26 JULY 2015 ተጻፈ በ 

መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ያሳስበው!

የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስመልክቶ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንደገና ትልቅ አጀንዳ ሆኗል፡፡ መንግሥትም ሰሞኑን የአገሪቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች የሚካሄዱበትን ዘመቻዎች

የሚመከትበት አንድ ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከፍተኛ ዕውቅና የተሰጠው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሁሌም መነጋገሪያ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ዘመን ለሰብዓዊ መብት ከምንም ነገር በላይ ክብደት መስጠት የግድ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት በሚከበርበት ሰላም፣ ብልፅግናና ተስፋ ሲኖር፣ ሰብዓዊ መብት ሳይከበር ሲቀር ደግሞ ለአመፅና ለብጥብጥ መንገድ ይከፍታል፡፡ ለዚህም ነው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ማግኘት አለበት የሚባለው፡፡

መንግሥት ሰሞኑን ያወጣው ሰነድ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ኃይሎች በአገሪቱ በመገንባት ላይ ባለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ በተከታታይ የሚያካሂዱዋቸውን ውንጀላዎች በማጋለጥ በተቀናጀ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችለው መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህ ሰነድ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች በማለት ዘመቻ የተከፈተባቸው የአገሪቱን ልማት ለማፋጠን፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን በሥራ ላይ የዋሉትን ሦስት ነገሮች ነው፡፡ እነሱም  የፀረ ሽብር ሕግ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕግ፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ ናቸው፡፡ በተለይ እነዚህ ለአገሪቱ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሕጎች ራሳቸውን በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰፊ ዘመቻ ከፍተውባቸዋል በማለት መንግሥት በሰነዱ አማካይነት ያወግዛቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመንግሥት በተቃራኒ የቆሙ ወገኖች መንግሥት ለልማት ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ ሰብዓዊ መብትን ችላ በማለት የዜጎችን መብት እየረገጠ ነው በማለት ይቃወሙታል፡፡ ይህ ተቃውሞ በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ይስተጋባል፡፡ መንግሥት የሚከራከርላቸው እነዚህ ሦስት ሕጎች ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሕጋዊ ሽፋን የሰጡ በመሆናቸው፣ አገሪቱ አፈና የሚካሄድባት ሆኖለች በማለት በተደጋጋሚ ይተቻሉ፡፡

መንግሥት እነዚህ ወገኖች ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መፋጠን የሚበጁ የሚላቸው ሕጎች እንዲሰረዙና የአገሪቱን ገጽታ ለማበላሸት የሚያደርጉትን የተቀናጀ ዘመቻ ለመመከት መነሳቱን ይገልጻል፡፡ ይሁንና በተቃራኒው ያሉ ወገኖች ደግሞ መንግሥት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እያሰረ መብት ይጥሳል በማለት ይወነጅሉታል፡፡ ይህ ክርክር ለዓመታት ቀጥሎ አሁንም በተለይ በዚህ ወቅት በጣም ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ከተሰማ ወዲህ፣ አገሪቱ በልማት ያሳየችው ስኬት ተመራጭ እንዳደረጋት በተለያዩ ወገኖች የተስተጋባውን ያህል፣ የሰብዓዊ መብት አያያዙ ጉዳይ ሲወገዝ ነው የከረመው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የተስተጋባው ይኼው ነው፡፡ ሰሞኑን የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የምዕራብ ንፍቀ ክበብ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴኔተር ማርኮ ሩቢያ ለፕሬዚዳንቱ በጻፉት ደብዳቤ፣ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ለሰብዓዊ መብትና ለፕሬስ ነፃነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ ሴኔቴሩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በፀረ ሽብርተኝነትና በአካባቢው መረጋጋት ላይ የጋራ ዓላማ ቢኖራትም፣ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ላይ እንዳላየ ሆና ማለፍ የለባትም ብለዋል፡፡ የመንግሥት ተግባርን እንዲያወግዙ ጠይቀዋል፡፡ ይልቁንም መንግሥት የሰብዓዊ መብትና የመደራጀት መብትን እንዲያከብር ማስገንዘብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ይኼ እንግዲህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

መንግሥት የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ በጣም ተለጥጦ በውጭ ኃይሎች ሰፊ ዘመቻ ተከፍቶበታል ሲል፣ የራሱን መረጃ ደግሞ ደጋግሞ መመርመር አለበት፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን ይጋፋል፣ የፕሬስ ነፃነትን አያከብርም ተብሎ ለዓመታት እየተተቸ መሻሻል በሌለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ተከፈተብኝ የሚለውን ዘመቻ ለመመከት የተዘጋጀውን ያህል ጉድለቶችን መመልከት የግድ ይለዋል፡፡ መንግሥት ለልማት የሰጠውን ትኩረት ያህል ለምን ለሰብዓዊ መብትና ለፕሬስ ነፃነት አይሰጥም? ተብሎ ሲጠየቅ አመርቂ መልስ መገኘት ይኖርበታል፡፡ በአገሩ ግብር ከፋዮች ከፍተኛ ተጠያቂነት ያለበት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይህንን ጉዳይ በዋናነት እንዲያነሳ ሲጎተጎት፣ ለራሱ ሕዝብ ተጠያቂነት ሊኖርበት የሚገባው የኢትዮጵያ መንግሥት ጉድለቶችን ሳያርም ለሙግት ቢነሳ ትርፉ ትዝብት ነው፡፡

በተደጋጋሚ እንደሚባለው ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ናት፡፡ የሚያስተዳድራት መንግሥትም ተጠሪ መሆን ያለበት ለሕዝቡ ነው፡፡ ለሕዝብ ተጠሪ የሆነ መንግሥት ደግሞ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን በሚገባ መረዳት አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምሰሶ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ተሟልተው በማይገኙበት ሁኔታ ውስጥ ሰብዓዊ መብት ሲጣስና የፕሬስ ነፃነት ሳይከበር ሲቀር፣ በርካታ ጩኸቶችና አቤቱታዎች ቢቀርቡ ሊያስገርም አይገባም፡፡ ይልቁንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የሠፈሩትን የሰው ልጆች መብቶች የሚያስጠብቁ አንቀጾችን አቅፎ የያዘው ሕገ መንግሥት ካልተከበረ፣ በውስጥና በውጭ ግፊት የሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ይቀጥላሉ፡፡ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይም አደጋ ይደቅናሉ፡፡

መንግሥት በልማትና በሰብዓዊ መብት ትስስር የአገሪቱን ዕይታ አመልካች ነው ብሎ ያመጣው ሰነድ ይፋ መደረጉ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች የሚካሄዱ የስም ማጥፋት ውንጀላዎች ብቻ ነው ብሎ መደምደሙ ግን ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም መሬት ላይ ያለው ዕውነታና ወረቀት ላይ የሠፈሩት ሐሳቦች በጣም የተራራቁ ናቸው፡፡ ይህ ሰነድ የተሻለ መከራከሪያ ይዞ እንዲዘጋጅ መንግሥት ከፈለገ፣ በመጀመሪያ መሬት ላይ ያሉትን ችግሮች አንጥሮ ይመርምር፡፡ ሰዎች በአመለካከት ልዩነት ምክንያት ለምን ይታሰራሉ? እንደተባለው በተለይ የፀረ ሽብር ሕጉ ተቃውሞን ፀጥ ለማሰኘት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ወይ? ሌሎቹ ሕጎችስ ዴሞክራሲን ለማፈንና ሰብዓዊ መብትን ለመጣስ እያገለገሉ ነው ወይ? የሚለውን በተጨባጭ መሬት ተወርዶ በባለሙያዎች ይመርመር፡፡ ከዚያ በኋላ ሰነዱ በሚገባ ዳብሮ ተዘጋጅቶ እንደተባለው አደባባይ በኩራት ቢወጣ መልካም ነው፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባኮረፉበት፣ አባላቶቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሲታሰሩባቸውና ሲጉላሉባቸው፣ ጋዜጠኞች በሥራችን ምክንያት እየታሰርንና እየተሰደድን ነው እያሉ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አልተከበረም፣ ወዘተ እየተባለና በርካታ ችግሮች በሚደመጡበት አገር ውስጥ የሚሰሙት ድምፆች ሐሰተኛና ውንጀላዎች ናቸው ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ በርካታ ተቃውሞዎች በተለያዩ የአሜሪካ ሚዲያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየቀረቡባቸው ችላ ብለው ወደዚህ መምጣታቸው ዕውን ሆኗል፡፡ አሜሪካ ዘላቂውን ጥቅም እያሰበች ለነገ የቤት ሥራዋ መዘጋጀቷ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጥረው ምሥል ጠባሳው ቀላል አይደለም፡፡ አገሪቱ በኢኮኖሚ መስክ ባስመዘገበችው ስኬት እየተጨበጨበላት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስሟ ሲብጥለጠል መስማት ያሳዝናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም ነገር አቻችለው ሲመጡ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ስኬት ነው ያመጣቸው በማለት ብቻ መኩራራት አይበጅም፡፡ ከዚህ በላይ በዓለም አደባባይ ደረት የሚያስነፋ ሁሉን አቀፍ ስኬት ማስመዝገብ ይሻላል፡፡ በሰብዓዊ መብት ምክንያት የሚነሳው ተቃውሞ መርገብ የሚችለው ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ በሰብዓዊ መብት ምክንያት አገር አንገቷን አትድፋ፡፡ ለዚህም ለሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ! አፋጣኝ ዕርምጃ ይወሰድ! መንግሥትን በጣም ያሳስበው!

Leave a Reply