ይህች ምስሉ ላይ ውሃ ባናቷ ተሸክማ የምትመለከቷት የፈረንጅ ሴት ….ማን ትመስላችኋለች ? …
ግዴለም ማንነቷ ይቆያችሁ ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ …ባልዲዋን ለአፍታ አሳርፋ አንድ የስልክጥሪ ብታደርግ ሰማዩን በኤሊኮፕተር ምድሩን በዘመኑ መኪናዎች ማጥለቅለቅ የምትችል ሴት ናት !! እና ምንድነው እንዲህ የሚያኳትናት በሉኛ ….ወዲህ ነው ነገሩ …
በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንኳን የሃብታም ሚስት የሃብታም ቅምጦች አፈር አይንካን ሲሉ ማየት የተለመደ ነው ! ምን ሩቅ አስኬደን እዚች የፈረደባት ኮንዶሚኒየም ላይ እንኳን አንዳንድ የአዲስ አበባሃብታሞች ልብስና ቀለብ ችለው የሚያደልቧቸው ወዛዝርት ከተቻለ በግል መኪና (አቶዝና ያሪስ ውለው ይግቡ) እሱም ካልሆነ ወጣ ሲሉ ‹‹ ህዝብ ህዝብ ላለመሽተት ›› ካለላዳ ታክሲ እንዲች ብለውእግራቸውን አያነሱም !
ከወደማላዊ የሰማነው ዜና ደግሞ ይህን ብሶታችንን አስረስቶ ለካስ ይች አለም ቢያንስም ሰው አላት እንድንል አስገድዶናል … ቢልጌትስን ታውቁታላችሁ ….(ወዳችሁ ነው የምታውቁት … ሌላውንተውትና ይሄን ያፈጠጣችሁበትን ኮምፒውተር ፕሮግራም ሰርቶ ያገናኘን ማን ሆነና) …. እና ይህ ሰው በአለም ላይ ከሃብቱ ቀጥሎ የሚታወቀው የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ነው … እንደውምበሚስቱና በራሱ ስም ባቋቋሙት ፋውንዴሽን /Bill & Melinda Gates Foundation / አፍሪካን በየአመቱ የአህያ ጆሮ የሚያካክል ዶላሩን እየመዘረጠ በቸርነት ሲረዳ ቆይቷል …(አፍሪካየአንዳች ሰላቢ አለባት እንጅ የሱ እርዳታ ብቻ ሰው ባደረጋት ነበር )
እና የቢልጌትስ ባለቤት መሊንዳ ጌትስ /MELINDA Gates/ በዚሁ በጎ አድራጎት ድርጅታቸው በኩል ዶላር እየወረወሩ ረዳሁ ማለቱ ብቻውን አላረካ ቢላት …የአፍሪካዊያንን እናቶች ድካም እናህመም በአካል ለመካፈል ወሰነች….ወስናም አልቀረች ወደማላዊ ሄዳ ይች ‹‹ሽ አሽከር ከፊቷ ሽ አሽከር ከኋላዋ የሚያረግድላት ›› እመቤት በአምሳ አመቷ የማላዊ እናቶች ጋር ሃያ ሊትር የሚይዝየፕላስቲክ ባልዲዋን አንጠልጥላ ወንዝ ወረደች …ለምን አትሉም …ውሃ ልተቀዳ!!
ፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ለሰአታት አብራቸው ተጉዛ ውሃ ቀድታ ተመለሰች …አለም ይህንን ድርጊት አይቶ ተደመመ !!የሚሊንዳም ፍላጎት ለአፍሪካዊያን እናቶች አለም ትኩረት ይስጥ ነውጥያቀዋ ..ንፁህ ውሃ ያገኙ ዘንድ እንርዳቸው ነው ዘመቻዋ! እኔም ከዛዛዛዛዛ ላይ ወርዶ እንዲህ የሰዎችን ችግር ከነድካምና ህመሙ መካፈል ከተቻለ እዚች አፍንጫችን ስር ያሉትን ሚሊየን ችግረኞችበችግራችሁ አለን ብንል ምን ይለናል ስል አካፈልኳችሁ ! አይታፈር መቸስ የማላዊ መንግስት “ባለቤቷም መጥቶ በጀሪካ ውሃ ቢቀዳ ለገፅታ ግንባታ ጥሩ ነበር ” ….ይሉ ይሆናል ውስኪ ፉት እያሉ !አፍሪካ ነዋ !!