29 JULY 2015
ተጻፈ በ 

የግሉ ሚዲያ አይጨፍለቅ!

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ፕሬዚዳንት ኦባማ ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት

በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያሉት ሚዲያዎች የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ስላለባቸው፣ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ሥልጠና እንዲሰጡዋቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አንድ ቋት ውስጥ ከቶ የመጨፍለቅ አስተያየት ዕርምት ያስፈልገዋል፡፡ ለዕርምት የሚረዱ ዋና ዋና የሚባሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት የግድ ይለናል፡፡

1.ለግሉ ሚዲያ የተመቸ ምኅዳር የለም

ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት በእጅጉ ከሚተችባቸው ዋነኛ ችግሮቹ መካከል በተለይ ለግሉ ሚዲያ ተገቢውን ዕውቅና ሰጥቶ፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን የፕሬስ ነፃነት ያለማክበር ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ቃል በቃል የተተረጎመው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 (Article 19) ሲሆን፣ መንግሥት በማናቸውም ሁኔታ በፕሬስ ነፃነት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ የሚያደርገው ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን የሚፈታተኑ በርካታ ችግሮችን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በአንድ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች የነበሩባት አገር፣ በአሁኑ ወቅት ባዶዋን ቀርታለች ቢባል ማን ሊያስተባብል ይችላል? በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በቀን ከ30 በላይ የፕሬስ ውጤቶች እንዳልነበሩ፣ አሁን በሳምንት ከሁለት የእጅ ጣቶች የሚያንሱ ናቸው የቀሩት፡፡ ከዚያ አልፎ ተርፎ ‹በሥራቸው ምክንያት አይደለም› እየተባለ የሚታሰሩትና በፍርኃት እየተሰደዱ ያሉት ጋዜጠኞች ጉዳይ ምንን ያመላክታል? የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ሲነሳ የፕሬስ ነፃነት በዋና አጋፋሪነት የሚቀርበው እኮ የሚዲያ ምኅዳሩ አመቺ ባለመሆኑ ነው፡፡

በተለይ የግሉ ሚዲያ በውስጡ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም በአመዛኙ ግን የሚበረታው ከውጭ ያለበት ጫና ነው፡፡ የመንግሥት ጫና፡፡ መንግሥት የግሉን ሚዲያ አቅም ለመገንባት ቀርቶ እንደ ባላንጣ በሚያይበት አገር ውስጥ፣ ሚዲያዎች የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ይታይባቸዋል ሲል ለመቀበል በጣም ይከብዳል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በጣም ያሳዝናል፡፡ መንግሥት ጠጋ ብሎ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ከሚጥር ይልቅ፣ ቢኖሩም ባይኖሩም አይጠቅሙም የሚልበት አገር መሆኑ እንዴት ይረሳል? የሙያ የሥነ ምግባር ችግር አለ ሲባልስ ሁሉንም አንድ ላይ አጠቃሎ የያዘ ችግር ነው ወይ? ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ የግል ሚዲያዎች በጣም በማይመች ምኅዳር ውስጥ እየሠሩ እንደሆነ ለማንም ነጋሪ አያሻውም፡፡

የግሉ ፕሬስ በመንግሥት በኩል የተሰጠው ዕውቅና እጅግ በጣም የወረደ ከመሆኑ የተነሳ፣ ኢንቨስትመንት የማይስብ ብቸኛው ዘርፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥት በበጎ የማያየውን ደግሞ ማንም ሊጠጋው አይፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የግሉ ሚዲያና የጎዳና ላይ ንግድ አንድ ዓይነት ናቸው የሚባልበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ለሙያ ፍቅር የሚሠራበት እንጂ ለኑሮም ለጤናም ተስማሚ ያልሆነ ነው፡፡ ሌሎች የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፎች የግብር እፎይታና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ሲያገኙ ለሚዲያ ሥራ የሚያገለግሉ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ይህንን ዕድል ተጠቅሞ ለማስገባት የሚፈቅድ የለም፡፡ በየጊዜው በሚንረው ሰው ሠራሽ የኅትመት ዋጋ ጭማሪ ምክንያት የግሉ ሚዲያ ህልውናው የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ነው ያለው፡፡ በሰባራና ሰንካላ ምክንያቶች ኅትመት ለቀናት ሲዘገይ ምንድነው ችግሩ ብሎ የሚጠይቅ ባለሥልጣን እንኳን የለም፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ሚዲያው በነፃነት የመዘገብ ዕድሉ በችግሮች የተሞላ ነው፡፡ የመረጃ ነፃነት አዋጁ ወጥቶ ዓመታት እየተቆጠሩ የመንግሥትን መረጃ ማግኘት የወርቅ ማዕድን ከመቆፈር አይተናነስም፡፡ በጣም ጥቂት ሚዲያዎች ያሉትን ጫናዎች በሙሉ ተቋቁመው የሙያ ሥነ ምግባሩን ጠብቀው ለመሥራት የሚያደርጉት ጥረት መከራ የተሞላበት ነው፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን አክብሮና አስከብሮ የሙያ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ ዘመናዊ ሚዲያ እንዲፈጠር መሥራት ሲገባው፣ ራሱ ጠልፎ ጥሎ የሙያ ሥነ ምግባር ችግር አለ ሲል ከማስረገም አልፎ በጣም ያስከፋል፡፡ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡

2.የሚዲያው ስታንዳርድ እንዴት ነው የሚለካው?

መንግሥት በልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለሙ ምክንያት በዓለም ላይ ታዋቂ ከሆነው የምርመራ ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) ይልቅ፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነት (Developmental Journalism) ላይ ነው ትኩረቱ ያለው፡፡ ለዚህም ዓላማው ስኬት በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በልማታዊ ጋዜጠኝነት አቅጣጫ የተቃኘ ትምህርት በማስረፅ ላይ ነው፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉት ሚዲያዎች በሙሉ በዚህ ዓላማ ሥር ሆነው የአፈ ቀላጤነት ተግባር እያከናወኑ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ ዕለት ጥያቄው የተነሳላቸው ከአሜሪካ በመጣ በሊበራሊዝም ቅኝት በሚሠራ ጋዜጠኛ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ የገጠመውን ችግር አውስቶ ‹‹መንግሥት ከነፃው ፕሬስ ጋር ምንድነው ችግሩ?›› ሲላቸው፣ እንደ ሰብዓዊ መብት ችግሩ ሁሉ አንዳንድ ምክንያቶችን ሳይጠቅሱ በአገሪቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው እየሠሩ ያሉ ሚዲያዎችን አንድ ቋት ውስጥ ነው የከተቱት፡፡ የሁሉንም ችግር የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ነው ያደረጉት፡፡ በልማታዊ ጋዜጠኝነት መርህ የራሱን ሚዲያዎች እየመራ ያለ መንግሥት ለግሉ ሚዲያ ‹‹የኒዮ ሊበራል›› ሚዲያውን ለፈውስነት ሲፈልግ እጅግ በጣም ያስገርማል፡፡ መንግሥት በአደባባይ ራሱን ሊወቅስበት የሚገባውን ሸፍኖ ሚዲያውን በሙያ ሥነ ምግባር ችግር መክሰሱ ያሳዝናል፡፡

የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ በትምህርት ዝግጅት፣ በልምድና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ መሆኑ ባይካድም፣ ለኢትዮጵያ የግል ሚዲያ አሠልጣኝ መሆን አይችልም እንላለን፡፡ ከተፈለገም የልምድ መለዋወጡ በራስ ፈቃድና ጊዜ የሚከናወን ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት 24 ዓመታት አገሪቱን ሲያስተዳድር ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ አሁንም ገና ይቀረኛል ቢልም፣ ቢያንስ አሁን በሥራ ላይ ያሉት የግል ሚዲያዎች ራሳቸውን ከምዕራባውያን ደረጃ በታች አድርገው አይቆጥሩም፡፡ ልዩነቱ የሀብትና የነፃነት ካልሆነ በስተቀር ከአንድ ምንጭ የሚቀዳው ሙያና ሥነ ምግባር ግን አንድ ያደርጋቸዋል ተብሎ በጥብቅ ይታመናል፡፡ በዚህ ጊዜ የሙያ ስታንዳርዱ መለካት ያለበት በዚህ ደረጃ ነው እንጂ፣ የምዕራባውያን ሚዲያዎች እንዲያሠለጥኑ የሚል የሐኪም ትዕዛዝ ዓይነት መሆን የለበትም፡፡

3.አሁንም የፕሬስ ነፃነት ይከበር

ሁሌም አበክረን የምናሳስበው ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ ይሰጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይከበር፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የወጡ ሕጎች ይከበሩ፡፡ በአገራችን በተደጋጋሚ በሚታየው የሕግ አወጣጥ ችግር ምክንያት የፕሬስ ነፃነትን ሊጋፉ የሚችሉ አንቀጾች (በተለይ በመገናኛ ብዙኃንና በመረጃ ነፃነት አዋጁ) ይመርመሩ፡፡ ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ከመንግሥት ጋር የማያስማማቸው ጉዳይ ሰበብ አይፈለግለት፡፡ አገሪቱ በጋዜጠኛ አሳሪ አገሮች ተርታ ግንባር ቀደም ተብላ ስሟ እየተብጠለጠለና በርካታ ጋዜጠኞች ከአገራቸው ተሰደው እያለ፣ ችግሮችን መርምሮ መፍትሔ መፈለግ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ መንግሥት ዲሞክራሲንና ሰብዓዊ መብትን ለማክበር 24 ዓመታት ካልበቁት፣ ጋዜጠኝነት አካባቢ ችግር ቢኖርስ ምን ይገርማል? የችግሩ አካል ያልሆነው መንግሥት ለመፍትሔው የምዕራባውያን ጋዜጠኞችን መካሪነትና አሠልጣኝነት ሲሻ ከእንቆቅልሽ በላይ ነው የሚሆነው፡፡

የፕሬስ ነፃነት ይከበር ሲባል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምሰሶ ከሆኑት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ አፅንኦት ይሰጠው ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ነፃነት አሳሳቢነት ሲነሳላቸው የመንግሥትን ችግሮች ረስተው፣ የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለትን እንደ ምክንያት ማንሳት አልነበረባቸውም፡፡ በእርግጥም በአገራችን የግል ሚዲያ ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባር ችግር የለም በማለት ማንም ደፍሮ መከራከር አይችልም፡፡ ነገር ግን የችግሮቹ አልፋና ኦሜጋ የሙያ ሥነ ምግባር ሆኖ ሲወሰድ ግን ልክ አይደለም፣ እውነትም አይደለም፣ ማለት ግዴታችን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሁሉንም አንድ ላይ ጨፍልቆ ለግሉ ሚዲያ የተለየ ምሥል መስጠት ተገቢ አይደለም!

Leave a Reply