Wednesday, 29 July 2015 17:02
44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሁለቱን የምስራቅ አፍሪካ አገራት መጎብኘታቸውን ተከትሎ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዐይን እና ጆሮዋቸውን ወደ ሁለቱ አገራት (ኢትዮጵያ እና ኬኒያ) ሆኗል። ታላላቆቹ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት እና ፕሬዚዳንቱ በሚጎበኟቸው አገራት ያሉትን ጆሮ ገብ መረጃዎች ሰባስበው ለአድማጭና ተመልካች የሚያደርሱ ዘጋቢዎቻቸውን ልከዋል። ዘጋቢዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ከላኩ መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ አልጄዚራ ሲሆን የአልጄዚራ ዘጋቢው መሀመድ የሱፍ የኦባማን ኢትዮጵያ መግባት አመልክቶ “ባራክ ኦባማ መቶ ፐርሰንት ምርጫ ያሸነፈውን መንግስት አገኙ” ሲል በስላቅ ገልጾታል። ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት እና ሂደት ላይ አገር ውስጥ የሚገኙም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ሲተቹት እንደነበረ ይታወሳል።
በሶስተኛው ዓለም በተለይም በአፍሪካ የሚካሄዱ ምርጫዎች ምንጊዜም በውጥረት ተካሂደው በግጭት ሲጠናቀቁ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም። በአህጉሪቱ ስልጣን ላይ የሚወጡ መንግስታት በሚከተሏቸው አምባገነናዊ አስተዳደር ስርዓቶች የተነሳ ከህዝባቸው ጋር የማይገናኙ ሲሆን በየአምስት ዓመቱ(እንደየአገሮቻቸው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት) በሚያካሂዷቸው ምርጫዎች ላይም ውዝግብ አይጠፋም። ለአብነት ያህል አስረጅ ሁነቶችን ማስቀመጥ ቢያስፈልግ እንኳ በ2015 ብቻ ከተካሄዱት 11 የአፍሪካ ምርጫዎች መካከል በብሩንዲ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተካሄዱት ምርጫዎች ፍጻሜያቸውም ሆነ ጅማሬያቸው በውዝግብ የታጀበ ነው። በሶስቱም አገራት ለተካሄዱት ምርጫዎች ከጅማሬያቸው እስከ ፍጻሜያቸው በውዝግብ ታጅበው እንዲጠናቀቁ ያደረጋቸው በየአገራቱ የሚገኙ ገዥዎች (በሱዳን ፕሬዚዳንት ኡመር አልበሽር፣ በብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፔይር ንኩሪንዚዛ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ኢህአዴግ) ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው የሚወዳደሩበትን ሜዳ ምቹ ባለማድረጋቸው መሆኑን ከላይ የገለጽኳቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማት ሲገልጹ ይሰማል።
አፍሪካን ሪሰርች ኢንስቲትዩት በድረ ገጹ እንዳስነበበው በዚህ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከተካሄዱት ምርጫዎች መካከል በስኬት የተጠናቀቀውና ሰላማዊ የስልጣን ልውውጥ የተካሄደው በናይጄሪያ እና በሌሴቶ የተካሄዱት ምርጫዎች ብቻ ናቸው። በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተካሄዱትን ምርጫዎች ደግሞ በገዥዎቹ ፓርቲዎች ፍጹም የበላይነት የተጠናቀቁ መሆናቸውን አስታውቋል። አፍሪካን ሪሰርች ኢንስቲትዩትም ሆነ የተለያዩ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትችት ከሰነዘሩበት አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የሚወጡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቤቱታ ግን “በምርጫው ለምን ተሳተፍን? ቢቀርብን ይሻላል አባሎቻችንን፣ ደጋፊዎቻችንን እና አመራሮቻችን ለእስር፣ ለድብደባ እና ለሞት ዳርገናቸዋል” ሲሉ ይናገራሉ።
የፓርቲዎቹ አቤቱታ እና የቅሬታቸው አስረጅ አመክንዮ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በትራይይ ክልል በድምሩ አምስት ኣባሎቼ በገዥው ፓርቲ የደህንነት አባላት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ከዚህ በላይ ደግሞ በርካታ አባሎቼ ለእስር ተዳርገዋል” ያለ ሲሆን በተመሳሳይ ቀን መግለጫ ያወጣው ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ “ከምርጫው ማግስት ጀምሮ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ያካሂዱ የነበሩ አባሎችን ከስራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሳደድ እና መግደል የአገዛዙ ዋና መገለጫ ሆኗል” ሲል መግለጹ ይታወሳል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ደግሞ በአባሎቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው አፈና እና እስራት ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የገለጹት። በተለይ መኢአድ በአሁኑ ወቅት 132 ኣባሎቹ በመላው አገሪቱ ታስረው እንደሚገኙ አስታውቋል።
የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት ሚንስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ በበኩላቸው “በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ አይነት አቤቱታዎች ፎርማል በሆነ መንገድ አልቀረበልንም። ሌላው ማንመ ሰው በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት የሚታሰር የሚገደል የሚሰደድበት ዘመን አብቅቷል። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ፈጽሞ በሀገራችን ውስጥ የለም። የፓርቲዎቹ አቤቱታም የስም ማጥፋት ዘመቻ አንዱ አካል ነው” ብለዋል። አቶ እውነቱ አያይዘውም “ደብረ ማርቆስ ላይ የሞተው ግለሰብ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ስለነበረ ነገር ግን አገዳደሉ የተፈጸመው ፈጽሞ ከፖለቲካ ጋር ትስስር የለውም። ከዚያ ባሻገር የሚነሱ ጉዳዮች ጥላሸት ለመቀባት፣ የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጠልሸት የሚደረግ ሩጫ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ቅሬታ የገዥው ፓርቲ የበታች ካድሬዎች የሚወስዷቸው ህግን ያልተከተሉ እርምጃዎች በአባሎቻችን ላይ በደል እያደረሰ ነው ይላሉ። ለመሆኑ ኢህአዴግ እንደ መንግስትም ሆነ እንደፓርቲ መዋቅሩ ሁሉንም አባሎቹንና ኃላፊዎቹን ተከታትሎ ይገመግማል ወይ? የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ የቀረበላቸው አቶ እውነቱ ሲመልሱ “ይህ ስርዓት (ኢህአዴግ መራሹ መንግስት) ህጋዊ ስርዓት ነው። ከታች ጀምሮ እስከላይ ድረስ በየተዋረዱ አደረጃጀትና የአሰራር መዋቅር ያለው፣ የታችኛው የአስተዳደር እርከን የተፈጸሙ በደሎች ካሉ ቀጣይ ካለው የአስተዳደር እርከን ጋር እየሄደ ይግባኝ የሚባልበት ስርዓት አለ። በአስተዳደር ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን በፍትህ ስርዓቱም እንደዛ ነው። ስለዚህ በህግና በስርዓት የሚመራ አገር እንጅ እንደሚባለው ዝም ተብሎ በአጋጣሚ በዘፈቀደ የሚዳኝበትና የሚመራበት አይደለም። የህዝብን መብት ማስከበር ሰብአዊ መብትን ማስከበር ገዥው ፓርቲ ዋናው አጀንዳው ነው። ነገር ግን ኢህአዴግ የመላዕክት ስብስብ ባለመሆኑ ክፍተቶችና ጉድለቶች የሉበትም አንልም። ክፍተቶችና ጉድለቶች ሲፈጠሩ በህጋዊ መንገድ ተከትሎ ነው ሊፈታ የሚገባው የሚል እምነት ነው ያለኝ” ሲሉ መልሰዋል።
የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ አበባው መሀሪ ግን “እስራት፣ ድብደባ እና ግድያ እየደረሰባቸው ያሉ አባሎቻችን በግል ባህሪያቸው ህግን ተላልፈው ወይም በደረቅ ወንጀል ሳይሆን በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ በመንግስት የደህንነት አባሎች ነው በደሉ እየተፈጸመባቸው ያለው” ሲሉ ይናገራሉ።
ከምርጫ ማግስት ለሚነሱ ውዝግቦች መነሻ ምክንያት
“ከምርጫ ማግስት የሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣሪው ምርጫ ቦርድ ሳይሆን የኢህአዴግ መዋቅር ነው” የሚሉት የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ዋሲሁን ታስፋዬ ናቸው። “ነገር ግን ምርጫ ቦርድ በተለይ በክልል እና በዞን ደረጃ የሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ የምርጫ ስርዓቱን በሚገባ እና በፍትሃዊነት ማካሄድ ስለማይችሉ ወይም ስለማይፈልጉ የምርጫን ውጤት ተከትሎ ችግር ይፈጠራል። አብዛኞቹ በግልጽ የኢህአዴግ አባል መሆናቸው እየታወቀ ነገር ግን የምርጫ አስፈጻሚ ሆነው ሲሰሩ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታ ሲቀርብለት መፍታት አይችልም” ብለዋል።
አቶ ዋሲሁን ከምርጫ ማግስት ጀምሮ በኢዴፓ ላይ ይህ ነው የሚባል የከፋ በደል አልደረሰበትም ያሉ ሲሆን “ይህ ሲባል ግን ፈጽሞ በፓርቲያችን ላይ ምንም አይነት በደል አልደረሰም ማለት አይደለም። በተለይ በአማራ ክልል ባህር ዳር ዙሪያ በፓርቲያችን አባሎች ላይ ለምን ተቃዋሚ ፓርቲ ሆናችሁ? በደጋፊዎቻችን ላይ ደግሞ ለምን ተቃዋሚዎችን ደገፋችሁ? እየተባሉ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል። እነዚያን ችግሮችም ፓርቲያችን በራሱ መንገድ ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” ብለዋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ከምርጫ በኋላ ለሚነሱ ውዝግቦች ምክንያቱ “መንግስት ስልጣኑን ለማስቀጠል ካለው ፍላጎት የተነሳ ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ ምርጫ በአገሪቱ እንዳይካሄድ ስለሚያደርግ ነው” ሲል ይገልጻል። ፓርቲው ከሳምንት በፊት አውጥቶት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ “በምርጫ ዋዜማ እና ማግስት በመግስት በኩል ከፍተኛ ወከባ እና ጫና ይበረክታል” ያለ ሲሆን በተለይ በተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የኢህአዴግን ፖሊሲ ተችተው በሚጽፉ ጋዜጠኞች እና መንግስትን በማይደግፉ ግለሰቦች ላይ ወከባ እና ጫናው ይፈጠራል። ይህ ደግሞ ከምርጫ ማግስት ለሚፈጠር ውዝግብ በር ይከፍታል” ብሏል።
ዓለም አቀፍ ትችቶች እና መነሻቸው
በአንድ አገር ለሚኖረው የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትም ሆነ ውርዴ መሆን ትልቁ ምክንያት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መስፈን እና የሰብአዊ መብት መከበር መሆኑን በርካታ የፖለቲካው ልሂቃን ይናገራሉ። በዚህ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ከትችት አላመለጠም። ሁለት ተከታታይ አገር አቀፍ ምርጫዎች የተመዘገበው ውጤት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአገሪቱ እየከሰመ መሄዱን ያሳያል ሲሉ ይናገራሉ። እቆረቆርለታለሁ የሚለውንና ማንም በክፉ እንዲያይብኝ አልፈልግም እያለ በአደባባይ የሚፎክርበትን ህገ መንግስት እንኳ ማክበር ተስኖት “ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ሲያፍን እና ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ ለእስር እና ለስደት የተዳረጉ ጋዜጠኞች አገር አድርጓታል” እያሉ ይተቹታል። በተለይ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በየዓመቱ የአገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ሲያቀርብ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የአገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ እየወረደ መሄዱን ይፋ አድርጓል።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በበኩሉ “ደሜ መራራ ሆኖ እንጂ ይህን ያህል የከፋሁ አይደለሁም” ያለ ይመስላል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን በብሔራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው ያነጋገሩት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “Our commitment to democracy is real and not skin deep. This is fledgling democracy; we are coming out of centuries of undemocratic practice.” (ለዲሞክራሲ ያለን ዝግጁነት ላይላዩን ሳይሆን እውነተኛ ነው፤ ለረጅም ዘመናት ከቆየንበት ፀረ ዲሞክራሲ ሥርዓት አንፃር ያለንበት ዲሞክራሲ ገና ያልጠና ነው) በማለት ተናግረዋል፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የተፈለገውን ያህል አለማደግ አገሪቱ ለረጅም ዘመን የቆየችበት ጸረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ኃይለማሪያም እንዲህ ቢሉም ዓለም አቀፍ ተቺዎቻቸውና አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸው ግን በጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየት የሚስማሙ አይመስልም። ምክንያታቸው ደግሞ አንድ መንግስት እንዴት ራሱ ላወጣው ህግ መገዛት ያቅተዋል ሲሉ ይጠይቃሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባሎቻችን እና አመራሮቻችን ታሰሩብን ተገደሉብንና ከመደበኛ ስራቸው ተፈናቀሉብን፣ በፖለቲካ አመለካከታቸን ብቻ የዜግነት መብታችን የሆነውን በአገራችን ሰርተን የመኖር መብታችን ሊከበርልን ባለመቻሉ ለስደት ተዳርገናል የሚሉ ጋዜጠኞች በአገሪቱ በስፋት ይሰማሉ። እነዚህን ሁሉ ትችቶች ውድቅ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት ግን ትችቶቹንና ቅሬታዎቹን “የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠልሸ ነው። ልማቱን ለማደናቀፍ ነው” ሲል ያጣጥላቸዋል። ለእነዚህ ሁሉ ትችቶች በአንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመብት ተሟጋች ተቋማት መንስኤያቸው መንግስት ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ያልተላበሰ መሆኑ ሲሉ ይከሳሉ። እነዚህ ትችቶችና ለትችቶቹ መንስኤ የሆኑ ነጥቦች ግን ወደየት እንደሚያመሩ አሁን ላይ ቆሞ መናገር አይቻልም።