹‹ፀረ ሃይማኖት›› በሚል ተኮንኗል፡፡
ለዜናው የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ሰበካ ጉባኤውን በተባባሪነት ከሠዋል፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን ህልውና እና የአባቶችን ክብር የሚነካ ነው›› ባሉት በዚኹ ዘገባ በእጅጉ ማዘናቸውን የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ገልጸው፣ ሰበካ ጉባኤው አንዳችም ማስተባበያ ባለማድረግ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱን አስደፍሯል›› ብለዋል፡፡
ሰበካ ጉባኤው ከሓላፊነት እንዲወርድና በሌላ እንዲተካ ግንቦት 18 ቀን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በተገኙበት በምልዓተ ጉባኤመወሰናቸውንና ይህንኑም ሰኔ 11 ቀን ለሚመለከተው አካል ማሳወቃቸውን ያስታወሱት የአስተዳደር ሓላፊዎቹ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን በጃኬት ለባሽ የማትመራ መኾኗን ማወቅ ያስፈልጋል›› በማለት ነው ሕገ ወጥ እገዳቸውን ያስታወቁት፡፡ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት አሠራር ውጭ የኾኑት ታጣቂዎቹ አማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎች÷ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሳቢነት በማኅበረ ካህናት፣ በማኅበረ ምእመናን እና በሰንበት ት/ቤት ምልዓተ ጉባኤ የተመረጠውንና ተጠሪነቱ ለአጥቢያው ካህናት እና ምእመናን ጠቅላላ ጉባኤ የኾነውን ሰበካ ጉባኤ የማገድ ሥልጣን ባይኖራቸውም ለሕገ ወጥ አካሔዳቸው ዋና መከታ ያደረጉት የፓትርያርኩን ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን እንደኾነ ተገልጧል፡፡
የሰበካ ጉባኤው በአሠራር እያጠናከረ በመጣው የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ቁጥጥር የተነሣ ከአማሳኝ በአስተዳደር ሓላፊዎቹ በኩል የሚቀርብላቸው ፈሰስ የቀረባቸው ንቡረ እዱ፣ የገዳሟ የልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ለፓትርያርኩ የሚቀርቡ የማኅበረ ካህናቱንና የማኅበረ ምእመናኑን አቤቱታ ሲያፍኑ ቆይተዋል፡፡
የአፈና ሚናቸውን በማጋለጥ ለችግሩ መባባስ ተጠያቂ እንደኾኑ በሚገልጹ የጋዜጣ ዘገባዎች በእጅጉ የተበሳጩት ንቡረ እዱ ጋዜጦቹን እንዲከሠሡ በማድረግ አልተወሰኑም፡፡ ‹‹የሙስና አባቱ፤ የአማሳኞች ካቢኔ ሊቀ መንበሩ›› ልዩ ጸሐፊው፣ የሀገረ ስብከቱን ግብረ አበሮቻቸውን በመጠቀም ከሰበካ ጉባኤው ጋር ይተባበራሉ የተባሉ የገዳሟ ሊቃውንትና ካህናት ከሥራና ከደመወዝ አሳግደዋል፤ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች አሸማቅቀዋል፤ አኹን ደግሞ ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን ሰጥተው በታማኝነት እና በትጋት የሚያገለግሉ የሰበካ ጉባኤው አባላት ‹‹ጃኬት ለባሽ››ተብለው እንዲታገዱና ጨርሶ በቅጽሩ እንዳይሰበሰቡ አስከልክለዋል፡፡
ንቡረ እዱን መከታ በማድረግ የሰበካ ጉባኤውን አባላት፣ ‹‹ከኛ ጋር ተስማሙ፤ በሰላም ብትለቁልን ይሻላችኋል፤ ዐርፈኽ ቤተሰብኽን ብትመራ ይሻልሃል፤ትቦህን ነው የምበጥስልኽ…›› በሚሉትና በመሳሰሉት ማስፈራሪያዎች በሰበካ ጉባኤው ላይ በየጊዜው ሲዝቱ የቆዩት ታጣቂ የገዳሟ ሓላፊዎች፡-
- መጋቤ ሥርዐት ኃይለ ጊዮርጊስ ዕዝራ – ጸሐፊ
- መ/ር ክብሮም ገብረ ትንሣኤ – ሒሳብ ሹም
- ዲ/ን መንክር ጸጋዬ – የንብረት ክፍል ሓላፊ
- መ/ታ ይትባረክ ወልደ ሥላሴ – ገንዘብ ያዥ
- መልአከ ብሥራት አባ ወልደ ትንሣኤ አዳም – ዕቃ ግዥ፣ የልማት ገንዘብ ተቀባይ፣ ንብረት ቁጥጥር፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ያዥ
- ቄሰ ገበዝ አባ ሳሙኤል ቀለመ ወርቅ – ቄሰ ገበዝ ናቸው፡፡
ሓላፊዎቹ፣ በተለይ ሒሳብ ሹሙ መ/ር ክብሮም ገብረ ትንሣኤ፣ በገዳሙ አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በፈጠሩ ከፍተኛ የአሠራር ድክመት እና የአቅም ማነስም የሚታወቁ ናቸው፡፡ ጸሐፊው መጋቤ ሥርዐት ዕዝራ ኃይለ ጊዮርጊስ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በሰነድ ማጭበርበር ለተፈጸመው ከፍተኛ ምዝበራ ተከሠው የኹለት ዓመት እስራት በገደብ እና ብር 5000 የገንዘብ ቅጣት ከተላለፈባቸውአንዱ ናቸው፡፡ የቀድሞው ተቆጣጣሪ የነበሩትና ከተጠቀሱት ባላነሰ ተጠያቂነት ያለባቸው መ/ታ ምሥራቅ ዘውዴ አኹን ሀገረ ስብከቱ በያዘው በጥቅም ትስስር እና በበቀል ላይ የተመሠረተ የማዘዋወር አሠራር ወደ ሌላ ደብር ተቀይረዋል፡፡
በሴሰኝነታቸው የታወቁት መልአከ ብሥራት አባ ወልደ ትንሣኤ አዳም እና በዚኹ ነውር በሔዱባቸው ቦታዎች ኹሉ ተደጋጋሚ ቀኖናዊ ውሳኔ የተላለፈባቸው ቄሰ ገበዝ አባ ሳሙኤል ቀለመ ወርቅ ክብረ ታቦትን የሚያቃልሉ ናቸው፡፡ መተዳደርያ ደንቡንና መመሪያዎቹን በመቃወም በተዛቡ መረጃዎች ማኅበረ ካህናቱን ከመከፋፈል ባሻገር ሰበካ ጉባኤውን ለማፍረስ በአባልነት የተመረጡ ተወካይ ካህናት፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፤ በፔይሮል ይከፈላቸዋል›› በሚል ከሥራና ከደወመዝ እንዲታገዱ፤ በሞያቸው የተመሰገኑ ሊቃውንት ከሰበካ ጉባኤው ጋር ታይተዋል በሚል ብቻ አግባብነት በሌለው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤ በመጨረሻም ሰበካ ጉባኤውን በማሳገድ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡
ሰበካ ጉባኤው እንደሚገልጸው፣ የውስጥ መተዳደርያ ደንብና መመሪያዎች ረቂቆቹ፣ የቃለ ዐዋዲውን መሠረታዊ ሐሳብ ሳይለቅ ለማውጣት በአንቀጽ ፲፪(፳፩) በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የውስጥ መተዳደርያ ደንቡ ረቂቅ ሊቃውንቱን ጨምሮ በማኅበረ ካህናት እንዲገመገም፤ የፋይናንስ፣ የንብረት፣ የግዢ መመሪያዎች ረቂቆቹ ደግሞ በአስተዳደር ሓላፊዎች አስተያየት እንዲሰጥበት ተባዝቶ መሰራጨቱንና ገና ውይይት እንዳልተካሔደበት ሰበካ ጉባኤው ጠቅሶ ‹‹ገዳሟን የጭቅጭቅና የንትርክ አውድማ አድርጓል›› መባሉን አስተባብሏል፡፡
አያይዞም መመሪያዎቹ፣ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ቀድሞ ሲዘርፉበት የነበረውን አካሔድ የሚያስቀሩና ካለአግባብ የሚያካብቱትን ጥቅም የሚያስቆሙ መኾናቸው የገለጸው ሰበካ ጉባኤው፣ ‹‹በገዳሚቱ ውስጥ ለሚደረገው የቤተ ክርስቲያንን መልካም አስተዳደር የማስፈን ሥራ ዕንቅፋት ኾነው ቢቀርቡ አይደንቅም፤›› ብሏል፡፡
የጀመረውን የመልካም አስተዳደር ውጥን ከፍጻሜ ለማድረስ የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የአስተዳደር ክፍሎች የጉዳዩን አሳሳቢነት አጢነው ከጎኑ በመቆም እገዛ እንዲያደርጉለት በተደጋጋሚ የጠየቀው ሰበካ ጉባኤው፣ በቅድሚያ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመቀጠልም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ላቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹ወደፊት ጉዳዩን አጣርተን መፍትሔ እንሰጣለን›› ከሚል በስተቀር በተጨባጭ ርምጃ የተደገፈ ምላሽ ባለማግኘቱ በማኅበረ ካህናት እና በማኅበረ ምእመናን ምልዓተ ጉባኤ የተሰጠው ሓላፊነት ሥልጣን በሌላቸው አማሳኞቹ ታጣቂዎች ሊታገድ በቅቷል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የሰበካ ጉባኤውን መሰብሰባቸውን በማቆም ከአማሳኝ ሓላፊዎቻቸው ጋር መሥራትን የመረጡት የገዳሟ አስተዳዳሪ ጨርሶ ካገዱበት ከሰኔ ፳፪ ቀን ጀምሮ ጉዳዩ በሕግ አግባብ እንዲታይና ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ የሰበካ ጉባኤው አባላት ከፍትሕ እና ከጸጥታ አካላት ጋር እየተነጋገሩበት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡
ሰበካ ጉባኤው ከሕገ ወጥ ርምጃው አስቀድሞ፣ ጥቂት የአስተዳደር ሓላፊዎች የሚፈጥሩት ግጭት በሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በገዳሙ ጽ/ቤት ተገኝቶ በሰላማዊ መንገድ ሥራዎችን ለማከናወን እንዳልቻለ በአድራሻ ለሀገረ ስብከቱ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት፣ በግልባጭ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
* * *
የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ሰበካ ጉባኤ በግንቦት ወር መጨረሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረሰው ሪፖርት ዐበይት ነጥቦች፤
- በአዲሱ የሰበካ ጉባኤ በአባልነት የተመረጡ የማኅበረ ካህናት፣ የማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች የቤተ ክርስቲያኒቱን አደራ በታማኝነት እና በብቃት ለመወጣት በተለይ ቅዱስነታቸው ለቤተ ክርስቲያናችን የያዙትን ራእይ እና ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ላለፉት አራት ወራት ሙሉ ጊዜአችንን ሠውተን ገዳሚቱን በታላቅ መንፈሳዊ ትጋት ስናገለግል ቆይተናል፡፡
- ከገንዘብ ዝውውር እና ፍሰት እስከ ንብረት አጠባበቅ ድረስ የሚታዩ ከፍተኛ የአሠራር ድክመቶችና የአቅም ማነስ በገዳሚቱ ልዩ ልዩ የአስተዳደር ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከትሏል፡፡ ከልዩ ልዩ የገዳማችን ክፍሎች ጋር ከተደረጉ ውይይቶች እና ሪፖርቶች በተገኙ የመነሻ ግብዓቶች መሠረት፡- ለማኅበረ ካህናቱ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የአስተዳደር ክፍሎች እንዲኹም ለምእመናን ግልጽ የኾነና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፤ የገዳማችን ጽ/ቤት አሠራር ወቅቱን የዋጀ እንዲኾን ለማስቻል ቃለ ዐዋዲውን መሠረት ያደረገ፣ ከሌሎች ገዳማት ተሞክሮ በማየትና ከገዳማችን ተጨባጭ ኹኔታ ጋር የሚጣጣም÷ ለሰው ኃይል አስተዳደር፣ ለፋይናንስ፣ ለንብረት፣ ለግዢ መመሪያዎች እና የውስጥ ደንቦች ረቂቅ ቀርበዋል፡፡
- የሰነዶቹን ረቂቅ በማባዛት በመደበኛ የማኅበረ ካህናት እና የሠራተኞች ስብሰባ ላይ ከመቅረቡ በፊት ለአስተያየት እና ለግምገማ ለመጽሐፍ መምህሩ አባ ገብረ መድኅን እና ለገዳሟ የቅኔ መምህር አባ ሙሴ ተሰጥቷል፡፡ የፋይናንስ፣ የንብረት፣ የግዢ እና የሰው ኃይል መመሪያ ለአስተዳደር ክፍሎች በጽ/ቤቱ በኩል እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ በቅድሚያ የፋይናንስ፣ የግዢ እና የንብረት መመሪያዎች ላይ መደበኛ ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ሥራ የሚገባበት ኹኔታ እንዲመቻች ውሳኔ ተላልፎ ለአፈጻጸሙ ጽ/ቤቱ ሓላፊነት እንዲወስድ ተደርጓል፡፡
- ለየዕለት ገንዘብ አሰባሰብ ሥርዐቱ በኮምፒዩተር የታገዘ አሠራር ለመከተል እንዲቻል ከማኅበረ ካህናት በሞያቸው ብቁ የኾኑት ለአንድ ወር በጊዜያዊነት ተመድበው የታቀደውን እንደተገብሩ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ በንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቅ ሲካሔድ በነበረው አሠራር እና በአዲሱ ሰበካ የተጀመረው የጨረታ ሽያጭ መካከል የሚታየው እጅግ የተጋነነ የገቢ ልዩነት ቀድሞ የነበረውን አሠራር ከግምት እና ከጥያቄ ውስጥ የከተተ በመኾኑ የጨረታ አሠራሩ እንዲቀጥልና ንኡስ መመሪያ የማውጣት አስፈላጊነትም ታምኖበታል፡፡
- ሒሳብ ክፍሉ በተደጋጋሚ የተጠየቀውን መደበኛ የሒሳብ ሪፖርት ያለማቅረብ ችግር ከታየ በኋላ የሦስት ዓመት ማስተር በጀት ተጠንቶ እንዲቀርብ፤ በቅዱስነታቸው ታዝዞ የነበረው የኦዲት ክንውን ሥራ አንዳንድ ቅድመ ዝግቶች ስለተከናወኑ ኦዲቱ በአፋጣኝ እንዲጀመር ተወሰነ፡፡
- ብልሹ አሠራርን ለማስተካከል፣ የጎበጠውን ለማቃናት እና በአስተዳደር ዙሪያ ለቁጥጥር እና ለመልካም አስተዳደር በሚያመች ኹኔታ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለመተግበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ፈተናዎች እንደሚከሠቱ ሰበካው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይኹን እንጂ የተጀመረው የገዳማችን የመልካም አስተዳደር አደረጃጀት ጅማሬ ከፍጻሜ ለማድረስ እንድንችል የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የአስተዳደር ክፍሎች የጉዳዩን አሳሳቢነት አጢነው ከጎናችን በመቆም እገዛ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን፡፡