ቀን:- 19/10/2007
ቁጥር:- መድረክ/141/2007
ግልጽ ደብዳቤ
ለክቡር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ክቡር ሆይ!
ሀገራችን ኢትዮጵያ በፊውዳል አስገባሪዎችና የእነርሱ የበላይ ጠባቂ በሆኑ አፄዎች፣ ቀጥሎም በአምባገነን ወታደራዊ ጁንታ ሲትገዛ ሕዝባችን ኑሮውን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገፋ ቆይቶ፣ በ1983 ዓ ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከደርግ የባሰ አይመጣም የሚል ብሩህ ተስፋ የሰነቀው አብዘኛው ሕዝባችን ኢህአዴግን በቀና መንፈስ ተቀብሎት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢህአዴግም እንደዛሬው ስልጣኑን ባላደላደለበትና ከእኔ ወዲያ ለዚህች ሀገር አሳቢና ተቆርቋሪ የለም ባላለበት በዚያን ወቅት መድበለ-ፓርቲ ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረትና ባደረገው ጥሪ የተደራጁና ያልተደራጁ የኢትዮጵያ ዴሞክራቶች፣ በኢህአዴግ ከተገለሉት በስተቀር፣ ጥሪውን ተቀብለው በመሰባሰብ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ጥረት ለማገዝ ደፋ ቀና ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ኢህአዴግ ከዴሞክራሲ ፈለግ እየወጣ እንደሆነ የተገነዘቡ አንዳንድ ድርጅቶች ባነሱዋቸው ጥያቄዎች ምክንያት ከሽግግሩ መንግሥት ተገፍተው ለመውጣት በመገደዳቸው፣ በኢትዮጵያ የመቻቻል ፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጥያቄ ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ መሆኑ፣እንኳን ለፖለቲከኞቹ ከተራው ዜጋም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር ኢህአዴግ ራሱ ባወጣው ሕገ-መንግስት ተጠቅመን የዴሞክራሲ ትግላችንን እንቀጥላለን ያለነውና በአሁኑ ወቅት በመድረክ ሥር የተሰባሰብነው የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ በእልህ አስጨራሽ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም በመታገል ላይ እንገኛለን፡፡
ሆኖም፣ ይህ የመድረክ አስተሳሰብና መልካም አካሄድ በኢህአዴግ ዘንድ ምንም ዋጋ ባይሰጠውም፣ እኛ ለሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚበጀው ይኸው ሰላማዊ የትግል ስልት መሆኑን አጥብቀን ስለምናምን እያካሄድን ያለነው ጥረቶቻችን ከፍተኛ አደጋ ባጋጠሟቸው ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ሕዝባችን በኢህአዴግና በኢህአዴግ መራሹ መንግስት እየተዋከበ፣ እየታሰረና እየተገደለ ትግላችንን ሲደግፍ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህን ፀረ-ሕዝብ ድርጊቶች እየተቋቋመ በየምርጫው ወቅት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ቀንና ከዚያም በኋላ የሚሰጠንን ድጋፍ ነፍጎን አያውቅም፡፡ ይህ የሕዝባችን ድጋፍ ዘንድሮም በቅድመ ምርጫ ወቅት ባካሄድናቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች በገሃድ ታይቷል፣ በምርጫው ዕለትም ድምፁን ለመድረክ ለመስጠት ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል አስመስክሯል፡፡
ከዚህ ገሃድ እውነታ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ15/10/2007 ዓ ም ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ኢህአዴግ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በ100 ፐርሰንት ማሸነፉን ማሳወቁን ሰፊው መራጩ ሕዝባችን ያልተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ መድረክም አልተቀበለውም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በየክልሎቹ በአሁኑ ወቅት በሕዝባችን ላይ መድረክን መርጣችኋል በማለት የኢህአዴግ ካድሬዎችና የመንግስት ታጣቂዎች የሚፈጽሙትን ወከባ፣ እስራትና ግዲያ እንዲያስቆሙልን ላቀረብንለት ጥያቄ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡ ችግሩ ዛሬም በስፋት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ለአብነት ያህልም፡-
1- በኦሮሚያ ክልል በምርጫው ዕለት በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አቶ ጊዲሳ ጨመዳ እና በምዕራብ አርሲ ዞን፣ አቶ ገቢ ጥሴጎ የተባሉ ሁለት አባሎቻችን ሲገደሉ በርካታ አባሎቻችን በየፖሊስ ጣቢያውና በየወህኒ ቤቱ ታጉረዋል፡፡
2- በትግራይ ክልል በምዕራብ ትግራይ ዞን፣ የአረና/መድረክ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና የ2007 ዓ ም ምርጫን በዞኑ ሲያስተባብሩና ጉልህ ሚና ሲጫወቱ የነበሩት የአመራር አባላችን አቶ ታደሰ አብርሃ አርአያ ከምርጫው በኋላ የተገደሉ ሲሆን፣ በዚሁ ክልል ወከባው፣ ማሳደዱና እስራቱ በከፍተኛ ሁኔታ እስከአሁንም ቀጥሏል፡፡
3- በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሀዲያ ዞን በሶሮ ወረዳ፣ አቶ ብርሃኑ ኤረቦ የተባሉ ተዘዋዋሪ የምርጫ ተወካያችንም ከምርጫው በኋላ በስም ተለይተው በሚታወቁ ሁለት ፖሊሶች ሲገደሉ ሌሎች በየገበሬ ማሕበር ጣቢያዎችና ፖሊስ ጣቢያዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየተያዙና እየታጎሩ ናቸው፡፡
4- በርካታ ለዕጩነት ያቀረብናቸው ተወዳዳሪዎቻችንና የምርጫ ጣቢያ ተወካዮቻችን ካለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስርና ለእንግልት በፖሊስ እንደሚፈለጉ ስለታወቀ ቤት ንብረታቸውን በመተው ለስደት ኑሮ እየተዳረጉ ናቸው፡፡
5- በርካታ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ዕጩ ተወዳዳሪዎቻችንና የምርጫ ጣቢያ ተወካዮቻችን ደሞዛቸው ታግዷል፣ብዙዎቹም ከሥራ እየተባረሩ ይገኛሉ፡፡
6- በብዙ አከባቢዎችም በተወካዮቻችን ላይ ድብደባ፣ የግዲያ ሙከራና ከቤት ንብረት የማፈናቀል እርምጃዎች እየተወሰዱባቸው ነው፡፡
7- መድረክን የመረጠው ሕዝባችን የሴፍቲ-ኔት ድጋፍ በመነፈግና ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመከልከል ለረዥም አመታት የኖሩባቸውን ቤቶች በማፍረስና የንግድ ተቋማቸውን በመዝጋት ወዘተ ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ነው፡፡
እነዚህ መጠነሰፊ በደሎች ሕዝባችንን በእጅጉ አስከፍተዋል፡፡ የምርጫ ውጤት ተብሎ በቦርዱ ይፋ የተደረገው መግለጫም ታዓማኒነት የሌለው በመሆኑ ይበልጡን ሕዝባችንን በሥርዓቱ ላይ እምነት አሳጥቷል፡፡ በሀገራችን የምርጫ ፖለቲካ አሁን ወደ ደረሰበት አስከፊ ደረጃ እንዳይደርስ መላ ለመፈለግ መድረክ ክብርነትዎ ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ ም በጽ/ቤትዎ በሰጡት መግለጫ፣ በተለይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ስለሚደረግ ምክክርና ውይይት ጉዳይ በተናገሩት ውስጥ “ቢሮአችን ሁልጊዜ ክፍት ነው፣ ለጋራ ሀገራችን በጋራ እንወያይ የሚል ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ” በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በደስታና በአክብሮት በመቀበል በ7/5/2007 በቁጥር መድረክ/019/2007 በተጻፈ ደብዳቤ ፣ መድረክ ቀጠሮ ጠይቆ እንደነበር ማስታወስ እንወዳለን፡፡ ሆኖም ለዚህ የመድረክ ሀገራዊና ሕዝባዊ ዓላማ የተላበሰ ቅን ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥ መታለፉም ላለንበት አስከፊ ሁኔታ አስተዋፆ እንዳለው ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ስለዚህ ክብርነትዎ ባለብዎት ከፍተኛ ኃላፊነት ይህን “ኢህአዴግን አልመረጣችሁም” በማለት በሕገወጥነት በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በአስቸኳይ በማስቆም ኃላፊነትዎን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አበክሮ ይጠይቃል፡፡
ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህንን ህገ-ወጥ ተግባር በማስቆም ረገድ የበኩላቸውን እርምጃ እንዲወስዱ ሀገራዊና ሕዝባዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
` ከሰላምታ ጋር
በየነ ጰጥሮስ (ፕ/ር)
የመድረክ ሊቀመንበር
ግልባጭ፡-
– ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ
– ለኢፌዴሪ የሕዝብ ዕምባ ጠባቂ
– ለኢፌዴሪ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፡፡