የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲን (አንድነት) ለማስተዳደር በተረከቡ የተወሰኑ አመራሮች በንብረቶች ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ ተቃውሞ አስነሳ፡፡
ይህ ዝርፊያ ያሳሰባቸው የፓርቲው አባላት ጉዳዩን ለሕግ እንደሚያቀርቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ችግር መኖሩን አምነዋል፡፡
ቀደም ሲል አንድነት ፓርቲ በገጠመው ችግር ምክንያት የፓርቲው ደንብ ተጥሷል በማለት አመራሩን ተቃውመው ወጥተው በነበሩ ግለሰቦች አማካይነት ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የችግሩ ማጠንጠኛም ፕሬዚዳንት ሊሾም የሚችለው በጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት ብቻ ነው የሚለውን ደንብ በመሻር ብሔራዊ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር መርጧል መባሉ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ አማካይነትም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከሥልጣን ተነስተው፣ አቶ በላይ ፍቃዱ ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል ምርጫ ቦርድ ዕውቅና የሰጠው በአቶ ትዕግሥቱ አወሉ የሚመራው ቡድን ፓርቲውን ተረክቦ ማስተዳደር ጀምሯል፡፡ ሆኖም ግን፣ ‹‹አሁን የተፈጠረው እኛንም የሚያሳዝን ነገር ነው፤›› በማለት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ የፓርቲው አባላት አንድነት ፓርቲ ችግር ውስጥ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹ፓርቲውን የተረከብነው አመራሮች ወደዚህ ስንመጣ ቃል የገባነው ነገር ነበረ፡፡ ነገር ግን ቃላችንን አላከበርንም፡፡ አንድነትን መልሰን እንገነባለን፣ አንድ እናደርጋለን ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ወደ ዘረፋ ነው የገባው፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ማስፈጸሚያ ተብሎ የተለቀቀው ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ አለመዋሉ፣ አንድ ትልቅ የቪዲዮ ካሜራ፣ ዲጂታል ካሜራና አምስት ላፕቶፖች ተዘርፈው ተወስደዋል በማለት አባላቱ የገለጹ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም መጋዘን ተቀምጦ የነበረ በአቶ ግርማ ሞገስ የተጻፈ ‹‹ሰላማዊ ትግል 101›› ገቢው በደራሲው አማካይነት ለፓርቲው ማጠናከሪያነት እንዲውል የሰጡዋቸው 2,500 መጻሕፍት፣ ‹‹የሁለት ዓለም ሰዎች›› የተሰኘ ርዕስ ያላቸው በርካታ መጻሕፍት ተሸጠዋል ብለዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በድምሩ አምስት ሺሕ የሚደርሱ መሆናቸውን፣ የተሸጡት ደግሞ በፓርቲው አንድ የአመራር አባል ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ ንብረቶች በተጨማሪም አንድ አነስተኛ ጄኔሬተር፣ በርካታ ለስብሰባና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያገለግሉ ወንበሮችና በክልል የሚገኙ አባሎች ለስብሰባ ሲመጡ እንዲጠቀሙባቸው የተገዙ በርካታ ምንጣፎች መቼ እንኳን እንደተሰረቁ ሳይታወቅ ከቢሮ ጠፍተዋል በማለት አባላቱ ገልጸዋል፡፡ ተጨማሪ ማስረጃዎችን አሰባስበው ወደ ሕግ እንደሚሄዱም አስታውቀዋል፡፡
ዝርፊያውን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በበኩላቸው፣ ‹‹እኔ ሳላውቀው የወጣ ነገር እንዳለ አላውቅም፡፡ እኔ ልናገር የምችለው የጽሕፈት ቤቱን ኃላፊ ሪፖርት እንዲያደርግ ማዘዝ ነው፡፡ ይህንንም ነግሬዋለሁ፡፡ ስለዚህ ምላሹን እየጠበቅኩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሪፖርቱ የዘገየበትን ምክንያት በተመለከተ፣ ‹‹የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሪፖርት እንዲያደርግ ሁለት ሦስት ጊዜ ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ምልዓተ ጉባዔው ባለመሟላቱ ምክንያት አልተሳካም፤›› በማለት አክለዋል፡፡ ከዚህ በላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይችሉም ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው አመራሮች ወደ ሥልጣን ሲመጡ የገቡትን ቃል አላከበሩም ለሚለው ወቀሳ፣ ‹‹አንድነት እኮ ዛሬ አይደለም የተዳከመው፡፡ ዛሬ ጐልቶ የወጣ ቢመስልም ድክመቱ ተያይዞ የመጣ እንጂ፣ በአንድ ጊዜ የወረደ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በአመራሩ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት አንድነት የተነሳለትን ዓላማ እንዳያሳካ እንቅፋት እንደሆነበትም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ችግሩ የቆየና የከረመ ነው ቢሉም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በአባላቱ ውስጥ ልዩነት እንዳለ አምነዋል፡፡ ‹‹የአንድነት ችግር ምንድነው ተብሎ መታየት አለበት፡፡ አባላቱ በውዥንብርና በብዥታ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ያንን አስተካክለን ወደ እውነታው እስክንመጣ ድረስ መንገጫገጭና ችግሮች ይፈጠራሉ፤›› በማለት ፓርቲው ችግር ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቀጣይ አቅጣጫዎችንና መፍትሔዎችን በተመለከተ፣ ‹‹በዚህ ቀን መፍትሔ ይመጣል ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን በሒደት ጠርተው ችግሮች ይፈታሉ የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ስብሰባ የመጥራት ሐሳብ አለኝ፡፡ ነገር ግን ለስብሰባ የሚጠሩት ሰዎች መጀመርያ በጉዳዩ ላይ ማመን አለባቸው፡፡ በችግሩ ላይ ለመወያየት ፈቃደኝነታቸው መታወቅ አለበት፡፡ ያለንበት ሁኔታ ቀኑን የሚፈጥረው ስለሆነ በዚህ ቀን ማለት ግን አይቻልም፤›› ሲሉ አቶ ትዕግሥቱ የመፍትሔ አቅጣጫውን ገና እንዳላገኙት ተናግረዋል፡፡