Wednesday, 15 July 2015 13:36
– ሰማያዊ ፓርቲ እስርና ግድያ እንዲቆም ጠየቀ
በግንቦት ወር 2007 በተካሄደው ምርጫ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በካፋ ዞን በግንቦ ወረዳበአድዮ ካካ ምርጫ ክልል በጎጀብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ምርጫ ታዛቢ/ወኪል ሆነው የሠሩት አቶ አሥራት ኃይሌ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሲያስታውቅ ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ እየተወሰደ ያለው እስርና ግድያ እንዲቆም ጠይቋል።
በአቶ አሥራት ላይ ድብደባው የተፈጸመው ሰኔ 27 ቀን 2007 ጎረቤቶቻቸውና ቤተሰባቸው ወደ ገበያ ሄደው ሳለ ቦንጋ ከተማ 01 ቀበሌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ከረፋዱ በ4፡00 ሰዓት ላይ ወደ ቤታቸው በመጡና ለጊዜው ማንነታቸው በትክክል ተለይቶ ባልታወቁ ሰዎች ጭንቅላታቸውን ተመትተው ራሳቸውን እንዲስቱ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ የሰውነት አካሎቻቸው ላይ በተጸመባቸው ዘግናኝ ድብደባ መሆኑን የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ክፍል በላከው ማብራሪያ ገልጿል። ሟች ሕይወታቸው ያለፈው ወደ ጅማ ሆስፕታል ተውስደው በመታከም ላይ እያሉ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም ሰኞ ማታ መሆኑም ታውቋል።
የሟች አስከሬን ሰኔ 30 ቀን ወደ መኖሪያቸው ቦንጋ ከተማ የተመለሰ ሲሆን የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው እንዳይፈጸም በአካባቢው ባለሥልጣናት በአካባቢው ባለሥልጣናት ተከልክሎ ከቆየ በኋላ በሕዝቡ አቤቱታ ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ ም ሊፈጸም መቻሉን መድረክ አስታውቋል።
በካፋ ዞን የኢማዴ-ደህአፓ/መድረክ ተወካይ የሆኑት አቶ አዲማሱ አምቦና ሌሎች የዞኑ የመድረክ አመራር አባላት ሁኔታውን ተከታትለው መረጃ እንዳያስተላልፉ በቢሮ ውስጥ እያሉ ከቢሮአቸው እንዳይወጡ ቢሮው በወታደርና በታጣቂዎች ተከቦ ቆይቷል። ስለሟቹ ማንነትና ስለግድያው ሁኔታ የማጣራት ሥራ ለማከናወን የተቻለውም የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈጽሞ በመድረክ ጽ/ቤት ላይ ተደርጎ የነበረው ከበባ ሲያቆም ነው።
አቶ አሥራት ኃይሌ የ35 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳ፣ ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅአባት የነበሩ ሲሆን አቅመ ደካማ እናታቸውንም ሲጦሩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
ቀደም ስልም በኦሮሚያ ክልል በሁለት አባላት፣ በትግራይ ክልል በአንድ አባል እና በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በአንድ አባል ላይ ተመሳሳይ ግድያዎች መፈጸማቸው መድረክ አስታውሷል።
በተያያዘ ዜና ሰማያዊ ፓርቲ ትላንት በሰጠው መግለጫ ከ2007 ሀገራዊ ምርጫ ማግስት በገዥው አካል እየተወሰደ የሚገኘው ግድያ፣ እስር፣ ከስራ ማፈናቀል፣ ማሸማቀቅና ድብደባ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥያቄ አቅርቧል።
ፓርቲው ትላንት ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም “የወለደውን የረሳ ብሶት የወለደው ስርዓት! የዘመቻ እስርና ግድያ ተጠናክሮ ቀጥሏል!” በሚል በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው፣ ምርጫው ከተጠናቀቀበት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ማግስት በምርጫው በንቃት ይሳተፉ የነበሩና በአስተሳሰባቸው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች በማንአለብኝነት መደብደብ፣ ከሰራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና መግደል የአገዛዙ ዋና መገለጫ ሆኗል ብሏል።
ሰማያዊ በመግለጫው “በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማዊ፣ የመኢአድ፣ የቀድሞው አንድነት፣ የመድረክና የሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በተለዬ ኢላማ ተጠምደው እየተሳደዱ፣ እየተደበደቡና በጅምላ እየታሰሩ አለፍ ሲልም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ይገኛሉ” ሲል ገልጿል።
አሁን በገዥው አካል እየተወሰደ ያለው ድርጊት ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን የሚለውን አስተሳሰባቸውን የሚያጨልምና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞችን አንገት የሚያስደፋ ይዋል ይደር እንጅ መዘዙም ለማንም ወገን በተለይም ለገዥው መደብ የማይጠቅም መሆኑንም ፓርቲው በመግለጫው አስገንዝቧል።
“የአፈናው ስርዓት ብዙ ዓይነት አስተሳሰብና ልዩነት ባለባት ኢትዮጵያ ምርጫን መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ ቢልም ሃቁ ግን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግብዓተ መሬት እየተቃረበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ይህንን እውነታ ገዥው ቡድንም የማይክደው መሆኑን በምርጫው ማግስት ጀምሮ የተዘፈቀበት ህዝብን እንደጦር የመፍራት አባዜው ገሃድ አድርጎታል” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።
ሰማያዊ ፓርቲ ገዥው አካል ከሚፈፅማቸው ህገወጥና የማን አለብኝነት ተግባሩ እንዲቆጠብ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ደጋግሞ መጠየቁን አስታውሶ፣ አሁንም ይህ አይነቱ ህገ-ወጥና የማንአለብኝነት ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።