26 JULY 2015 ተጻፈ በ 

‹‹ለውጥ›› በሚለው ከፍተኛ ጉልበት ያለው ቃል የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ የሳበ ‹‹የምረጡኝ ቅስቀሳቸው›› እጅግ ይታወቃሉ፡፡ ምናልባት በአገራቸው ውስጥ ስለሚካሄድ ምርጫም ሆነ የመንግሥት ለውጥ ደንታ የሌላቸው ሳይቀሩ በወቅቱ በኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ ያልተማረከ አልነበረም፡፡

 

በቀለማቸውም ሆነ በቅድመ ታሪካቸው ከቀደሙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ለየት የሚሉት ባራክ ኦባማ፣ በአሜሪካ ምድር የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሁለት ጊዜ ተፎካካሪዎቻቸውን በምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙት የልዐለ ኃያሉዋ አሜሪካ መንበረ ሥልጣን ለሌላ አሸናፊ ሊያስረክቡ የሚቀራቸው ዓመት ከመንፈቅ ብቻ ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ለሦስተኛ ጊዜ እንዲወዳደሩ አይፈቀድላቸውምና፡፡

በተዓምረኛው የምርጫ ቅስቀሳቸው የገቡትን ቃል ያህል ለአሜሪካዊያን ‹‹ለውጥ›› አላመጡም በሚል ትችቶች ይቀርቡባቸዋል፡፡ በዓለማችን በኢኮኖሚ ቁጥር አንድ የሆነችው አሜሪካ ‹‹99 በመቶ ምጣኔያዊ ሀብቷ ሁለት በመቶ በማይሞሉ ሰዎች እጅ ይገኛል›› በማለት በዎል ስትሪት ሠልፍ ወጥተው አቤቱታ ያቀረቡ አሜሪካዊያን ቁጥር አነስተኛ አልነበረም፡፡ የብዙኃኑ የአሜሪካዊያን ጥያቄም ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡

ጉዳዩን እጅግ አነጋጋሪ የሚያደርገው የአሜሪካ መንግሥት አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሥፍራዎች ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን ፊታውራሪ መሆኑ ነው፡፡

በሥልጣን ዘመናቸው በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች የገጠሙዋቸው ኦባማ ሽብርተኝነትን፣ የእስራኤልና የፍልስጥኤም ግጭትንና እንዲሁም በተለይ የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የዓለማችን በተለይ ደግሞ የአሜሪካ የዘመናችን ቁጥር አንድ ጭንቅ ከሆነው ሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ በመካከለኛ ምሥራቅ በምትወስዳቸው ዕርምጃዎች በርካታ ትችቶች የሚቀርብባት አሜሪካ፣ የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን የተገደለው በኦባማ የሥልጣን ዘመን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከፍ ያለ ውዝግብ ሲያነሳ የነበረው ‹‹ኦባማ ኬር›› በመባል የሚታወቀው የጤና ዋስትና ሽፋን የፀደቀውም በእሳቸው ጊዜ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው አሜሪካዊያን የሚመለከት የውስጥ ጉዳይ ሲሆን፣ አሜሪካ በተለይ ከሦስተኛ ዓለም ጋር እያላተማት ያለው የግብረ ሰዶም ነፃነትን የሚያውጅ ሕግም በቅርቡ በሴኔት አፅድቃለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ የአፍሪካ ጉዳዮችን ጮክ ብለው በመናገር የሚታወቁት የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤና የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን ጨምሮ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት ያለው ይኼው ጉዳይ፣ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንዲሆን በኃይል እየገፋችበት ነው፡፡ በአሁኑ የኬንያና የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ጋር በተያያዘም ከጋዜጠኞች ተደጋግሞ እየቀረበባቸው ያለው ቁጥር አንድ ጥያቄ ይመስላል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ደግመ በተደጋጋሚ እየቀረበ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነው፡፡

ኦባማና ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ የሚመጡት ባራክ ኦባማ አፍሪካን ሲጎበኙ ለአራተኛው ጊዜያቸው ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ደግሞ የመጀመርያቸው ነው፡፡ ወደ አባት አገራቸው ወደ ኬንያም ሲሄዱም ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ወደ ኬንያም ወደ ኢትዮጵያም ሥልጣን ላይ ሆኖ የመጣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባለመኖሩ እሳቸው የመጀመሪያው ናቸው፡፡

ሥልጣን ላይ ሲወጡ በአሜሪካ ከሚገኙት በተለይ መንግሥትን ከሚቃወሙ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በሥልጣን ዘመናቸው ጫና ያደርጋሉ የሚል ተስፋም በብዙዎች ዘንድ ተጥሎባቸው ነበር፡፡

በቡሽ አስተዳደር አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ዕርዳታ እንዲቀንስና የፖለቲካ ጫና እንድታደርግ የሚያዘው ኤችአር 2003 መሰል አዋጅ እንዲያፀድቁም ግፊት ቢደረግም ነበር አልሆነም፡፡

ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ይልቅ ለአሜሪካ በአካባቢው ቁጥር አንድ የሆነውን ሶማሊያ ውስጥ የመሸገውን የሽብርተኝነት ሥጋት ያስቀደሙ ይመስላል፡፡ የኦባማ አስተዳደር አንዳንድ አፍአዊ ንግግሮች ከማሰማት ይልቅ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ የተጠበቀውን ያህል አጀንዳ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ የአሁኑም ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን፣ ይኼ ጉብኝት ‹‹ዴሞክራሲያዊ መንግሥት›› መሆኑን ማረጋገጫ እየሰጠ ነው የሚል ገጽታ ይዟል፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሱዛን ራይስ ከፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ጋር በተያያዘ ይህ ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹በኢትዮጵያ በተለይ የጋዜጠኞችን አያያዝ በተመለከተ ሥጋታችንን በተደጋጋሚ ለመንግሥት ገልጸናል፡፡ በቅርቡ አምስት ጋዜጠኞች ከእስር ተፈተዋል፡፡ የሚበረታታ ተግባር ነው፡፡ በዚሁ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ውይይት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ አሁንም እንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች አንስተን እንነጋገርበታለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኬንያና የኢትዮጵያ መሪዎች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የመጡ ናቸው ብለው ያምናሉ?›› በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹በመጀመሪያ አዎ! የኬንያ ፕሬዚዳንት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው የተመረጡት፡፡ ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያም ጠቅላይ ሚኒስትርም እንደሚመስለኝ መቶ በመቶ ድምፅ ነው የተመረጡት፡፡ በእርግጥ ውጤቱ ላይም ባይሆን ሒደቱ ላይ የተዓማኒነት ችግር እንደነበር አመላካች ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግን ኦባማ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነበር ብለው ያስባሉ?›› በማለት አንድ ጋዜጠኛ ጥያቄውን ይቀጥላል፡፡ ‹‹አዎ! መቶ በመቶ›› በማለት ሱዛን ራይስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተገቢነት ብዙዎችን እያነጋገረ ሲሆን፣ ይህንን ጉብኝት አስመልክቶ የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ አዘጋጅ ጆን ሶፔል ለፕሬዚዳንት ኦባማ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡ ‹‹ይመስለኛል ከተመረጡ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ባቀኑበት ጊዜ ‘በአፍሪካ የምንፈልገው ጠንካራ ተቋም እንዲገነባ ነው’ ብለው ነበር፤›› ሲላቸው የኦባማ ምላሽ ‹‹አዎ!›› የሚል ነበር፡፡

ጋዜጠኛው ጥያቄውን አልቋጨም፡፡ ‹‹ጠንካራ መሪ አላሉም፡፡ ወደሚሄዱባት ኢትዮጵያ ግን አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሌለበት ፓርላማ ነው፤›› ይጠይቃል፡፡ ‹‹እውነት ነው፤›› ነበር የኦባማ ምላሽ፡፡

‹‹በኬንያም ቢሆን ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ የመሠረተባቸው ባለሥልጣናት ያሉበት መንግሥት ነው፤›› ሲል አከታትሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ የኦባማ ሰፋ ያለ ምላሽ ይቀጥላል፡፡

‹‹መልካም! በእርግጥ ጠንካራ ተቋማት አይደሉም ያሉት፡፡ ነገር ግን ከመንግሥታቱ ጋር በመቀራረብና በድፍረት በመናገር ለሲቪክ ማኅበረሰቦች የሚሆን ቦታ ለመፍጠርና ለማግኘት ዕድል ይሰጠናል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችንም አጀንዳ ለማድረግ ዕድል ይከፍታል፤›› በማለት ብዙዎች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ የሚሆን ምሳሌ ሰጡ-የበርማ ጉብኝታቸውን፡፡ ‹‹በርማን ስጎበኝ የተወሰነ የለውጥ ጭላንጭል አይተን ነበር፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ግን አልነበረም፡፡ የእኔ ጉብኝት ግን የመብት ተሟጋቾችን ሥራ ያጠናከረና ያጎለበተ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤›› ብለዋል፡፡

የቻይናንም የሩሲያንም ጉብኝት በተመሳሳይነት አንስተዋል፡፡ ‹‹ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ እያየንም ቢሆን፣ አሁንም ከጎናቸው መሆናችንና ወደተፈለገ አቅጣጫ ይጓዙ ዘንድ ውይይት ለማድረግ እንደምንፈልግ ለማሳየት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት የሚጨበጥ ዕርምጃ አልወሰደም በሚል የሚተቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀናቃኞች፣ ይባስ ብሎ በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት የሌለው ሥልጣን ይዟል በሚሉበት የምርጫ ማግሥት እየተከናወነ ያለው የኦባማ ጉብኝት ይህንን ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የሚያጠናክር መስሎ ታይቷቸዋል፡፡ ኦባማ ግን ጉብኝታቸው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዴሞክራሲያዊነት የሚያመላክት ሳይሆን፣ መንግሥታቸው ከበርማ፣ ከቻይናና ከሩሲያ ምድብ እንደሚመድቡት ያሳዩበት ምላሽ ነው የሰጡት፡፡

አምባሳደር ሱዛን ራይስ የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ዋና አጀንዳ የደቡብ ሱዳን ቀውስና የፀረ ሽብር ትብብር መሆኑን ያስረዱ ሲሆን፣ ‹‹በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዓለም ተመሳሳይ ጉብኝት ስናደርግ ጉብኝት በማድረጋችን ከሚሰጠው ትርጉም ይልቅ፣ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ላይ አንስተን የምንናገርባቸው ጉዳዮች በዘላቂነት ሕዝቡን የሚጠቅሙ ናቸው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ለማንኛውም ግን ከደርግ ውድቀት በኋላ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የምናደርግበት ነው፤›› ብለዋል አምባሳደር ራይስ፡፡

የግብረ ሰዶማዊያን መብት 

የኦባማ ጉብኝት የአሜሪካ ሴኔት የግብረ ሰዶማውያንን ጋብቻ የሚፈቅድ ሕግ በማፀደቅ አሜሪካ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሆኖ እንዲታይ የምትንቀሳቀስበት በመሆኑ በጉብኝቱ አንዱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በተለይ በኬንያ ይህንን በመቃወም 500 ሴቶች እርቃናቸውን እንደሚቀበሉዋቸው ተገልጾ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም የታሰበ ተቃውሞ ባይኖርም፣ በተለያዩ መንገዶች ውዝግብ እንዳስነሳ ይስተዋላል፡፡

ይህንን አስመልክቶ በተለይ የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ዊሊያም ሩቶ፣ ‹‹በአሜሪካ የግብረ ሰዶም መብት መፍቀዳቸውና ሌሎች አፀያፊ ነገሮችን ሰምተናል›› ማለታቸውን አንስቶ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጉዳዩን ለኦባማ አንስቶላቸዋል፡፡ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ከእሳቸው እለያለሁ፤›› በማለት አስተያየታቸውን ቀጥለዋል፡፡

‹‹ቀደም ብሎ ሴኔጋልን በጎበኘሁ ጊዜ ከፕሬዚዳንቱ ተመሳሳይ ተቃውሞ ገጥሞኛል፡፡ እኔም የመሰለኝን በድፍረት ከመናገር አልተቆጠብኩም፡፡ ሁሉም ሰው በፆታም ሆነ በቀለም፣ እንዲሁም በፆታዊ ፍላጎቱ እንዲገለል አልፈልግም፡፡ ስለሆነም የአጀንዳችን አንድ አካል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤›› ብለዋል፡፡

ኦባማና የአፍሪካ ተስፋቸው

እ.ኤ.አ. በ2008 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ባራክ ኦባማ፣ በአባታቸው ከጎረቤት ኬንያ ውስጥ ከሚገኘው አንድ አነስተኛ መንደር የተገኙ ሲሆኑ፣ ኦባማም መንበረ ሥልጣን ላይ በወጡ ጥቂት ወራት ውስጥ ባደረጉት ዓለም አቀፍ ጉብኝት ያጠናቀቁት እዚሁ አኅጉር ጋና ነበር፡፡ ‹‹በሰላማዊ የመንግሥት ለውጥ አክራ የአፍሪካ ተምሳሌት ትሆናለች›› በማለት፡፡

ጉብኝታቸውን አስመልክተው ከአክራ ለአፍሪካዊያን ባስተላለፉት መልዕክት እውነትም በአፍሪካዊያን ዘንድ የተስፋና የለውጥ ምንጭ ተደርገው ታይተዋል፡፡ ‹‹እዚሁ ጋና የመጣሁት በአንድ ቀላል ምክንያት ነው፡፡ 21ኛው ክፍለ ዘመን ቅርፅ የሚይዘው ሮም፣ ሞስኮ ወይም ዋሽንግተን ላይ በሚከናወን ሳይሆን፣ እዚሁ አክራና በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ በሚከናወን ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ ንግግራቸው ለዘመናት የቅኝ ግዛት ማረፊያ፣ የዕርዳታ ማራገፊያና የምዕራባዊያን ፖሊሲ መሞከርያ የሆነችው አፍሪካ፣ እውነትም ከገባንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተስፋይቱ ምድር ትሆን ይሆን እንዴ የሚል ተስፋ ጭሮ ነበር፡፡

‹‹ዓለማችን ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ የአፍሪካዊያን መበልፀግ የአሜሪካ መብልፀግ ነው፡፡ የአፍሪካውያን ደኅንነት የአሜሪካዊያን ደኅንነት ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የኦባማ የአፍሪካ መፃኢ ንግግራቸው በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ እነሱም ዴሞክራሲ፣ ዕድል፣ ጤንነትና ሰላማዊ የግጭት አፈታት መላ ናቸው፡፡

የኦባማ አስተዳደር አፍሪካዊያን በራሳቸው መንገድ እንዲለወጡ የአቅም ግንባታ ማድረግ እንጂ፣ ዕርዳታ መስጠት እንደማይሆን በጠዋቱ አሳውቆ ነበር፡፡ ከውጭ የሚመጣ ለውጥ አስተማማኝነትና ዘላቂነትን አይኖረውም ከሚል አስተሳሰባቸው የመነጨ ይመስላል፡፡ ለዘመናት የቆየው የምዕራባዊያን በዴሞክራሲ ስም የሚደረግ ጣልቃ ገብነት የሚያስቀር ነበር፡፡

ቻይና አሜሪካን በመፎካከር ላይ ባለችበት ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ የቻይናዊያን በአፍሪካ የመስፋፋትና አኅጉሪቱን የመቆጣጠር እንቅስቃሴ ወደ አፍሪካ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሳይገድበው አልቀረም፡፡ ይህንን አስመልክቶ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ቻይናዊያን ለዘመናት የተትረፈረፈ ሀብት አላቸው፡፡ ያለተጠያቂነት ወደ አፍሪካ እያመጡት ነው፡፡ ሆኖም ለአፍሪካ የሚሰጠውን ዕርዳታ በፍፁም አንቃወምም፡፡ የንግድ ግንኙነቱ የበለጠ እያንዳንዱን ኬንያዊና ኢትዮጵያን እየረዳ ነው፡፡ ቻይና፣ አውሮፓና አሜሪካ የጋራ አጀንዳ በመፍጠር በጋራ እየሠራን እናገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

ቻይና በአፍሪካ ዕርዳታ በመስጠት፣ ለትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር በመፍቀድና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ መልካም አማራጭ መሆኗ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊያን ቁጥር አንድ የገንዘብና የሐሳብ ምንጭ መሆናቸውን ያስቀረ ይመስላል፡፡ ምሥራቁም ምዕራቡም ከአፍሪካ ጋር ባላቸው ግንኙነት በዕርዳታ ተፅዕኖ ለመፍጠር ከመሆን ወጥቶ የግብይትና የኢንቨስትመንት እንዲሆንም በር የከፈተ ይመስላል፡፡ የኦባማም አስተዳደር ወጣት የአፍሪካ መሪዎችን መፍጠርንና አፍሪካ በኃይል ራሷን እንድትችል ማድረግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዓመት የአፍሪካና የአሜሪካ መሪዎች ስብሰባ እዚሁ አዲስ አበባ መከናወኑ ይታወሳል፡፡

የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በቅርቡ በአዲስ አበባ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በአሜሪካ ድጋፍ የመጣ ዕድል እንደነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኦባማ በተለያዩ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ታጅበው የሚያደርጉት ይኼው ጉብኝት የአሜሪካና የአፍሪካ የንግድና የኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል፡፡ የአፍሪካ ዕድገትና ዕድል ስምምነት (አጎዋ) በኋይት ኃውስ አሥረኛ ዓመቱ እየተከበረ ሲሆን፣ አፍሪካዊያንን የበለጠ ይጠቅም ዘንድ ይሻሻላል የሚል ግምትም አለ፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የስብሰባ አዳራሽ በሚደረገው ውይይት ፕሬዚዳንት ኦባማ የሴቶችና የልጃገረዶች መብት፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች እንቅስቃሴ፣ የምግብ ዋስትና፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ሙስናን መዋጋት፣ ተጠያቂነት ያለው አስተዳደርን ማስፈንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃን የመሳሰሉ ጉዳዮች ያነሳሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡

ከኦባማ ጋር ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪዋ አምባሳደር ሱዛን ራይስ፣ ይህንን ጉብኝት በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ጊዜ እነዚህ ጉዳዮችን በዋናነት አንስተዋል፡፡

Leave a Reply