Wednesday, 22 July 2015 13:44
“የኤርትራ መንግስት ከግንቦት ሰባትና ከአርበኞች ግንባር ጋር የፈጸመው ያረጀ ጋብቻ፣ ዜና መሆኑ አስገራሚ ነው”
አቶ እውነቱ ብላታ
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ
በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የአርበኞች ግንባር እና ግንቦት ሰባት የጋራ ግንባር በመፍጠር ከኤርትራ ግዛት በመነሳት የትጥቅ ትግል መጀመራቸው እየተዘገበ ቢገኝም ያረጀ የሽብር ጋብቻ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ስጋት አይሆንም ሲል የኢትዮጵያ መንግስት ዘገባውን ውድቅ አደረገ።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ስለሁኔታው ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት፣ “የኤርትራ መንግስት ከግንቦት ሰባትና ከአርበኞች ግንባር ጋር የሽብር ጋብቻ ከፈጸመ አመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ ላይ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ይህን ያረጀ የሽብር ጋብቻ በአዲስ መልክ ለመዘገብ እንደተፈለገ የሚያውቁት ዘገባውን ያጠናከሩት ተቋማት ናቸው። በመንግስት በኩል ገንዘብ ለመሰብሰብ የተቀናጁ ግለሰቦች በምንም አይነት መመዘኛ ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የስጋት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም” ብለዋል።
“ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ከፍተኛ የግንቦት ሰባት አመራሮች ትጥቅ ትግል ለማድረግ ወደ አስመራ መግባታቸው ተነግሯል። ወደ አሜሪካም ዳግም እንደማይመለሱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። በዚህ ላይ የመንግስትዎ አስተያየት ምንድን ነው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ እውነቱ በሰጡት ምላሽ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግንቦት ሰባት ፓርቲና የፖለቲካ አመራሩን በሽብርተኝነት መፈረጁ የሚታወቅ ነው። አሁንም አሸባሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ እንደተጠበቀ ነው። በሕግ ስርዓታችንም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሞት ፍርድ የተበየነበት ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ የሞት ፍርድ ውሳኔው ሊያሸብረው፣ ፍርሃት ሊደቅንበት እንደሚችል የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ፍርሃት አዙሪት ለመላቀቅ ዲያስፖራውን በየአዳራሹ እየሰበሰበ ይህን አድርገናል፣ ወደፊት ይህን ልናደርግ ነው እያለ በአደባባይ ገንዘባቸውን ሲዘርፍ የከረመ ሰው ነው። አሁን ደግሞ አዲስ ታክቲክ ዘርግቶ በረሃ ገብቼ ልታገል ነው፣ ገንዘብ እርዱን የሚል ስልታዊ የዘረፋ መንገድ ፈጥሮም ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ እነዚህ ግለሰቦች የመደብ ውክልናም ሆነ ማሕበራዊ መሰረት ሳይኖራቸው ወደ ትጥቅ ትግል ገብተናል ማለታቸው የዲያስፖራውን ሕብረተሰብ ለመዝረፍ ያላቸውን ተነሳሽነት ከማሳየት ውጪ ቦታ የሚሰጠው ተግባር አይደለም” ሲሉ አቶ እውነቱ ተናግረዋል።
“የኤርትራ መንግስት ለአሸባሪዎች መጠለያ ይሰጣል ተብሎ በመንግስትዎ ከታመነ፣ በቀጣይ በኤርትራ መንግስት ላይ ሊወሰድ የታቀደ እርምጃ ወይም ወደ ሙሉ ጦርነት የሚያስገባ ሁኔታዎች ሊፈጥር ይችል ይሆን?” ለሚለው ጥያቄም አቶ እውነቱ ሲመልሱ፣ “የኤርትራ መንግስት የሽብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መከተል የጀመረው ዛሬ አይደለም። በእኛ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብምና በቀንዱ ሀገሮች የሚታወቅ ባሕሪው ነው። ኢትዮጵያም የኤርትራ መንግስት በሚፈጽመው የሽብር ድርጊት መነሻነት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዷ ይታወሳል። አሁኑም በሚደቅነው የሽብር አደጋ መጠን ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስትን አቋም ገልጸዋል። ወደ ሙሉ ጦርነት ውስጥ ልትገቡ ትችላላችሁ ለተባለው፣ ሙሉ ጦርነት ለማካሄድ እኩያነት ያስፈልጋል። ይህም ሲባል፣ የኤርትራ መንግስት በሂደት ራሱን እየጨረሰ፣ እያጣፋ ያለ መንግስት ነው። ዜጎቹን ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ እየገረፈ የሚያሰቃይ መንግስት ነው። የኤርትራ ወጣቶች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው በሳዋ ጦር ሰፈር ተከማችተው ነው የሚገኙት። ከዚህም ስቃይ ለማምለጥ የኤርትራ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በየቀኑ እየጎረፉ ነው። ከዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብም ተገልሎ ያለ መንግስት ነው። እነዚህ እና ሌሎች ችግሮቹ ሲደመሩ የኤርትራ መንግስት የውድቀቱን ቁልቁለት የጀመረ መንግስት በመሆኑ እኛ የጀመርነውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አጥፈን ከኤርትራ መንግስት ጋር ጦርነት የሚያስገባን አንዳችም አስገዳች ሁኔታ የለም። የኤርትራ መንግስት መወገድም ካለበት በጀመረው የውድቀት ቁልቁለት እና በኤርትራ ሕዝብ ውሳኔ ብቻ ነው።” ብለዋል።