የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉብኝት ባደረጉበት በዚህ ሳምንት፣ በአገራቸው አንድ ፍርድ ቤት ኢትዮጵያን ባልተፈቀደ ስለላ የሚወነጅል ክስ መቅረቡ ተሰማ፡፡
በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነ ኪዳኔ በተባለ በሜሪላንድ የሚኖር ግለሰብ ላይ የስካይፒና የኢንተርኔት የስልክ ልውውጦችን በመጥለፍ፣ እንዲሁም ቤተሰቦቹ በኢንተርኔት የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በድብቅ ለወራት በመከታተል ወንጀል በመጠርጠር ነው በኢትዮጵያ ላይ ክስ የቀረበባት፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያ መንግሥት በወንጀል እንደማይፈለግ የሚጠቅሰው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ግንቦት ሰባት የተባለ ቡድን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚሰጥ ያትታል፡፡
ግለሰቡ በኢትዮጵያ መንግሥት ዓይን ውስጥ የገባበት ምክንያትም ይህ ሊሆን እንደሚችል ዘገባው ያስረዳል፡፡
የተበዳይ የሕግ አማካሪ የሆነው ኤሌክትሮኒክ ፍሮንቲየር ፋውንዴሽን ተወካይ ሚስተር ናት ካርዶዞ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ የሆነውን ግለሰብ ኮምፒውተር የስካይፒ የስልክ ጥሪዎችን ሲቀዳ እንደነበረ፣ የግለሰቡን የኢሜል ልውውጦች ኮፒ ያደርግ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበበት ክስ ውድቅ እንዲሆን መጠየቁን፣ ለዚህም ያለመከሰስ መብት እንዳለው በምክንያትነት መጥቀሱን ዘገባው ያስረዳል፡፡
ይሁን እንጂ የቀረበው ክስ ውድቅ አልተደረገም፡፡ ይልቁንም ፍርድ ቤቱ አንድ የውጭ አገር መንግሥት በአሜሪካዊ ግለሰብ ላይ የኤሌክትሮኒክ ስለላ ያለፈቃድ ማድረግ ይችላል ወይ የሚለውን እየተመለከተ መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡
የተበዳይ የሕግ የሕግ አማካሪ ድርጅት በሰጠው አስተያየት፣ ማንም ይሁን ማን የፍርድ ቤት ፈቃድ ሳያገኝ የግለሰቦችን የስልክ ግንኙነት መጥለፍ ይቻላል ወይ የሚለውን ለመመለስ የሚረዳ ጥሩ የሕግ ክርክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት የስለላ ተግባር ለማከናወን እንዲረዳው ሐኪንግ ቲም ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ በ330 ሺሕ ዶላር ሶፍትዌር መግዛቱን፣ ሰሞኑን ዊኪሊክስ የተባለው መረጃ አፈትላኪ ተቋም ይፋ ማድረጉ በዘገባው ተካቷል፡፡