ከጠያቂዎቹ የሚበዙት ሙስሊም እህቶች እና እናቶች ናቸው። ይህ አልገረመኝም፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ እንዲሁ ስለሚያጋጥመኝ ይመስለኛል። ዛሬ ግን በጥሞና ስለነሱ አሰብኩ – ፅናታቸው ልዩ ነው – ፍፁም መታከት አይነበብባቸውም። አብዛኞቹ ገና የወራት እድሜ ያላቸውን ህፃናት ይዘዋል። የፈታሾቹ ግልምጫና ማመናጨቅ ችለው በፈገግታ ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ ~ ልዩ ናቸው።
ከሁሉ ልቤን የነካው ግን አንዳቸው ለአንዳቸው ያላቸውን መተሳሰብ ሳስተውል ነው! አንዷ አዘን ላለችው ታፀናታለች፤ ትመክራታለች፤ ትገስፃታለች፤ ግን አይተዋወቁም። – ያስተዋወቃቸው በደል ነው። የፍትህ እጦት ነው! በተለይ በአቅም የደከመችዋን ሻል ያለችው ኢድን ከሷ ቤት እንድታሳልፍ ስትጋብዛት ሳይ የሆነ ኩራት ነገር ተሰማኝ። ከሚያዋርዱን ጋር ሳይሆን የሰው ልክ ከሆኑ ሰዋች ጋር ኢትዮጵያዊ መባል እውነት ያኮራል። እንደዚህ ያሉ እንስቶች የሚያሳድጏቸው ልጆች በጨለመው ዛሬ፤ የነገ ብርሃን ናቸው!
እንዲህ እንዲህ ብዙ መንፈስ የሚያበረቱ መልካም ነገሮችን እየታዘብኩ የታሰሩት ሙስሊም ወንድሞች መንፈሰ ጠንካራነት ከፈጣሪ ቀጥሎ የነዚህ እህቶች እና እናቶች ሚና ገዝፎ ታየኝ . . .
እናንት የጥንካሬ ተምሳሌት ሴቶች ከልብ አከበርኩአችሁ! ፈጣሪ አብዝቶ ይባርካችሁ! አባቶቻችሁ ወንድሞቻችሁ ባሎቻችሁ ተፈተው ደስታ ይሁንላችሁ ~ ኢንሻ አላህ ዋጋችሁ ከንቱ አይቀርም!
ኢድ ሙባረክ!!!