እንጋባ ሲል ጠየቃት
አልተቀበለችውም አስማሩ ወንድምና እህትነቱ ይበልጣል አለችው
ተስማሙ
ቤቷ እየመጣ ይጠይቃታል
ቡና ታፈላለች ይጠጣሉ ካላት ታቀርባለች ይበላሉ
አውግተው ይለያያሉ
የትዳር ነገር ዳግም አልተነሳም
አሳምነው አንድ ቀን በጠረራ ፀሐይ መጣ
እንደመጣ የደረበውን ሹራብ አውልቆ አስቀመጠ ስለሙቀቱ ብዙ አውርተወ ተለያዩ
አስማሩ አሳምነው እረስቶት የሄደውን ሹራብ ልብሷን ስታጥብ አጠበችለት
ዳግም ሲመጣ ደርቦ ደራርቦ ነበርና የሚያወልቀው እንጂ የሚደርበው ልብስ አላስፈለገውም
ጃኬቱን አውልቆ ሄደ
አስማሩ እሱንም አጥባ አኖረችው
ሱሪውን ደርቦ መጣ ወበቀኝ አወለቀው
አስማሩ አጥባ አኖረችው
ካፖርቱን ጥሎ ሄደ
አጥባ አኖረችው
አንድ ቀን በጠራራ ፀሐይ ብርድ ልብሱን ለብሶ መጣ
አስማሩ ምነው አለችው
በጠራራ ፀሐይ ብርድ ሆዴ ገባ አላት
ምች ይሆናል አለችው የምች መድኃኒት ብታሽለት ተሻለው
ሲሻለው ብርድ ልብሱ አላስፈለገውም ጥሎት ሄደ
አስማሩ አጥባ አኖረችው
ትንሽ ቆይቶ ፍራሹን ተሸክሞ መጣ
ምነው አለችው
ላሳድሰው መሄዴ ነው አይቼሽ ልለፍ ብዬ ነው አላት
አመነችው
ጨዋታው ደራ ፍራሹን እረስቶት ሄዶ ኖሮ እኩለ ሌሊት ቢመጣ አስማሩ ቦታ ስላጣች ፍራሹን ፍራሿ ላይ ደርባው ደረሰ ያኔ ተነሽ ከማለት ጠጋ በይ ማለት ቀልሎ ተገኘ
ጠጋ አለች።
*********
ይህ የ አጭር አጭር ልብ ወለድ በኩርቢት መፅሐፍ ላይ የሰፈረ ነው የ አለማየሁ ገላጋይ ሶስተኛ መፅሐፍ በነገራችን ላይ አሌክስ ያልተዘመረለት ነው ለኔ..! ቅበላ አጥቢያ የብርሃን ፈለጎች ከድንቅ ስራወቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው አዲሱን መፅሐፉን(ወሪሳ)
ደግሞ በወርሃ ሀምሌ እንካችሁ ብሎናል።