ዜና መድረክ : ከ2007 ምርጫ ወዲህ በ5ኛ የመድረክ አባል ላይ ሰሞኑን ግዲያ ተፈጸመ፣ የኢህአዴግ አገዛዝ በመድረክ አባላት ላይ የሚፈጽማቸውን የተለያዩ ወከባዎች ቀጥሎበታል፡፡
I. የሰሞኑ ግዲያ፣
በሀገራችን በ2007 በተካሄደው ምርጫ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በካፋ ዞን በግንቦ ወረዳ በአድዮ ካካ ምርጫ ክልል በጎጀብ ምርጫ ጣቢያ የመድረክ ምርጫ ታዛቢ ወኪል ሆነው የሠሩት አቶ አሥራት ኃይሌ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ ም በተፈጸመባቸው አሰቃቂ ድብደባ ምክንያት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሎአል፡፡ በአቶ አሥራት ላይ ድብደባው የተፈጸመው በተጠቀሰው ዕለት ጎረቤቶቻቸውና ቤተሰባቸው ወደ ገበያ ሄደው ሳለ ቦንጋ ከተማ 01 ቀበሌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ከረፋዱ በ4፡00 ሰዓት ላይ ወደ ቤታቸው በመጡና ለጊዜው ማንነታቸው በትክክል ተለይቶ ባልታወቁ ሰዎች ጭንቅላታቸውን ተመትተው ራሳቸውን እንዲስቱ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ የሰውነት አካሎቻቸው ላይ በተጸመባቸው ዘግናኝ ድብደባ ሲሆን፣ ሕይወታቸው ያለፈው ግን ወደ ጅማ ሆስፕታል ተውስደው በመታከም ላይ እያሉ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ ም ሰኞ ማታ ነው፡፡
የቃለሕይወት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆኑት የአቶ አሥራት አስከሬናቸው ሰኔ 30 ቀን ወደ መኖሪያቸው ቦንጋ ከተማ የተመለሰ ሲሆን የቤተክርስያኑ አባላት ሲቀበሩ በቆዩበት የቀብር ቦታ የቀብር ሥነሥርዓታቸው እንዳይፈጸም በከተማው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ የሆኑት ቄስ መምህረ ታፈሰ መኩሪያና በግንቦ ወረዳ ባለሥልጣናትና ፖሊሶች ተከልክሎ ከቆየ በኋላ በሕዝቡ አቤቱታ ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ ም ሊፈጸም ችሎአል፡፡ የሟቹ አስከሬን ወደ ቦንጋ ከተማ ከተመለሰ በኋላ በካፋ ዞን የመድረክ ተወካይ የሆኑት አቶ አዲማሱ አምቦና ሌሎች የዞኑ የፓርቲው አመራር አባላት ሁኔታውን ተከታትለው መረጃ እንዳያስተላልፉ ከቢሮአቸው እንዳይወጡ ቢሮው በወታደርና በታጣቂዎች ተከቦ ቆይቷአል፡፡ ስለሟቹ ማንነትና ስለግዲያው ሁኔታ የማጣራት ሥራ ለማከናወን የተቻለውም የቀብር ሥነሥርዓቱ ተፈጽሞ በመድረክ ጽ/ቤት ላይ ተደርጎ የነበረው ከበባ ሲያቆም ነው፡፡
አቶ አሥራት ኃይሌ የ35 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳ፣ ባለትዳርና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበሩ ሲሆን አቅመደካማ እናታቸውንም ሲጦሩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሎአል፡፡
ቀደም ስልም በኦሮሚያ ክልል በሁለት አባላት፣ በትግራይ ክልል በአንድ አባል እና በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በአንድ አባል ላይ ተማሳሳይ ግዲያዎች መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡
II. የተለያዩ ወከባዎች፣
1. በካፋ ዞን፣
በፈለገሰላም ወረዳ በጨታ ምርጫ ክልል በቦባ ቀበሌ የመድረክ የምርጫ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ገረመው ቆዲ፣ የምርጫው ቀስቃሾች የነበሩት አቶ አሥራት ሻውአኖ፣ አቶ ገረመው ጋንአቾ እና የሾላይ ቀበሌ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ገዛሃኝ ገንቢ እንደዚሁም በዴቻ ወረዳ ጭሪ ምርጫ ክልል የሚታ ቀበሌ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ተክሌ ቆጭቶ ከሚያስፈሊጋቸውና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ማዳበሪያ እንዲገዙ በቀበሌው አመራሮች ታዘው ትዕዛዙን ለመፈጸም ባለመቻላቸው ተይዘው እንዲደበደቡና እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡
2. በቤንች ማጂ ዞን፣
ሸዋ ቤንች ወረዳ ደግሞ አቶ መኮንን ሚቱስ፣ አቶ ማሙር ሁሌት፣ አቶ ሉቃስ አለሙ፣ አቶ ቶሳ ሳቁያብ፣ አቶ ዘለቀ ታቹያብ፣ አቶ ሐሰን ዴሪያብ፣ አቶ ተስፋዬ ወ/የስ፣ አቶ ሳሙኤል ቸሪቲ፣ አቶ መላኩ ታርሳ፣ አቶ መንግስተ ሾዳ፣ አቶ ኬሪቲ ቡጢያብ፣ አቶ አድነው ወ/የስ እና አቶ አብርሃም ሳሙኤል የሚባሉ የመድረክ አባላት መስከረም ሲሲ በሚባል ቀበሌ ውስጥ ባለው ፖሊስ ጣቢያ ከአራት ቀን እስከ ሁለት ሳምንታት ያህል ጊዜ ታስረው ከቆዩ በኃላ ተለቀዋል፡፡ ባሎቻቸው እቤት ያልተገኙ 12 ምስቶችም ታስረው ከቆዩ በኃላ እንደተፈቱ ታውቋል፡፡ እንደዚሁም በዞኑ ውስጥ በሸኮ ልዩ ወረዳ የፉዥቃ ቀበሌ ነዋሪና የመድረክ የምርጫ ታዛቢ ወኪል የነበሩት አቶ ደርጀር ዲኩ እና አቶ ፀጋዬ ፉርጃ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ አባላቱ የታሰሩት ያለፍረድ ቤት ትዕዛዝ ሲሆን የማዳበሪያ ግዥ ጉዳይ እንደሽፋን ቢቀርብባቸውም በ2007 ምርጫ ወቅት ለመድረክ ቅስቀሳ አካሄዳችኋልና ከአሁን በኋላ የመድረክ አባልነታቸውን እንዲለቁ የሚል ጥያቄና ማሰፈራሪያም እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሎአል፡፡
3. በደቡብ ኦሞ ዞን፣
3.1. በማሊ ወረዳ ደግሞ አቶ ታገሰ ቡርዝጋ፣ አቶ ቦት ቦርታ እና አቶ ነጌ ደምቤ የሚባሉ የመድረክ አባላት ለመድረክ ቅስቀሳ አካሄዳችሁ ነበር በሚል ውንጀላ ታስረው ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በዚሁ ወረዳ የኩንታር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 26 አርሶ አደሮች የመድረክ ደጋፊና ቀስቃሾች ስለነበራችሁ የእርሻ መሬታችሁን ሊቀቁ በማለት በቀበሌው አመራር አባላት የእርሻ መሬታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ አቶ ሲሳሞ ሰንቆ፣ አቶ ባኮ ሲሳሞ፣ አቶ ባንኬ ዳርማሌ፣ አቶ ዳኤ ኤይዶ፣ አቶ ካማ አፋ፣ አቶ ጃማሉ፣ አቶ ቦንቃ ቦቴ፣ አቶ አጢሬ አዙሌ፣ አቶ አይዞ አፋ፣ አቶ ሻላ ሳባ፣ አቶ ተስፋዬ ዳቦ፣ አቶ ዳትፋቴ ዳርማሌ፣ አቶ ኤእኤ ቦርቻ፣ አቶ ሚና ሚሊሞ፣ አቶ ቢቅሌ ቲቻ፣ አቶ አዋሳ አጢሬ፣ አቶ አማኔ አለሙ፣ አቶ ባዜ ሲሳሞ፣ አቶ ጋልጋላ ዳሚቴ አቶ የሬቦ፣ አቶ ወሮሲ ኦሻንካ፣ አቶ ማላጬ ዳርማሌ፣ አቶ አጢሬ አጫና፣ አቶ ምሥራቅ ሂላዬ፣ አቶ ዳይንቴ ዳርማሌ እና አቶ ባልዶ ዎኮ የሚባሉት እነዚሁ አርሶ አደሮች ለተፈጸመባቸው ሕገወጥ ከመሬታቸው ማፈናቀል ለሚመለከታቸው አካላት ቢያመለክቱም እስከአሁን ምንም መፍትሔ አልተሰጣቸውም፡፡
3.2. በካምባ ወረዳ ደግሞ በመድረክ በኩል በምርጫው ወቅት የምርጫ ጣቢያ ወኪል ታዛቢዎች ሆነው የሠሩት አቶ ግዛ ግብሳ እና አቶ ገጦሬ ገባሌ የተባሉ የግብርና ኤክስተንሽን ሠራተኞች ከሚያዚያ ወር 2007 ጀምሮ ከሥራና ከደመወዛቸው የታገዱ ሲሆን አቶ ሕዝቃኤል ፋንጌ እና መምህር አቴ አይሳ የተባሉት የመድረክ የክልል ም/ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ደግሞ የየካቲት ወርና ከሚያዚያ ወር 2007 ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያለው ደመወዛቸው በሥራ ላይ እያሉ ታግዶ ይገኛል፡፡ በወረደው ውስጥ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ በርካታ የመድረክ አባላትና ደጋፊ የሆኑ አርሶ አደሮችም ከአቅማቸው በላይ እንዲገዙ የተመደበባቸውን ማዳበሪያ በወቅቱ አልገዙም በሚል ሰበብ እስከ 1000 ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እየተጣለባቸው እንዲከፍሉ በመገደድ ላይ ይገኛሉ፡፡
4. በኦሮሚያ ክልል፣
4.1. በጉጂ ዞን ዋመና ወረዳ አቶ ሮባ ገልቹ፣
4.2. በቦረና ዞን መልካ ሶዳ ወረዳ አቶ ጠደቻ አሬሮ፣
4.3. በምስረቅ ሻዋ ዞን ሞጆ ወረዳ አቶ ዝናቡ ዳምጤ የሚባሉ የመድረክ አባላት በየወረዳዎቻቸው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ታስረው ይገኛሉ፡፡
4.4. በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ደግሞ አቶ አሸናፊ ነጋሽ፣ አቶ ለሚ እንዳለማው፣ አቶ ባብሣ ገመዳ፣ አቶ ጉዳታ ቢራ፣ ወ/ሮ ወይንሸት፣ አቶ እሸቱ ዲማ፣ አቶ አንበሳ ያኢ፣ አቶ ታምሩ ቁምቢ፣ አቶ ቀነኒ ደሜ እና ወ/ሮ ደምበልቱ ዳሜ የተባሉ የመደረክ አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ አርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች በቀበሌው አመራሮች እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡
4.5. በምዕራብ ሸዋ ግንደበረት ወረዳ የመድረክ አደራጅና በምርጫው ወቅት የመድረክ ቀስቃሽና ተዘዋዋሪ ታዛቢ ወኪል የነበረው ተማሪ ጉቱ ሦሬም በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ያልተፈቀደ ስብሰባ አካሄደሃል በምል መሠረተብስ ክስ በጸጥታ ኃይሎች ተደብድቦ ታሥሮ ይገኛል፡፡