Wednesday, 22 July 2015 13:29

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ያደርጉታል በተባለው ጉብኝት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በሚያደርጉት ውይይት የኢሕአዴግን ከፍተኛ አመራሮች ለመከፋፈል ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ተባለ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ከፍተኛ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነትና የደህንነት ባለሙያ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፣ “አሜሪካኖች በራሳቸው መመዘኛ በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ለዘብተኛ እና አክራሪ ሃይሎች አሉ ብለው ያምናሉ። ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና የነፃ ገበያ ክለሳን እና የሲቪል ሶሳይቲ ሕግን በተመለከተ አሜሪካኖች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላቸውን ልዩነት ዊክሊክስ በድረገጾች አስነብበዋል። በተለይ የአምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ  ለአሜሪካ መንግስት በፃፉት ሚስጥራዊ ሰነድ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው በሁለቱ ሀገሮች መካከል የፖሊሲ ልዩነት እና ያልተረጋጋ የትብብር መንፈስ መኖሩን ያሳያል። ሆኖም ግን አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶን የተኩት አምባሳደር ቪክ ሁድልስቶን በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ከመሰረቱ በማስተካከልና ተገቢውን አቅጣጫ በማስቀመጥ በተለይ ዊክሊክስ ድረ ገጽ ላይ “Time to stop hating Ethiopia” በሚል አምባሳደሯ በሚስጥራዊ ሰነድ ያሰፈሩት ትንታኔ መሬት የወረደውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገላጭ ነበር።” ብለዋል።

አያይዘውም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞትን ተከትሎ ፕሬዝደንት ኦባማ በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ሽግግር ሳይደረግ ቀድመው በወቅቱ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አብረው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ለመግለጽ የቀደማቸው አልነበረም። አሜሪካኖቹ ይህን ያደረጉት በራሳቸው ትንታኔ በምዕራቡ ዓለም ያልተማረ አክራሪ ኃይል ስልጣን ሊቆጣጠር ይችላል ከሚል ፍራቻቸው የመነጨ ነበር። ስለዚህም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር የተጠቀሙበት መንገድ ነው። ገዢው ፓርቲ ግን በወቅቱ በራሱ የውስጥ አሰራር ኃ/ማሪያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መምረጥ ችሏል። አሜሪካኖቹ ግን በእነሱ ጫና የተደረገ ይመስላቸዋል።” ሲሉ የአሜሪካኖች እምነት የተሳሳተ መሆኑን አብራርተዋል።

“አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ኦባማ እንዴት መከፋፈል ለፈጥሩ ይችላሉ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ገዢው ፓርቲ በቀጣይ ጉባኤ ያደርጋል። በጉባኤውም ለቀጣዩ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ፓርቲውን የሚመራ ሊቀመንበር ይሰይማል። ይህን ተከትሎ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት በመቅረብ አዲስ መንግስት ይመሰርታል። ይህ ከመሆኑ በፊት ነው የኦባማ ጉብኝት በአሜሪካ መንግስት የታቀደው። የአሜሪካ መንግስት ይህን እቅድ መንደፍ የፈለገው በራሳቸው ትንታኔ ምዕራብ ሀገር የተማረ መሪ ከሌላው የተሻለ ዴሞክራት ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው። በምዕራብ ሀገሮች የተማሩ ወደ ፖለቲካ አመራርነት ሲመጡ የዴምክራሲ ዕሴቶችን በግልጽ እንዳይተገብሩ ሌሎች አክራሪ ኃይሎች በዙሪያቸው ስለሚቀመጡ ነው የሚል ትንታኔም ያስቀምጣሉ። በእነዚህ እና በሌሎች በራሳቸው ምክንያት አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ቢያንስ ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲቀጥሉ ጫና ለማሳረፍና ወገንተኛነታቸውን ለማሳየት ነው፣ የኦባማ አንዱ የጉብኝታቸው ዓላማ። ስለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የአሜሪካን ፍላጎት በጥንቃቄ ሊመለከቱት ሊመረምሩት ይገባል። በመካከላቸውም የአሜሪካን ድጋፍ ለማግኘት የተሳሳተ ሩጫ ውስጥ እንዳይገቡ መጠንቀቅ አለባቸው። ሁሉም ውሳኔ በፓርቲዎቹ ቀጣይ ጉባኤ ብቻ እንደሚወሰን ሁሉም ግንዛቤ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply