ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ንግግር ያደረጉ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ባራክ ኦባማ፣ ዴሞክራሲ ማለት ምርጫ ማካሄድ ብቻ አለመሆኑን ገለጹ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ 48 ደቂቃ ያህል
በፈጀው ንግግራቸው፣ አፍሪካ እያሳየች ያለው ለውጥ በዴሞክራሲ ላይም የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በከፍተኛ ጭብጨባ እየታጀቡ ባደረጉት ንግግር የእውነተኛ ዴሞክራሲ መገለጫ የሆኑት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብና የሚዲያ ነፃነት ሁለንተናዊ መብቶችና በአፍሪካ አገሮች ሕገ መንግሥትም የሰፈሩ በመሆናቸው፣ የአኅጉሪቱ ሕዝቦችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ዴሞክራሲ ሥር እየሰደደባቸው ናቸው ያሏቸውን ሴራሊዮን፣ ጋና፣ ቤኒን፣ ቦትስዋና፣ ናሚቢያና ደቡብ አፍሪካን ጠቅሰዋል፡፡ በናይጄሪያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ድምፅ ሰጥቶ ሥልጣን በሰላም ለተቃዋሚ ፓርቲ የተሸጋገረበትን ሒደትም አድንቀዋል፡፡
‹‹በዚሁ ወቅት ይህ ተመሳሳይ መብት ለሌሎች አፍሪካውያን ተነፍጓል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ‹‹ዴሞክራሲ ማለት ምርጫ ማካሄድ ማለት ብቻ አይደለም፤›› በማለት አክለዋል፡፡
‹‹ጋዜጠኞች ሥራቸውን ስለሠሩ ብቻ እስር ቤት ከተወረወሩ፣ የመብት ተሟጋቾች ጫና ከተደረገባቸው፣ ሲቪክ ማኅበራትን መንግሥት ካኮላሸ፣ ዴሞክራሲው የይስሙላ እንጂ እውነተኛ አይደለም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ ከፍተኛ ጭብጨባና ጩኸት ከታዳሚው ተችሯቸዋል፡፡
ከአራት ሰዓታት በላይ በአፍሪካ ኅብረት በትዕግሥት ሲጠብቋቸው ከነበሩ ታዳሚዎች መካከል የአፍሪካ አገሮች ልዑካንና አምባሳደሮች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የሃይማኖት መሪዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ኢትዮጵያን በተመለከተ በአገሪቱ በተሠሩት ሥራዎች መደነቃቸውን ገልጸው፣ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡
‹‹ሆኖም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር እንደተነጋገርኩትም ይህ የዴሞክራሲ መነሻ ነው፤›› ያሉት ኦባማ፣ ‹‹ጋዜጠኞች ላይ ዕቀባ ከተጣለ፣ ሕጋዊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ማድረግ ካልቻሉ፣ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን ዕምቅ አቅም በሙሉ ኃይል መጠቀም አያስችላትም፤›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ዴሞክራሲ እንድትገነባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጭምር ብዙ መሠራት እንዳለበት እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ ዴሞክራሲ ከሁለት ምዕተ ዓመታት ግንባታም በኋላ ፍፁም እንዳልሆነ ያመኑት ፕሬዚዳንቱ፣ አገራቸው ግን የዴሞክራሲ ሥርዓቷን ለማዳበር በተከታታይ በሀቅ መሥራቷ ጥንካሬዋ ነው ብለዋል፡፡
ዜጐች መብታቸውን ከተነፈጉ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን ዓለም ሁሉ ለእነዚህ ዜጐች ሊቆም ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ምቹ ባይሆንምና የአሜሪካ አጋር አገሮችን ባያስደስትም፣ አገራቸው ለእነዚህ እሴቶች ከመቆም ወደኋላ እንደማትል አስረድተዋል፡፡
‹‹አውቃለሁ አንዳንድ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን ይመርጣሉ፡፡ እንደዚያ መሆኑም ለአንዳንድ መሪዎች ምቾትን ሊሰጥ ይችላል፤›› ያሉት ኦባማ ታዳሚዎችን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡
ነገር ግን አሜሪካ በዴሞክራሲ ዙሪያ የምታራምደው አቋም ራሷ ከትችት ነፃ ስለሆነች፣ አልያም ሁሉም አገሮች አሜሪካ በሄደችበት መንገድ ይሂዱ ከሚል አስተሳሰብ የሚነሳ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡
‹‹ዘራችን ከአፍሪካ ለሚመዘዝ ኢፍትሐዊነት ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ መገለል ምን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ መታሰር ምን እንደሆነ አይተነዋል፡፡ ታዲያ ሌሎች ላይ ይህ ሲፈጸም እንዴት ዝም ብለን እናያለን?›› ሲሉ ከፍተኛ የድጋፍ ጭብጨባ ተደርጐላቸዋል፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ ሁሉም ድምፃቸውን ሊያሰሙ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ኦባማ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ የምዕራባውያን እሳቤ ሳይሆን የሰብዓዊነት እሳቤ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሌላኛው ለአፍሪካ ለውጥ አደጋ የአኅጉሪቱ መሪዎች የሥልጣን ዘመናቸው ሲጠናቀቅ ሥልጣን ለመልቀቅ አለመፈለጋቸው ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህን ጉዳይ ‹‹ለእኔ አይገባኝም›› ብለዋል፡፡
‹‹እኔ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመኔ ላይ ነኝ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኜ ማገልገሌ ለእኔ እጅግ ታላቅ ክብር ነው፡፡ ለእኔ ከዚህ የበለጠ ክብር ወይም የሚያስደስት ሥራ የለም፡፡ ሥራዬን እወደዋለሁ፡፡ ነገር ግን በእኛ ሕገ መንግሥት መሠረት ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር አልችልም፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡
የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ኑሮአቸውን ለመግፋት እንደሚጓጉ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ በዚህም ጊዜ ለአገራቸው የተለየ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ ለቤተሰቦቻቸው ጊዜ መስጠትና አፍሪካን መጐብኘት ያለ ደኅንነት ግርግር ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸው ነገሮች እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
‹‹ለዚህ ነው ለምን መሪዎች ለረጅም ዘመን ሥልጣን ላይ መቆየት የመፈለጋቸው ሚስጥር የማይገባኝ፣ በተለይ ብዙ ገንዘብ እያላቸው፤›› ሲሉ በአዳራሹ ከሳቅ ጋር የታጀበ ከፍተኛ ጭብጨባ ተችሯቸዋል፡፡
‹‹አንዳንድ ጊዜ መሪዎች እኔ ከሌለሁ አገራቸው መቀጠል እንደማትችል ሲናገሩ ይሰማል፤›› ያሉት ኦባማ፣ ‹‹ይህ አባባላቸው እውነት ከሆነ በመሪነት ዘመናቸው በአገር ግንባታ ውጤታማ ሥራ አልሠሩም ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የሚታወሱት በሥልጣን ዘመናቸው በሠሩት ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ የሥልጣን ዘመናቸው ሲጠናቀቅ የሥልጣን ሽግግር በሰላም በመጠናቀቁ እንደሆነም ፕሬዚዳንት ኦባማ አስታውሰዋል፡፡
መሪዎች በሥልጣን ለመቆየት ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ የጨዋታውን ሕግ መቀየራቸው አለመረጋጋትን እንደሚፈጥር፣ በቅርቡ በብሩንዲ የተከሰተውን ችግር እንደ ማሳያ አቅርበዋል፡፡
‹‹እኔ አሁንም ወጣት ነኝ፡፡ ደግሜ ብወዳደር እንደማሸንፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን አዲስ ጉልበትና ሐሳብ ይዞ የሚመጣ ሌላ አካል ለአገሬ እንደሚጠቅም አውቃለሁ፡፡ ለእናንተም ይህን ማድረግ ጥሩ ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት በመፈንቅለ መንግሥት የሥልጣን ሽግግር ሲደረግ እንደሚያወግዘው፣ መሪዎች ከተቀመጠላቸው የሥልጣን ዘመን በላይ ለመሥራት ሲሞክሩም ጠንካራ ድምፁን ሊያሰማ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ አሳስበዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ኦባማ ታሪካዊ ንግግር በኅብረቱ አዳራሽ አንደኛና ሁለተኛ ባልኮኒ ላይ ታድመው በነበሩ ወጣቶች ከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱም ንግግራቸውን ከማድረጋቸው በፊትም ሆነ በኋላ እነዚህን ታዳሚዎች እጃቸውን በማውለብለብ አመስግነዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከዴሞክራሲ ባሻገር በአሜሪካና በአፍሪካ ንግድ ግንኙነት፣ በሙስና፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላምና በፀጥታ እንዲሁም በሽብርተኝነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
በአፍሪካ ኅብረት በተደረገው የፕሬዚዳንት ኦባማ ንግግር ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ተገኝተዋል፡፡