የሃይል ሚዛኑ ያጋደለለት የሃይል ሚዛኑ ያላጋደለለት በፕሮፓጋንዳ የተወጠረው በአጉል የፖለቲካ ድቀት የሚዋዥቀው በጡዘት የሚሾረውን ጨምሮ በሰከረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የማናየው የማንሰማው ጉድ የለም::እኔ አውቅልሃለሁ ካለኔ ታጋይ ላሳር እኔ ካሌለሁ ኢትዮጵያ አበቃላት ወዘተ የሚለውን አካቶ ከተሳዳቢ እና ዘርጣጭ ጥሬ የፖለቲካ ከበሮ ማዜም የማይችለው ሁሉ ተነስቶ ባልዋለበት ኩበቱን ለመልቀም አጓጉል ይንከራተታል::ይህ ሁሉ እርግማን ነው::በራሳችን ችግር ተተብትበት ተይዘን እኛው እጅ መፍትሄው እያለ እኛው በኛው ራሳችንን የምንበላ የምሶሶ አብዮት አፍራሽ ለራሳችን ያልበጀን የማንታረም በሃገር ወዳድ ሽፋን የሃገር እና የሕዝብ በታኝ ሃይሎች ለራሳችን አሊያም ለሌላው ሻማ ሆነን በጋራ አብርተን በጋራ ቀልጠን ለመስዋትነት ያልተዘጋጀን የፖለቲካ ዲስኩራም ብኩኖች ነን::ከገባን !!!
ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጀምሮ እስከ ተመስገን ደሳለኝ ከአንዱአለም አራጌ ጀምሮ እስከ አንዳርጋቸው ጽጌ ከጦማርያኑ እስከ የሃይማኖት ኡስታዞቻችን ድረስ ለሕዝብ መብት እና ነጻነት ትርጉም ያለው ስራ ሲሰሩ እኛ ግን ራሳችን በራሳችን ተሥለን ለመተራረድ የምናቆበቁብ አንዱ ላንዱ የማይተኛ ከተሰዉልን ታጋዮችና እስር ቤት ከታጎሩብን ታላላቅ አስተማሪዎቻችን መማር ያቃተን የራሳችን ጠላቶች ሆነን በትግል ሽሚያ ውስጥ እየዋዥቅን የምንገኝና ልንነቃ ያልቻልን ነን::በዚህ ሂደት ውስጥ ላለማለፍ ስንል ስንቶቻችን ከሰከረው ፖለቲካ እና በጡዘት ከተሞላው የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደራቅን ምስክሮች ነን::በትንሽ ድል የምንወጣጠር በትንሽ ሽንፈት አንገታችንን የምንደፋ መማር ያቃተን በነፈሰበት የምንነፍስ በአንድ ሰሞን ወሬ ሆያሆዬ የምንል እንደ ቆርቆሮ የምንጮህ የንፋስ ፖለቲካ ውላጆች ነንእኛ::ለሃገር እና ለህዝብ የሚበጁ የዳበሩ ሃሳቦችን የይዙ አካላትን እና ግለሰቦችን በማግለል ራሴ ብቻ ልወስን በሚል አባዜ መጠናዎት ስንቱን ገደል ጨምረናል::በቀና የፖለቲካ ሂደት ትራክ ላይ ከመሮጥ ይልቅ በአሻጥርና የግለሰቦች ስም በማጥፋት ስንቱ ታይቷል ታልፏል::ከባለፈው ለምን እንደማንማር እና የመቻቻል እና የመተሳሰብ ባህል አዳብረን እንደማንጓዝ የማይገባን ወደ ገደል ሽምጥ ጋላቢ ሆነናል::
ከባለፈው መማር ከቻልን የመቻቻል እና የመተሳሰብ ቀናነት የተሞላው ሽፍጥ ያልተላበሰ ለአገር እና ለሕዝብ ነጻነት ለመታገል ለራሳችን ቃል ከገባን አንድነታችን የማይጠናከርበት አንዳችም ምክንያት የለም::ከሃሜት ፖለቲካ ከፖለቲካ ምቀኝነት እና ቅናት ወጥተን በጋራ ለትግሉ ስኬት በመመካከር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ አብዮት ካራመድን ለውጥ የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም::እኔ ብቻ አዋቂ ከኔ በላይ ታጋይ ለአሳር ከሚል አጉል መኮፈስ ራሳችንን አውጥተን ከሌላው ጋር በአንድነት መስራት ከቻልን ከትግል ሽሚያ ተላቀን ነገ ትዝብት ላይ ከሚጥለን ፕሮፓጋንዳ ወጥተን በጋራ መስራት ከቻልን ድል የማይገኝበት ምክንያት የለም::ከማግለል እና ከመፈረጅ ከማጣጣል እና ከመርመስመስ መንገኝነት የወረት ፖለቲካ መላቀቅ ግድ ይለናል:: ራሳችን ራሳችንን ልንመክር እና ልናርመው ልናሻሽለውና ልንተቸው ይገባል::ይህ ሁሉ እና ሌሎች የአንድነት እና የመቻቻል መንፈሶች በቀናንት ለአገር እና ለወገን ተደማምረው ለትግሉ ስኬት በአንድነት ለመቆም አሁንም ጊዜው አረፈደም::