Wednesday, 22 July 2015 14:11

 በይርጋ አበበ

በ1954 እ.ኤ.አ አሜሪካን በፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት ዳዊት ኤዘንሀወር በወቅቱ ብቸኛ ከቅኝ ግዛት ቁጥጥር ነጻ የሆነችዋን አፍሪካዊት አገር መሪ ወደ አሜሪካ ይጋብዛሉ። የፕሬዝዳንቱን ግብዣ የተቀበሉት የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴም አሜሪካን የጎበኙ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ለመሆን በቁ። ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማለትም በ1963 ኦክቶበር 3 ቀን የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ኒውዮርክ ያቀኑት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እግረ መንገዳቸውን ታላቁን የአሜሪካ ቤተ መንግስት (በተለምዶ ነጩ ቤት) እየተባለ የሚጠራውን ቤተ መንግስት ጎበኙ። ያንን ቤተ መንግስት የጎበኘ አፍሪካዊይም ሆነ ከአፍሪካ ውጭ ያለ የጥቁር ህዝብ መሪ ባለመኖሩ ንጉስ ቀ/ኃይለስላሴን ባለታሪክ አደረጋቸው፡፡

ይህ ከሆነ ከ45 ዓመታት በኋላ ልዕለ ሀያሏን አገር አሜሪካን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ የሆነ መሪ ያስተዳድራት ዘንድ እድል ተፈጠረላት። የዘር ሀረጋቸው ከኬኒያ እንደሚመዘዝ የተነገረላቸው የመጀመሪያው ጥቁር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የነጩ ቤት አለቃ ሆነው ከተሾሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ እሳቸውም በተራቸው የአራት ኪሎን ቤተ መንግስት በመጎብኘት የመጀሪያው የአሜሪካ መሪ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የቀናት እድሜ ብቻ እንደቀራቸው ተነግሯል። ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ኋይት ሀውስን ከመጎብኘታቸው ዘጠኝ ዓመታት ቀደም ብሎ አሜሪካን የመጎብኘት እድል አግኝተው ነበር። በተመሳሳይ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም የኋይት ሀውስ አለቃ ከመሆናቸው በፊት ወይም ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው ዘጠኝ ዓመታት በፊት ገና የአሜሪካ ምክር ቤት አባል እያሉ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እድል አግኝተው ነበር።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ሆነ የባራክ ኦባማ የመጀመሪያ ዙር ጉብኝት ይህን ያህል ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም። በምትኩ ሁለቱ መሪዎች አንደኛው የሌላኛቸውን አገር ለመጎብኘት ለሁለተኛ ጊዜ የሚጎበኙትን አገር አፈር ሲረግጡ ግን ትልቅ ትኩረትን አግኝተዋል። ልዩነቱ ኦባማ ካለፈው ጊዜ ይልቅ አሁን እድሜ እና ስልጣን የጨመሩ መሆናቸው ሲሆን የኃይለሥላሴ ደግሞ በአሜሪካ የሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ እና ኃይለሥላሴም በወቅቱ ታሪካዊ ንግግር ያደረጉበት ዘመን መሆኑ ነው። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። አስተያየቶቹ ምን ይዘት አላቸው? ለሚለው እና ሌሎች ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡን በአገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን እና የገዥው ፓርቲ የስራ ኃላፊዎችን አነጋግረን ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 

የኦባማ ጉብኝት የትኩረት ማዕከል

ባለፉት ሁለት ዓመታት ታንዛኒያን፣ ደቡብ አፍሪካን እና ሴኔጋልን መጎብኘት የቻሉት የልዕለ ሀያሏ አገር መሪ የፊታችን ሀምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአባታቸው የትውልድ አገር የሆነችዋን ኬኒያንም የሚጎበኙ ሲሆን ይህም ማለት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ አገሮችን ይጎበኛሉ ማለት ነው። እነዚህን ሁለት ጎረቤት አገሮች በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመጎብኘት ምን አስገደዳቸው? የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ አስተያየት ሰጭዎች የዘርፉ ልሂቃን (የፖለቲካ ተንታኞች) የመሰላቸውን መልስ ለመስጠት ሞክረዋል። በእርግጥ ባራክ ኦባማም ቢሆኑ ከሊሂቃኑ ጋር የተመሳሰለ መልስ ሰጥተዋል።

የባራክ ኦባማ ጉብኝት ዋናው የትኩረት ማዕከል ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ የነበረውም በእሳቸውም አንደበት የገለጹት በሽብርተኝነት ዙሪያ ላይ የሚያተኩር መሆኑን ነው። ሁለቱ ጎረቤት አገሮች (ኬንያ እና ኢትዮጵያ) አልሻባብ በሚባለው የቀጠናው አሸባሪ ቡድን ጥርስ ውስጥ የገቡ አገሮች ሲሆኑ በተለይ ኬንያ በተደጋጋሚ ጊዜ የአልሻባብ ፈርጣማ ጡንቻዎች አርፈውባታል። በዚህ በኩል ግን ኢትዮጵያ የተሻለች ሳትሆን አትቀርም “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ አልሻባብን በመመከት በኩል ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት በድንበር አካባቢም ሆነ የአልሻባብ ቀጥተኛ ሰለባ በሆነችው ሶማሊያ ላይ በማስፈር የአሸባሪውን ቡድን ጥቃት በብቃት እየመለሰች ትገኛለች። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጉብኝት ዋና የትኩረት ማዕከል የሆነውም በዚሁ የአሸባሪ ቡድን ላይ ያጠነጠነ እንደሆነ ራሳቸው ተናግረዋል።

 

ኦባን ለማነጋገር የተዘጋጁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች

ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን ጠቅላላ ሁኔታ ከሁሉም ወገን መስማት አለባቸው ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ ከሰጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው እና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ናቸው። ኦባማን ማነጋገር ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት የፓርቲዎቹ አመራሮች፤ “ኦባማ አገሪቱን የሚጎበኙ ከሆነ ስለ ኢትዮጵያ ሊያውቁ የሚገባቸው በአንድ ወገን ብቻ ያለውን መረጃ ሳይሆን በተቃዋሚዎች በኩል ያለውንም ከተቃዋሚዎች ጋር በመነጋገር ሊያውቁ ይገባል ብለን እናምናለን። ገዥው ፓርቲ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ላይ በመጣል ብቸኛ ጠቅላይ ፓርቲ ሆኖ ይገኛል። ይህ አካሄድ በጣም የሚያሳስብ ስለሆነ አሜሪካ ደግሞ የዴሞክራሲ ስርዓትን አበረታታለሁ የምትል አገር ስለሆነች አሜሪካ እንደዚህ አይነት አምባገነን ስርዓት የሚገነባ መንግስትን ማበረታታት ሳይሆን ማስተካከል የሚቻለው በሁለቱም ወገን ያሉ ወገኖችን አነጋግሮ መፍትሔ መፈለግ ሲቻል ነው” ሲሉ የመድረኩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናግረዋል።

የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ከባራክ ኦባማ ጋር ለመነጋገር ሶስት ፓርቲዎች በጣምራ (ኢዴፓ፣ መኢአድ እና ኢራፓ) ደብዳቤ ማስገባታቸውን ይናገራሉ። “ለባራክ ኦባማ ልናቀርብ ያሰብናቸው ነጥቦች መንግስት ህገ መንግስቱን አላከበረም በሚለው ነጥብ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። በተለይም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተረጋገጡት ዓለም አቀፍ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አግባብ ባልሆነ መንገድ እየተጣሱ መሆናቸውን እናነሳለን። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም በዚህ ጉዳይ ላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ? ለኢትዮጵያ መንግስትስ ምን አስተያየት ይሰጣሉ? የሚለውን ሀሳብ እናቀርባለን” ብለዋል።

ባራክ ኦባማን ማነጋገራችሁ የኢትዮጵያ መንግስት ችግርች አሉበት የምትሉትን መቅረፍ ያስችላል ብላችሁ ታምናላችሁ? ተብለው የተጠየቁት የፓርቲዎቹ አመራሮች መልስ ሰጥተዋል። ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ “ለችግሮቹ (መንግስት አለበት ብለው የሚያምኗቸውን ችግሮች) መፍትሔ ለመስጠት በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርተን የሚመጣ ለውጥ ነው መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “የአሜሪካ መንግስት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ ያለን አገር (ኢትዮጵያን) በዲፕሎማሲያዊ አሰራር፣ በውጭ ጉዳይ እና አጠቃላይ በሰብአዊ መብት አከባበር ሂደት ላይ በሚኖሩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ላይ ምን አልባት ምክር አዘል አስተያየት ለኢትዮጵያ መንግስት መስጠት የሚችሉ ከሆነ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የተሻለ ምዕራፍ ሊይዝ ይችላል ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም እነሱ (አሜሪካውያን) የተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት ያላቸው እንደመሆናቸውና እንደዚህ አይነት አምባገነናዊ ስርዓትን የሚቃወሙ እንደመሆናቸው መጠን ቢያማክሩ የተሻለ ስርዓት ሊመጣ ይችላል ብለን ስለምንገምት ብቻ ነው” ብለዋል።

ዶክተር ጫኔ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያመኑበትንም ሲተነትኑ፤ “መፍትሔ ሊኖር የሚችለው ግን እኛው በራሳችን ህገ መንግስቱን ለማክበ በምናደርገው ጥረት ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ያፈጻጸም ችግርና የህግ ክፍተት መፍታት የምንችልበትን ሂደት በቀናነት ይህ መንግስት(ኢህአዴግ) ማመቻቸት የሚችል ከሆነ መፍትሔው በኢትዮጵያ ህዝብ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም በመንግስት እጅ ነው ብለን ነው የምናስበው። ከዚያ ውጭ ሊኖር የሚችል ተጽዕኖ ግን የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ጫና ከመፍጠር በዘለለ በአንድ ሉዓላዊት አገር ውስጥ ‘ይህንን አድርግ ያንን አታድርግ’ ብሎ ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚችልበት ነገር እንደሌለ ይታወቃል። ካለብን ተጽዕኖ ብሶትና ጫና አኳያ በአገራችን ያለውን ሁኔታ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለን ስለምናስብ ነው ይህንን ለማድረግ (ኦባማን አግኝተው ለማነጋገር) የተነሳነው” ሲሉ መልሰዋል።

አቶ ጥላሁን እንደሻውም ከዶክተር ጫኔ ጋር የሚቀራረብ መልስ ሰጥተዋል። አቶ ጥላሁን “የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ ያመጣል ብለን አናምንም። ነገር ግን አገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንዲያውቁት ነው። ባለፈው ጊዜ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊ ዊንዲ ሸርማን የኢህአዴግን ብቻ በመስማት የዴሞክራሲ ስርዓቱ የተስተካከለ መሆኑንና የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱም ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸው ነበር። ነገር ግን በአገሪቱ ያለው እውነታ ከዊንዲ ሸርማን አስተያየት በተለየ መልኩ ነው። እኛ አሁንም ባራክ ኦባማን በማግኘት መነጋገር የፈለግነው ስለ አገሪቱ ከሁለቱም ወገን ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ እንጅ ለችግራችን መፍትሔ እንዲሰጡን አይደለም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትስ የኦባማን ጉብኝት በምን መልኩ ይመለከተዋል?

 

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የባራክ ኦባማ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማዳበር እድል ሰለሚፈጥር ተደስተናል ሲሉ ይናገራሉ። በጉዳዩ ዙሪያ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ “ጉብኝታቸው በጣም ጠቃሚ እና ከፍተኛ ነው። እንደሚታወቀው ሁለቱ አገሮች (አሜሪካ እና ኢትዮጵያ) ከ100 ዓመታት በላይ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት አሳልፈዋል። የአሁኑ የባራክ ኦባማ ጉብኝትም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያና አሜሪካ በጸጥታ እና በሽብርተኝነት ጉዳዮች ላይ መረጃን በመለዋወጥ በትብብር ይሰራሉ” ያሉት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ አያይዘውም “በክልላችን (የአፍሪካ ቀንድ) ከአሸባሪዎች ጋር ፍልሚያ ስናካሂድ ቆይተናል። አሸባሪ ቡድኖቹ በክልላችን መስፋፋት ከጀመሩ ወዲህ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አብረን እንሰራለን። በአላፉት ዓመታት ከአሜሪካውያን ወዳጆቻችን ጋር በመሆን ከእነዚህ አሸባሪዎች ጋር ስንዋጋ የቆየነውና ስለዚህ በሁለቱ አገሮች መካከል ግንኙነቱና ትብብሩ ይጠናከራል” ብለዋል።

Leave a Reply