———-
ከትናንት በስትያ ጠበቃችንን (በአስቸጋሪ ሁነት ውስጥ የብዙዎች ጠበቃ ነበር) ተማም አባቡልጉን በመኖሪያ ቤቱ ተገናኝተን ለሰዓታት ቁም ነገሮችን እንደተለመደው ተጨዋውተን ነበር፡፡ ተማምን ከረመዳን ጾም ፍቺ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበረ በአካል የተገናኘው ስለጾሙም ትንሽ ሀሳቦች ተለዋውጠናል፡፡

በጨዋታ መካከል ስለባልደረባችን ጋዜጠኛ ሀብታሙ ምናለ መታሰር ነገርኩት፡፡ ደነገጠ፡፡ ‹‹አጃኢብ›› አለና ‹‹በምን?›› አለኝ በጣም አዝኖ፡፡ ‹‹የአልሸባብ ህዋስ ነህ፤ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሚገኙበት ስብሰባ ላይ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም አሲረሃል›› ተብሎ ተጠርጥሮ መያዙን አስረዳሁት፡፡ ተማምና ሀብታሙ በአካል ይተዋወቃሉ፡፡ ሀብታሙ ከጋዜጠኝነት ሥራው ባሻገር፣ በዋነኝነት (በቀዳሚነት ብል ይሻላል) የቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ እና የሰንበት ትምህርት ቤት መምህር መሆኑንም ጨምሬ ገለጽኩለት፡፡
ተማም በጣም ተገረመ፡፡ ‹‹አልሸባብ ሀብታሙን ቢያገኘው ኖሮ ይገድለው ነበር፡፡›› ሲል ከተናገረ በኋላም ለአምስት ደቂቃ ገደማ ያህል ከልቡ እንባው እየመጣ ጭምር ሳቀ፡፡ ተማምን ሳውቀው እንዲህ ለደቂቃዎች ያልተቋረጠ ሳቅ ሲስቅ ለመጀመሪዬ ስለነበረ በአግራሞት መመልከቴ አልቀረም፡፡ በእውነተኛ ሳቁ ውስጥ የተፈጠሩትን እንባዎች በጃኬቱ እስከመጥረግ ደረሰ፡፡ የተማም ሁለተኛ ልጅ የሆነው መሃመድ ከሳሎን ወጥቶ እኛ የተቀመጥንበት በረንዳ ድረስ መጥቶ ‹‹አባዬ ምንድን ነው እንዲህ ያሳቀህ? ንገረኝ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ እነግርሃለሁ ብሎት ወደቤት ውስጥ ገባ፡፡
ከአግራሞቱ እና ከሳቁ መለስ ሲልም ‹‹ይሄ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ድራማ ነው›› ብሎ ከእስር እና ክስ ጋር የተገኛኙ ኢትዮጵያዊ ሁነቶችን ከሙያው አኳያ ያስረዳኝ ጀመር፡፡
የሆነ ሆኖ፣ በሀገራችን ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ዘወትር መመልከት አንዱ ልምዳችን ሆኗል፡፡ ለማንኛውም ነገ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥልጣን ዘመናቸው የኢትዮጵያን ምድር የሚረግጡት ፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝታቸውን በሰላም ጨርሰው ወደሃገራቸው ይመለሱና ወዳጆቻችን እነ ሀብታሙ ምናለ፣ ፍቃዱ በቀለ (ፍቄ) ሌሎችም ከእስር ተፈትተው እናግኛቸው፡፡ መሻቴ ይሄው ነው!!!