ESAT “Welkait Tegede Breaking News” debunked by the Welkaites

የወልቃይት ተወላጆች መሬታቸውን መነጠቃቸው ሳያንስ ትግላቸውም በሻዕቢያ መነገጃ መዋሉ አስቆጥቷቸዋል
July 22, 2015

አድነው ዋሚ

ጦሩ ገሰገሰ
ከተሰነይ ጉልች ገና ሳይነሳ
ከጎንደር ደረሰ።

ከሁለት ሳምነት በፊት ጀምሮ ህዝባዊ ሀይል በሚል የሚጠራውና መቀመጫቸው ኤርትራ የሆነው የግንቦት 7 ጦርና የአርበኞች ግንባር ጦር ውህደት ውጤት የተባለው ድንበር አቋርጦ ወደ ወልቃይት (ኤሳት ትግራይ ብሎ አጽድቆታል!) በመዝለቅ ቃፍቲያን አጥቅቶ በመገስገስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠገዴንም አቋርጦ ወደ አርማጨሆ መዝለቁን (እኔ ሳልሆን ኤሳት ነው ያለውና ከቃፍቲያ እስክ ሳንጃ ያለውን ርቀት የምታውቁ በእኔ ላይ ትዝብት አትጣሉ)ና አልፎም መተማን ማስጨነቁን እወቁት ተብለናል። እንደ ኤሳት ገለጻ ከሆነ ይህ ተዓምረኛ ጦር ይገሰግሳል እንጂ ነጻ አወጣሁት የሚለውን መሬት አይዝም፤ አይሰፍርበትም ። አዲስ ግኝት ነው በሽምቅ ውጊያ ወይስ ታንክና የመጓጓዣ መኪና ለጦሩ ቀርቦለታል እየተባልን ነው?

በበኩሌ በሰሞኑ እሰጥ አገባና የፓል ቶክ ግብግብ ቅር ተሰኝቻለሁ። መጠየቅ ያለባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ሳይነሱ ሁሉም ወገን በስሜት ውሳኔዎችን በስድብ አጅቦ ደርድሯል ። ለምሳሌ ግንቦት 7 ከሻዕቢያ ጋር መወገኑ አዲስ ዜና አይደለም ። መሪዎቹ አስመራ መመላለሳቸውም የተነገረ ነው ። አንዱ መሪ ወደዚያ ሲያቀና ነው በየመን ተይዞ ለወያኔ የተሰጠው ። ስለዚህም ግንቦት 7 የሻዕቢያ ወዳጅ ወይም መሳሪያ ሆነ የሚለው የለፋ ቆዳን ዳግም ማልፋት ነው ። ለነገሩ ግንቦት 7 ሻእቢያን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለሻዕቢያ ሳይሸጥ ጦር ሊመስርትና ለድል ሊበቃ ከቻለ ብዙም ባላከራከረ ነበር ። ዋናው ጉዳይ አሁን ይህ አከራካሪ ጉዳይ ሳይሆን እውን ህዝባዊ ሀይል የሚባልስ አለ ወይ? አቅሙስ ምን ያህል ነው ? ተጀመረ የተባለው ጦርነት በእውነት ተጀምሯል? ተዓምረኛውስ ጦር እንዴትስ ከመቅጽበት ጎንደር ዙሪያ ደረሰ? በቃፍቲያ እውን ተኮሰ? ተታኮሰ? ለነዚህ ነው መልስ የሚፈለገው፤ ትኩረትም መሰጠት ያለበት ። ይህን አድበስብሶ ግን ወያኔን ለመጣል ከሰይጣንም ጋር ቢሆን መተባበር ይገባል አይገባም ብሎ ርዕስ መቀየሩ ለክርክሩም ሆነ ሀቁን ለማግኘት አይረዳም ።

ላላፉት 20 ዓመታት ወደ ኤርትራ ያቀኑ ሀይሎች ሁሉ አይዋጉበት አያስፈራሩበት ሆነው መክነው ቀርተዋል ። ቀደም ሲል ኦነግም ፤ አርበኞች ግንባርም፤ ቱሃት ፖልና መቶ አለቃ ኦላናም፤ ቤኒ ሻንጉሎችም እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞካክረው በልዩ ልዩ ምክንያት ከሽፎባቸዋል፡፡ አንዳንዶች ለዚህም ውድቀት የሻእቢያ ተጠያቂነት መጠቅስ አለበት (ተስፋዬ ጌታቸውን በመግደሉ፤ ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህን አስሮ ደብዛውን በማጥፋቱ፤ ኦነግን በአራት በመክፈሉ፤ ድርጅቶችን በመከፋፈሉ ወዘተ)፤ ሊከሰስ ይገባዋል ይላሉ። አቶ አንዳርጋቸው ራሱ ወደ ኤርትራ ተመላልሶ ከሻዕቢያ የፈለገውን እርዳታ ሊያገኝ ባለመቻሉ ይበሳጭና ተቃውሞም በምርጥ ቦታዎች ያሰማ ነበር ተብሏል ። ለማንኛውም የእሱም ጥረት — ተዋጊ ሀይል ለመመስረት — ሊሳካለት እንዳልቻለ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ ።ከኬንያ፤ደቡብ አፍሪካ ወዘተ ተመልምለው ወደ ኢርትራ የተላኩ ወጣቶች ብዙም ሳይቆዩ እየሸሹ ወጥተው በተወሰነ ጊዜ ከወደ አውስትራሊያና በስዊድኑ አንድነት ራዲዮ አማካኝነት አጋልጠው ነበር። እየተመናመነ የመጣው የአርበኞች ግንባር (እኔ ነኝ ይህ ግንባር የሚሉ ቢያንስ ሶስት ቡድኖች አሉ) በሻእቢያ በኩል ከግንቦት 7 ጋር እንዲጣመር የተደረገበትን ግፊትና ጫና ለረጅም ጊዜ ተቁዋቁሞ ነበር ተብሎ የነበረው ተቀይሮ ከአቶ አንዳርጋቸው መያዝ በኋላ — እጆች ተጠምዝዘው– ውህደቱ ተመሰረተ ተባልን ።ሕዝባዊ ሀይል የሚባለው ማለት ነው። ይህን ተስታኮ በነአቶ ነዓምንና በነ ፋሲልና መሳይ የሚባሉ ግንቦቴዎች የተደረገ ጉብኝትና አሳፋሪ ለኢሳያስ መስገድ የተነሳ የግንቦት 7ም ድጋፍ መቀነሱ ምስጢር አይደለም። ሁለቱ ጋዜጠኞች አንድ ዜጋ እንዳለው ኢሳያስ ፊት እንደ አፈረች ልጃገረድ እየተሽኮረመሙ አፍረው ሲያሳፍሩን በግላጭ አይተናቸው ጉድ ብለናል።

በመጀመሪያ የወያኔን ጦር እንደሚባለው ድባቅ የሚመታ ጦር በድርጅቶቹ ተመስርቷል ወይ? መልሱ የለም የሚል ነው። የአርበኞች ግንባር ጦር ሻዕቢያ ተደባልቆት ቪዲዮ ሳይነሳ ግፋ ቢል 50 ቢደርስ ነው ተብሏል ። ይመሩት የነብሩት እነ ፕርፌሰር ሙሴም ቁጥሩን ከዚህም አያደርሱትም ። የአማራ ንቅናቄ የሚባለው ሲበተንና መሪው የነበረው ኮለኔል ወደ ስዊድን ለስደት ሲሄድ ከጠፊ ቀሪ የነበረውም የሰው ቁጥር ብዙ የሚባል አልነበረም ። ለማንኛውም ይሁንላቸው ብለን የሕዝባዊ ሀይልን መቶ እናድርስ። የመቶ ሰው ጦር በተጠናከረ ደረጃ በወያኔ ተዘግቶ የሚጠበቀውን ድንበር ጥሶ ወረራ ለማካሄድ ይችላል? አይችልም ነው መልሱ ። ሻዕቢያም ካልቃዠ በስተቀር በዚህ መልክ ወያኔን ሊተናኮስ ዝግጁ አይሆንም ። ከወደ ቃፍቲያና አክባባቢው ተሰምቶ የነበረው ተኩስ ሀገሬው ከወያኔ ጋር በመሬትና በብረት አውርድ ጉዳይ ባደረገው ግጭት ነው የሚለውን ሀቅ ወደ ጎን እናድርግና የመቶ ሰው ጦር ሀምሳ ገድሎ ስድሳ ለማቁሰል (ምነው ማንም ተማረከ የሚል መስማት አቃተን?) ብዙ ጥይትን መጨረሱ አይቀርም ። ወደ ኋላ ተመልሶ ተጨማሪ ጥይት አመጣ እንዳንል (በነፍስ ወከፍ እያንዳንዱ የሚሸከመው በሺዎች ሊሆን አይችልምና) ጦሩ ገሰገሰ ተብለናል። ነጻ መሬት ልያዝ ብሎም አይጨነቅም ሲል የኤሳቱ ቱሪናፋ አስደምጦናል ። ከሁመራ ጎንደር ወደ 257 ኪሎሜትር ነው ዳንሻ ደግሞ ከጎንደር ቢያንስ ወደ 152 ኪሎሜትር ይርቃል። ሳንጃ ደግሞ ከጎንደር አንጻር ናዝሬት/አዳም አዲስ አበባ ማለት ሲሆን ዛሬ በህዝባዊ ሀይል ጦር ታመሱ የሚባሉት አብደራፊና መተማ ደግሞ ከቃፍቲያ የሚጠይቁትን የእግር ጉዞ እነ መሳይ ባያውቁትም የአካባቢው ሕዝብ ያውቃል ። የነብርሃኑ ጦር ሁመራም ተታኮስኩ ካለ (ይህ ነው የማይባል የወያኔ ጦር ከሻእቢያ/ኡም ሀጀር/ ተፋጦ ባለበት ጥቂቶች ሞተውበት ና ወያኔን ገድሎ ሊያመልጥ አይችልም ። ወያኔ ከመጀመሪያው ጥይት አንስቶ አሳዶ ጉዳት ባደረሰባቸው ነበር። በየአቅጣጫው ጦር ሰደው ወያኔን እየመታን ነው ካሉ ደግሞ ይህ የብዙ ሺዎች ወታደሮችን ስምሪት ይጠይቃል። ነገሩን በአጭሩ ለመቅጨት እንመናቸው ብለን ብንሞክርም ማመን ያስቸግራል። ነጭ ውሸት ነው — ጭፍን ተከታዮችን (ያውም ልብ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እያሉ)–ብቻ የሚያታልል ።

ከኤርትራ ተነስቶ ወያኔን ያጠቃ ጦር የለም።
ኤሳት የሚያወራው ሀሰትና የፈጠራ ወሬ ነው።

ማንም አልተማረከም እንዴ ስንላቸው የትግሬ ስም ደርድረው ተገደለ ተማረከ ሊሉን እንደሚችሉ እንገምታለን ። ይህ ሁሉ ውሸት ግን ውሎ አድሮ ይጋለጣል– ያመኑ ያፍራሉ። ይብላኝ ለብርሃኑ ያኔ? ስለጦሩ እንቅስቃሴ ምንም መግለጫ ያስልሰጠው ብርሃኑ ነገ እውነቱ ሲጋለጥ በመዋሸቱ አልነበርኩበትም ለማለት ይሆን? ያጠራጥራል ። የተኩሱ ቪዲዮ በሻዕቢያ አቀነባባሪነት በዚያው በጉልች — ተሰነይ አካባቢ ኮለኔል ሙሴ ቪላ አካባቢ–የተነሳ ነው ። የሀሰቱ አቀነባባሪዎች ግን ሕዝብን ንቀዋል ። በግርግር ቶሎ ቶሎ ገንዝብ ሊመነትፉን የ 500ዶላር፣ የ250ና የመቶ ዶላር ቲኬቶች አዘጋጅተዋል ። አሁንም የሚሞኝ የሚዘረፍ ይኖራል–ቢያንስ የነብርሃኑ ተስፋ ይህ ነው ። በሎስ አንጀለስ የተሞከረው አልተሳካም ። በሊሎች ቦታዎችም የታቀደው የሚሳካ አይመስልም ። ለነብርሃኑ አታዋጡ፤ ለአርበኝነት ሰርቲፊኬት ብሎ ወሰደው 500 ዶላር ይበቃል የሚሉንም አሉ ። የወልቃይት ተወላጆች ደግሞ መሬታቸውን መነጠቃቸው ሳያንስ ትግላቸውም በሻዕቢያ መነገጃ መዋሉ ያስቆጣቸው መሆኑን ገልጸዋል ። ከቃፍቲያ በሁለት ሳምንት መተማ የሚደርስ ጦር ምን ያህል ቢበዛ ነው? የስንቅና የመጓጓዣም ጉዳይ አለ። ለመሆኑ 50 እየገደለ ነው ከዚያ የሚደርሰው? በኢዲዩና በኢሕአፓ በነዚህ ሁሉ አካባቢዎች የታገሉ ያካባቢውን ተወላጆች ጨምሮ፣ መሬት ነጻ ያወጡና ዛሬም በሕይወት በሀገር ቤትም በአሜሪካም አውሮጳም የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ብርሃኑ ተረሳው እንዴ? ሀቅ ሀዘን ገብቶ ውሸት ጮቤ ልትረግጥ ብትችልም ሀቁ መጋለጡ አይቀርም።

ለግንቦት 7 ደጋፊዎችና አባሎች ያለኝ መልዕክት ድርጅታችሁን ከወደዳችሁት ከሻዕቢያና ከቅጥረኞቹ አላቁትና ከሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጎራ ቀላቅሉት የሚል ነው።

ለኢሳት አድማጮችና ደጋፊዎች ደግሞ ይህ ስርጭት በግንቦት 7 ቁጥጥር ስር የገባና ለሻዕቢያም አፈቀላጤ በመሆኑ ከቻላችሁ ነጻ ራዲዮ ለማድረግ ታገሉ ሲሆን ካልተቻለ ደግሞ ማዕቀብ አድርጉበት የሚል ነጻ ምክሬን አሰማለሁ።

ለመላው ሕዝብ ግን ይህንን አዲስ የሻዕቢያ ጸረ ትግል ሴራ በጋራ ሆነን አጋልጠን እናክሽፈው የሚል ነው።

ዋሾዎች ይጋለጣሉ !!
የምትሀት ጦር ኢትዮጵያን ነጻ አያወጣም !!

Leave a Reply