(ኢ.ኤም.ኤፍ) የታሰሩ ጋዜጠኞች እየተፈቱ ባለበት በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኛ ሃብታሙ ምናለን፤ እኩለ ለሊት ላይ የኢህአዴግ ደህንነቶች ከመኖሪያ ቤቱ አፍነው ወስደውታል። አገር ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ እንደዘገበው ከሆነ፤ የቀዳሚ-ገፅ ስራ አስኪያጅ ሀብታሙ ምናለ ከመኖሪያ ቤቱ የተወሰደው፤ እኩለ ሌሊት ላይ ማንነታቸው በውል ባልታወቁ የ’ደህንነት መስሪያ ቤት’ ባልደረቦች ነው። አሁን ወዳልታወቀ ስፍራ የተወሰደው ሀብታሙ፤ ከዚህ በፊትም ለአንድ ሙሉ ቀን ጥብቅ-ምርመራ ሲደረግበት ውሎ አሻራ ሰጥቶ መውጣቱ ይታወቃል።” ብሏል።ጋዜጠኛ ሃብታሙ ምናለ፤ የርዕዮት አለሙን መፈታት ሰምቶ እና አይቶ፤ በዚህም ደስ ተሰኝቶ ነበር የዋለው። “እንኳን ተፈታሽልን! ርዕዮት አለሙ” የሚል አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ለሊቱን ደህንነቶች ቤቱ ገብተው አፍነው ወስደውታል።
ጋዜጠኛ ሃብታሙ ምናለ፤ የርዕዮት አለሙ እጮኛ ለሆነው ስለሺ ሃጎስም እንዲህ ብሎ ጽፎለት ነበር። ‹‹ስለሺ ትላንት ቀትር ላይ እቤትህ ልንጠይቅህ ስንመጣ ስለ ርዕዮት ያልከውን ዛሬ ላስታውስህ። ‘የርዕዮትን ዓመት ከመቁጠር ወደ ወር መቁጠር ተሸጋገርን፡፡ ልደቷ ሊከበር 11 ወር ቀራት። ይሄንስ ማን አየው! ተመስገን!››› ብለኸን ነበር፡፡
ለካ ከልብ ስለ አንድ ነገር መመኘት ጥሩ ነገር ያሰማል፡፡ ይሄው መልካም ዜና መጣ ይሄ መንግሥት ‹‹አስራ አንደኛው ሰዓት እንጂ አስራ አንደኛው ወር አይገደኝም›› ያለ ይመስላል፡፡ ፈታ ሊያረገን እኛን ከእስር ፈታት፡፡ ከትላንቱ ጨዋታ አንዱን ልድገምህ “አሁን እኮ ርዕዮት ባቡር የሚባለውን ሰምታም፣ አይታም አታውቅም፡፡ ስትወጣ ግራ ነው የሚገባት” ያልከው እውነት ልብ ይነካል፡፡ ለካ ሰዎቹ የጠሉትን ለመቅጣት ሲሉ ‹‹ልማታቸውንም›› ለማሳየት ላይ ንፉግ ናቸው!፡፡ 11 ወርን ስትጠብቅ የነበርከው ስለሺ ይሄው አሁን ከጎንህ መሆኗን ሳውቅ ደስ ብሎኛል፡፡