15 JULY 2015
ተጻፈ በ 

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የተረከቡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ በወቅቱ ከአልጄዚራ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹አስመራም ድረስ በመሄድ ዕርቅ

ለማድረግ ዝግጁ ነኝ›› ብለው ነበር፡፡ ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ሊገደድ ይችላል፤›› ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡ አሁንም በቅርቡ በፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት አሁን በያዘው ፖሊሲ የሚቀጥልና ኢትዮጵያን ማተራመሱን የሚቀጥል ከሆነ፣ ተገደን ዕርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤›› ማለታቸው እያነጋገረ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በአስመራ ላይ ይዞት ከቆየው አቋም ይለያል ወይ? ኤርትራ ውስጥ አዲስ ሥጋትስ አለ ወይ?›› የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘውን አቋም የሚያጠናክር እንጂ አዲስ ነገር አይደለም የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይበዛሉ፡፡

ከድንበር ወደ ሽብር

አንድነት በአንድ ወገን ፍላጎት ሊመጣ አልቻለም፡፡ ከብዙ ደም መፋሰስ በኋላ ፍቺው ዕውን ሆነ፡፡ ይኼኛው ያስገኘው ሰላም ግን የአሥር ዓመት ዕድሜም አልነበረውም፡፡ በድንበር አስታኮ ደም መፋሰሱ ተደገመ፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቀጠፈ፡፡

አሁንም ድረስ ያልተጠናቀቀውን ጦርነት አስመራና አዲስ አበባ ላይ የከተሙት ሁለቱ ድርጅቶች በይዋል ይደር ያቆዩትና ሳይፈነዳ እንደማይቀር አድርገው የሚገነዘቡት ተንታኞች አልጠፉም፡፡ በጦርነት የታመሰውን ይኼው በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ትኩረት ያለውን ቀጣና በበላይነት የመቆጣጠር አባዜ ተጋብቶባቸው ነበር የሚል መነሻ አላቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ የሚቀረው አልቀረም፡፡ ዕርቅ እንዲወርድ የተሞከረው ጥረትም አልተሳካም፡፡ ዛሬም ሥጋቱ እንዳለ ነው፡፡

የማታ ማታ ከአጀማመሩ በተቃራኒ በድንበሩ ጦርነቱ ምክንያት የኃይል ሚዛኑን ያጣው የአስመራ መንግሥት በጉልበት ተሸንፎ ፊቱን ወደ ዕርቅ እንዲያዞር ሆነ፡፡ በፈጥነትም የአልጄርስ ስምምነትም ተፈረመ፡፡ ለጊዜው ጦርነቱ ረገብ ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰላም አስከባሪ ኃይል በሁለቱ አገሮች መካከል ሰፍሮ፣ ሁለቱ ወገኖች ይግባኝ የሌለውን ፍርድ ሲጠባበቁ ከረሙ፡፡

የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ግን ጦርነቱን ለማብቃት ሞራል የነበረው አይመስልም፡፡ አንዳንዶቹ እንደሚሉት ከቀረበው መረጃና ማስረጃ በተቃራኒው ፍርደ ገምድል የሆነ ውሳኔ ሰጥቶ፣ ጦርነቱን የማራዘም ሚና ተጫውቶ ነበር የተበተነው፡፡ ከባድ ጦርነት ባይነሳም ጧትና ማታ የጦር ነጋሪት ሲጎሰም ይስተዋላል፡፡ አስመራ ፍርደ ገምድል ውሳኔውን ይዞ ተንቀሳቀሰ፡፡ አልተሳካለትም፡፡ በአካባቢው ተሰሚነት እያገኙ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያቀረቡት አማራጭ የሰላም ሐሳብ ከሕጋዊ ውሳኔ ይበልጥ በዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡ ተቀባይነት አገኘ፡፡ ይኼ ደግሞ ለአስመራ መንግሥት የሚሆን አይደለም፡፡ የሰላሙን ሐሳብ ባለመቀበሉ ይባስ ብሎ የአሜሪካን መንግሥት ጨምሮ ከኃያላን መንግሥታት ጋር አላተመው፡፡

በዲፕሎማሲ ቋንቋ ተበልጦ መንፈራገጥ ሆነ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ሕግ በአብዛኛው የሚገዛው በፖለቲካ ነው›› የሚለው የእውነታውያን (Realist) አስተሳሰብ በዚህ ቀጣና ተግባራዊ ሆነ፡፡ ፍርደ ገምድሉ ውሳኔ የአስመራ መንግሥት ከኃያላንም ከደካሞችም ነጠለው፡፡ እንደ ተንታኞች እምነት የመጨረሻ አማራጭ ለመውሰድም ተገደደ፡፡ ከሽብርተኞች ጋር መውዳጀት፡፡

መንግሥትን የሚቃወሙ የኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች መደገፍና ጥፋት መፈጸም ቀጠለበት፡፡ ፊቱን አዙሮም በደቡብ ምሥራቅ በኩል መጣ፡፡ ከዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው ተብሎ ከሚታመነውና በአሜሪካ በሚፈልጉት  ‹‹ኢስላሚስቶች›› የሚመራውን አልሸባብ መደገፍ ጀመረ፡፡  ከደጋፊዎቹ የዓረብ አገሮች በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የነበሩት አገሮች ወታደራዊና የፋይናንስ ድጋፍ ድልድይ መሆኑ በተለያዩ የተመድ መርማሪ ቡድኖች ተረጋገጠ፡፡ ደካማውን የሞቃዲሾ መንግሥት የምትደግፈው ኢትዮጵያ፣ ወደ አካባቢው በመግባት ዕርምጃ ለመውሰድ ተገደደች፡፡

የቀጣናውን የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ ውስብስብነት የሚያጠኑ እንደ ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ የመሳሰሉ ምሁራን ጦርነቱ፣ ‹‹የውክልና ጦርነት›› [Proxy War] እንደሆነ ተንትነው ነበር፡፡

ጦርነቱም በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ አልሸባብ ጨርሶ ባይሞትም ኢስላማዊ ኅብረት ለመበታተን በቃ፡፡ የኤርትራ መንግሥት በወቅቱ ያጣው ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በአካባቢው ለተፈጠረው ትርምስ ተጠያቂነትን ወሰደ፡፡ ሶማሊያና አካባቢውን በማተራመስ ተወንጅሎ እ.ኤ.አ. በ2009 በተመድ የተለሳለሰም ቢሆን፣ ማዕቀብ ተጣለበት፡፡ የአስመራ መንግሥት ከሁለት ያጣ ሆነ፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳሉት፣ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ሳይተነኩስ መኖር አይችልም፡፡ ትንኮሳው ከመደጋገሙ ውጪ ግን ‹‹የተወሰነልኝን መሬት ለማስመለስ›› በማለት ወደ ሙሉ ጦርነት አልገባም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ብቻ ሳይሆን፣ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ከውስጥ ሊመነጭ የሚችል የለውጥ ፍላጎት ለመጫንና ሌላ የተሻለ አማራጭ ያገኘ አይመስልም፡፡

ኢትዮጵያን በመተናኮል የኤርትራ ነፃነት ጠባቂነት ካርድ ይዞ ከመቆየት ውጪ፣ ሰበብ አይገኝም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለማወክ ‹‹አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ›› የሚል የሽብር ፕሮግራም ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሮ እንደነበርና እንደከሸፈበት ይታወሳል፡፡ ከኤርትራ በሚዋሰነው የትግራይ ድንበር አካባቢ በየጊዜው ትንኮሳዎችን ማካሄድ ቀጥሎበት ነበር፡፡ ዛሬም እየተነኮሰ ነው፡፡

ዛሬ አዲስ ትርክት?

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነት ከሶማሊያ ጦርነት በኋላ፣ በብዙ መልኩ ሰላምም ጦርነትም አልባ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ሆኖም ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአስመራ ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኘውን ማይዓይኒ የተባለውን ካምፕ ማጥቃቱ ሲያነጋግር ነበር፡፡ ይህም የኤርትራ መንግሥት በወቅቱ ላደረገው በግልጽ ያልተዘገበ የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴ ምላሽ እንደሆነ ነበር የተገለጸው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ጉዳዩ ወደ ሙሉ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት አጥልቶ ነበር፡፡ ያ አልሆነም፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት የግንቦት ሰባት የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ተደርጎ የሚታየው ኢሳት ሰሞኑን አስተላለፈው የተባለው ግን፣ በኤርትራ የሚገኙ አማፂ ቡድኖች በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ነው፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት 30 ታጣቂ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በፌዴራል ፖሊስ መደምሰሳቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ ይህ እየሆነ ያለው በኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ ነገሮች ሊከናወኑ ዋዜማ ላይ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙ ቀልብ የሳበው፡፡

በአንድ በኩል አምስት ሺሕ እንግዶች የሚተፉበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በማብራሪያቸው እንዳሉት፣ የኤርትራ መንግሥት በውስጥ ያለበትን ጫና መቋቋም አቅቶት ኢትዮጵያን እንደ መተንፈሻ እየተጠቀመባት መቀጠሉ አያቆምም፡፡ የፖሊሲ ለውጥም አይመጣም፡፡ ‹‹ይህ ለኤርትራ መንግሥት የሞት ሽረት የሆነ ጉዳይና የመኖርያ አጀንዳው ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ትንኮሳ የፈጸመው ተመድ በኤርትራ መንግሥት ይፈጸማል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ባወጣበት ማግሥት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እንዳሉት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ዜጎችን ለመታደግ ዕርምጃ ይወስዳል የሚል ተስፋ ያለው ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጋር እያያያዙት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት አስመራ ድረስ በመሄድ የመንግሥት ለውጥ ታደርጋለች የሚል እምነት ያላቸው ግን ጥቂቶች ይመስላሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የአሁኑ ንግግር ከዚሁ ቀደም ጠንከር ያለና የተለየ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ምርምር በማድረግ የሚታወቀውና በአሁኑ ወቅት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆነው ወጣት ጎይቶም ገብረልዑል ግን፣ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ንግግር ምንም አዲስ ነገር አያሳይም፡፡ የቆየና ተመጣጣኝ ምላሽ የሚለውን የበለጠ የሚያጠናክር ነው፤›› ብሏል፡፡ ለኤርትራ መንግሥት በተደጋጋሚ አማፂ ቡድኖችን የማስረግ የቆየ ልማድ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያም የአስመራ መንግሥትን የመንቀል ፍላጎት የላትም፡፡ ምክንያቱም አንድና ቀላል ነው፡፡ አስመራ ውስጥ የሥልጣን ክፍተት ይፈጠራል፤›› ብሏል፡፡ ይህንን ክፍተት የሚሞላ የተዘጋጀ የኤርትራ ድርጅት አለመኖሩን በምክንያትነት በማቅረብ፡፡ ‹‹አጠቃላይ ጦርነት መቼም ቢሆን የኢትዮጵያ አማራጭ አይሆንም፡፡ የኤርትራ መንግሥት በግልጽ ራሱ ካልጀመረ በስተቀር፤›› በማለት ምክንያቱን አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ አይነቴ ተመሳሳይ እምነት አላቸው፡፡ ‹‹ንግግሩ የፖሊሲ ለውጥ አያሳይም፡፡ በተሟላ ቁመና ዕርምጃ ለመውሰድና የአፀፋ ምላሹን ጠንከር ያለ እንዲሆን ማድረግ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አበበ እንደሚሉት፣ ዕርምጃው የአስመራን መንግሥት እስከ መገልበጥ ይሄዳል ለማለት አጠራጣሪ ነው፡፡ ‹‹በራሱ ግፊት ካልመጣ ቁስሉን እያስታመሙ መኖር ይመረጣል፡፡ በራሱ ጊዜ የሚሞት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አማካይነት ከፈረሰ ግን ሌላ መንግሥት አልባ ጎረቤት መፍጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኤርትራ ውስጥ አሉ ስለሚባሉት የኢትዮጵያ አማፂ ቡድኖች አቅም በተመለከተ አስተያየት የሰጡ አቶ አበበ፣ ‹‹የእነሱ አቅም የሚወሰደው በሻዕቢያ አቅም ነው፡፡ ነፍስ ያላቸው አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱም የፖለቲካ ተንታኞች በኤርትራ መንግሥት ላይ ተመሳሳይ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ በእነሱ እምነት ኤርትራ ውስጥ ያለው መንግሥት የተመናመነ ነው፡፡ በእሱ የሚደገፉ አማፂ ቡድኖችም የተመናመኑ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የደኅንነት ሥጋት የሚሆን ኃይል ኤርትራ ውስጥ አይኖርም የሚል ይመስላል፡፡ የሚታይ ሥጋት በሌለበት ጦርነት መክፈት ደግሞ አዋጪ አይሆንም የሚል ነው፡፡

አቶ ቶማስ ሰለሞን የተባሉ በአስማሪኖ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ድረ ገጽ ላይ የጻፉት “The Possible war between PFDJ and Ethiopia” የሚለው ደግሞ፣ ‹‹ህግደፍ [ሻዕቢያ] ወደ ሙሉ ጦርነት አይገባም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ሆኖም ለሁሉም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ይሉና በውጭ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት የኤርትራ ተቃዋሚዎች በጋራ ይህ እንዳይሆን የመከላከል ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ከሰው ውጪ አገር አይኖረንም፡፡ በሻዕቢያ ዕብደት አንድም ሰው መሞት የለበትም፡፡ የሚገባበት ከሆነ በራሱ እንዲወጣው ማድረግ ነው፡፡ ሕዝባችን ከደሙ ንፁህ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ኤርትራውያን የሚታወጀውን የጦርነት ጥሪ እንዳይቀበሉ በመምከር፡፡

‹‹እነ ግንቦት ሰባትና ደምሒትም በራሳቸው ይወጡት›› ይላሉ፡፡ በትምክህትና በፉከራ ሕዝባቸው ተታሎ የዚህ ጦርነት አካል እንዳይሆን ማስተማር እንዳለባቸውም ጽፈዋል፡፡

አንዳንዶች በኢትዮጵያ ላይ ካላቸው ጥርጣሬ በመነሳት ላይገባቸው እንደሚችል በመገመት፣ እንዲያው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን፣ ጠመንጃ የታጠቁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ሕዝባችንን ለባርነት በዳረጉ ወንጀለኞች ላይ እንዲያነጣጥሩም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

ጥሪው የሁሉም ተቃዋሚ ኤርትራውያን አቋም ስለመሆኑ መናገር ባይቻልም፣ በውጭ የሚገኙ የኤርትራ ተቃዋሚ ቡድኖች ጨቋኝ የሚሉት የአስመራ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲወገድ ፍላጎት ያላቸው ግን አይመስልም፡፡

ሰሚ ያጡ ጩኸቶች

የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ ያገኘው ድል ለአንዴና ለመጨረሻ አልሆነም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ብሎ የሰየመው ግንቦት ሰባትን ጨምሮ፣ የአርበኞች ግንባር የተባለው ቡድንና ደምሒት [ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ነፃነት ትግራይ] የመሳሰሉ ቡድኖች በማስታጠቅና ወደ ኢትዮጵያ በማስረግ አንዳንድ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡

በተመድ የተጣለው ማዕቀብም አልገታውም፡፡ የተጠበቀው የባህርይ ለውጥም አልመጣም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀደም ሲል በፓርላማ ባደረጉት ንግግር ‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ እየወሰዱ መቆየት› የሚለውን መርህ መንግሥታቸው እንደሚከተል፣ ወደ አጠቃላይ ጦርነት (All out War) ከተገባ ግን ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት እንደማይኖር አድርጎ ለመጨረስ የሚል ዕቅድ አስምረውበት ነበር፡፡ በእርግጥ በአገር ውስጥ በሚያደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድጋፍ እያጣ ያለውን የኤርትራ መንግሥት ጭንቅ ውስጥ የከተተ ንግግር ቢሆንም፣ በዚህ መሀል ግን አንዳንድ ምሁራንና በተለይ የአሜሪካ ነባር ዲፕሎማቶች የኤርትራን መንግሥት ከገባበት ጭንቀት ለማውጣትና ገንቢ ሚና ይጫወት ዘንድ የመነጋገር በር እንዲከፈት የጠየቁ ነበሩ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በአሜሪካ መንግሥት ተሰሚት ያላቸውና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ሄርማን ኮኸን የተባሉ ዲፕሎማት፣ ኤርትራን መታደግ ተብሎ ሊተረጉም የሚችል [Bringing Eritrea in from the Cold] በማለት ባቀረቡት የሰላም ሐሳብ፤ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ኤርትራ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ፣ ከአስመራ መንግሥት ጋር ድርድር እንዲጀመርና የአስመራና የአሜሪካ ግንኙነትም እንዲሻሻል በሚል ያቀረቡት ሐሳብ ነበር፡፡ በኳታርና በሌሎች አገሮችም ውስጥ ለውስጥ የተሞከሩ የሰላም ሐሳቦች የነበሩ ሲሆን፣ የአምባሳደሩ ሐሳብ ግን ትንሽ አነጋግሮ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር ዴቪድ ሺንም መጠነኛ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ሐሳቡ ግን በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት ያገኘ አልነበረም፡፡ የዲፕሎማቱ አቀራረብም የተመቸ አልነበረም፡፡ በአስመራ መንግሥት ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ጥያቄ ላይ የጣለና እንዲነሳ በቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ መሆኑ የሰላም እልባት መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡

Leave a Reply