Wednesday, 05 August 2015 14:29
በሳምሶን ደሳለኝ
44ኛው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ እና በኬኒያ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰዋል። ፕሬዝደንቱ ወደተለመደ የስራ ገበታቸው ቢመለሱም በሁለቱ ሀገሮች ያደረገጓቸው ጉብኝቶች በተለያዩ ወገኖች ብዙ እየተባለበት ያለ ጉዳይ ነው። የአሜሪካ መንግስት በዓለም ላይ ከሚጫወተው ሚና አንፃር የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ብዙ ትርጓሜ ቢሰጠውም የሚገርም አይደለም።
በዚህ ጽሁፍም ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ያለውን አንደምታዎች ለማሳየት ይሞክራል። ይህም ሲባል፣ በተለይ ባራክ ኦባማ በቻይና መንግስት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ልዩነት ለማሳየት የተጠቀሙበትን አገላለጽ እንዲሁም በገዢው ፓርቲን ላይ በሰነዘሩት ምልከታዎች ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምላሽ አደምታዎችን ለመዳሰስ ያለመ ነው።
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንፃር
የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በአንዳንድ የዲያስፖራ ኃይሎች የተወደደ አልነበረም። በተለይ የ2007 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን እና ገዢው ፓርቲም በዴሞክራሲያዊ መንገድ መመረጡን ባራክ ኦባማ እውቅና መስጠታቸው በተቃዋሚ ኃይሎች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የመብት ተሞጋች ተቋማት ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሎባቸዋል። በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎች ኦባማ “ቀብሮን ሄደ” እስከማለት ደርሰዋል።
ባራክ ኦባማ ይህ አስተያየት ከሰጡ በኋላ በአፍሪካ ሕብረት በማንዴላ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር “…..From Sierra Leone, Ghana, Benin, to Botswana, Namibia, South Africa, democracy has taken root.” በእነዚህ ሀገሮች ዴሞክራሲ ስር ይዟል ከማለት ውጪ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ስር ይዟል የሚል ቋንቋ አልተጠቀሙም። ይህን የኦባማ አባባል አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎች እንደማካካሻ ወስደውታል። ወይም እንደየምርጫቸው ተርጉመውታል።
በርግጥ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ለገዢው ፓርቲ የተመረጠ እና ቅቡል መንግስት መሆኑን እውቅና መስጠት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አሜሪካ በዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ መድረክ ያላትን ሚና በቅጡ የሚረዳ ሰው የባራክ ኦባማ እውቅና መስጠት ትርጉሙ የትየለሌ ነው። በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ መንግስት ገዢው ፓርቲን ስንወስደው፣ ከኢኮኖሚ ድጋፍ ባሻገር ዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን ከአሜሪካ መንግስት ያስገኝለታል። ሰፋ ተደርጎ ሲወሰድ ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ለመረጠውም ላልመረጠውም ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ተጠቃሚነት ይኖረዋል።
የሚነሳው ጥያቄ ግን፣ ባራክ ኦባማ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ ሂደት ማረጋገጫ መለኪያ ተደርገው መወሰዳቸው ላይ ነው። ይህም ሲባል፣ የኦባማ መንግስት ዴሞክራሲን ለመተረክ የሚያበቃው ዓለም ዓቀፍ የሞራል ልዕልና ያለው መንግስት ነው? የአሜሪካ መንግስት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመርህ ወይንስ በጥቅም ላይ የተንጠለጠለ ነው? ባራክ ኦባማ አሁን ላይ ኢትዮጵያን ለምን መጎብኘት አስፈለጋቸው?
ከሁሉ በላይ ግን ኦባማ “ቀብሮ ከገደለን በኋላ” የሚለው አገላለጽ በጣም አጠያያቂ ወይም በየዋህነት የተሰነዘረ ፖለቲካዊ ምልከታ የሌለው ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህም ሲባል፣ በኢትዮጵያ የዴምክራሲ ሂደት ላይ ባለቤቱ እና ወሳኙ አካል ማንነው? በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቀባሪው፣ ገዳዩ ወይም እስትንፋስ ሰጪውስ ማን ነው? የኦባማ አስተያየት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ላይ ያለው ፋይዳስ ምን ያህል ነው? እና ሌሎችም ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡
ቁምነገሩ ያለው ወይም በጥሬው የፖለቲካ ቋንቋ ነገሮችን ለመቀበል ወይም ለመረዳት አለመሸሽ ነው። ባራክ ኦባማ ገዢው ፓርቲ በምርጫ የተመረጠ እና ቅቡል ፓርቲ ነው በሚል ያላቸውን መረዳት በአደባባይ አንጸባርቀዋል። ተቃዋሚዎች ለምርጫው እውቅና መሰጠቱ እና ገዢውን ፓርቲ ሕጋዊ መሆኑን በኦባማ መገለጽን ለመቀበል አልፈቀዱም። ካለመቀበል መብት አንፃር ይቻላል። ሆኖም ግን ኦባማ ገዢ ፓርቲ የተመረጠና ቅቡል ከማለት ይልቅ፣ አሁን ካለው ተጨባጭ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አንፃር ከገዢው ፓርቲ ጋር ወገንተኛ በመሆኔ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያስከፍለኝ የፖለቲካ ዋጋ የለም ቢሉስ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?
በርግጥስ ባራክ አባማ ገዢውን ፓርቲ ከምንም ትንታኔ ውጪ ቢደግፉት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአሜሪካን መንግስትን ምን ሊያስከፍሉት ይችላሉ? በሁለቱ ሀገሮች መካከል ባለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተቃዋሚ ኃይሎች ሚና እና ተፅዕኖ ምንድን ነው? በአሁን ሰዓት በሁለቱ ሀገሮች መካከል በሚደረሱ የሁለትዮሽ ስምነቶችን በመቃወም የሚያንቀሳቅሱት ማሕበራዊ መሰረት አላቸው? ለእነዚህ ምላሽ የሚሰጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ከተገኘ በርግጥም የሚከበር ነው፡፡
ለማሳያነት ግን ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ምርጫ በተመለከተ በዚህ ጋዜጣ የሰፈረውን የአዲስ አበባ ምርጫን ውጤት በድጋሚ እንመልከተው። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለምርጫ እድሜያቸው የደረሱ ነዋሪዎች ቁጥር 1.91 ሚሊዮን መሆኑን የቤቶችና የስታስቲክ መረጃ የሚያሳየው። ለምርጫ የተመዘገቡት ነዋሪዎች ቁጥር 1.4 ሚሊዮን ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 1.14 ሚሊዮን ነዋሪዎች ናቸው ወደ ምርጫው ጣቢያ ሄደው ድምጻቸውን የሰጡት። ይህ ማለት (1.91-1.14) 770ሺ ነዋሪዎች በምርጫው አልተሳተፉም። ከዚህ አንጻር የፕሬዝደነት ባራክ ኦባማ የ2007 ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር ማለታቸው ነው አሳሳቢው ነገር፤ ወይንስ 770ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በምርጫ አልተሳተፉም የሚለው ነው አሳሳቢው ነገር፣ ለተቃዋሚዎች?
ምላሽ የሚሻው ነገር የሚሆነው እነዚህ 770ሺ ነዋሪዎች በምርጫው ለምን አልተሳተፉም? የእነዚህ 770ሺ የነዋሪዎች ድምጽን ለማግኘት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን አልሰሩባቸውም? በሌላ መልኩ ስንመለከተው ለገዢው ፓርቲ ማሸነፍ 770ሺ የነዋሪዎች በምርጫው አለመሳተፋቸው የነበረው ጠቀሜታ በግልጽ የሚታይ ነው። በአንድ ምርጫ የተመዘገበ ሁሉ በምርጫው ይሳተፋል፣ ይመርጣል ማለት አይደለም። በዓለም ዓቀፍ ያለው ተሞክሮ ይህንኑ ነው የሚያሳየው። ስለዚህም ለምርጫ ከተመዘገቡ መራጮች መካከል ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ ማሸነፍ የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘት ችሏል። ይህ ማለት ግን ለምርጫ እድሜው የደረሰ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መርጦታል ማለት አይደለም።
ለማጠቃለል ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አለመጠንከር፣ ተወዳዳሪ አለመሆኑ ገዢው ፓርቲ የራሱ ድርሻ አለው ቢባል እንኳን ለተቃዋሚ ኃይሎች ጠንክሮ ላለመውጣት ግን የአንበሳውን ድርሻ አይወስድም። በትንሹ ለማስቀመጥ ተቃዋሚው ኃይል በዘውግ እና በዘውግ ዘለል አደረጃጀት መካከል ውስጥ የሚዋኝና አንዱ መርጦ መውጣት ያልቻለ ነው። ከርዕዮተዓለም አንፃር የቀያጭነት መስመር የመረጠ ነው። የመደብ ውክልና እና ማሕበራዊ መሰረቱን አንጥሮ ማውጣትና መያዝ ያልቻለበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተያየት ለመታገያም ሆነ ለማኩረፊያ የሚሆን አይደለም። የኢትዮጵያን ችግር ማረቅ የሚቻለው ከኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ መፍትሄ ነው። ሁሉም የቤት ስራውን ይስራ፤ በመጪው ምርጫ ሕዝብ ዳኝነት ይዞ ይጠብቃል።
ከገዢው ፓርቲ አንፃር
ገዢው ፓርቲ ለፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ብቻ ሳይሆን ችግርና ድክመቱን በሰነድ እየጠረዘ የሚያከፋፈል ፓርቲ ነው። በተለይ በአዲስ ራዕይ መጽሄት ላይ የሚስተናገዱት ጽሁፎች ለተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች መታገያ የሚሆኑ ጭምር ናቸው። በጣም የሚገርመው በምርጫ ክርክር ወቅት ገዢው ፓርቲ በራሱ ሰነድ ያሰፈራቸውን ችግሮች ነቅሶ የሚከራከር ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይል የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አድምጦም አያውቅም።
በገዢው ፓርቲ ላይ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ከፍተኛ የሆነ ጫና መሳደሩ አይቀርም። ምክንያቱም ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ከፍተኛ የሚዲያ ጦርነት ያስተናገደ በመሆኑ ነበር። አሁንም በተወሰነ ደረጃ ቀጥሏል። በተለይ በዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች በኩል የተሰነዘረው አስተያየት ለጆሮ እንኳን የሚደሉ አይደለም። በፕሬዝደንቱም ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ምስጋና ይግባውና ለአሜሪካ መንግስት የውጭ ግኝኙነት ፖሊሲ ሁሉንም ነገር ያስችላቸዋል።
ፕሬዝደንቱ ለመንግስታቸው ጥቅም መምጣታቸው ቢታወቅም፣ ገዢው ፓርቲ በበኩሉ ትልቅ መንግስት መሆኑን ግን ማስመስከር ይጠበቅበታል። ይህም ሲባል በምርጫ 2007 አሸናፊ ፓርቲ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ያገኘውን ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ደምሮበት፣ በፖለቲካ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ፍትህ በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችን በተሰጠው ክብርና ልክ ለመፍታት መንቀሳቀስ አለበት። ይህን የሚያደርገው ከሌላው ሊመጣ የሚችል ጫናን ከመፍራት ሳይሆን የትልቅ መንግስት ባሕሪያት መገለጫ በውስጡ የያዘ መንግስት መሆኑ ማሳየት ስለሚጠበቅበት ነው። የዓለም ዓቀፉም ማሕበረሰብ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ተመዝግቧል ከሚባለው ድል በላይ ይጠብቃል።
በአንፃሩ ገዢው ፓርቲ አሁን ከአሜሪካ መንግስት ያገኘውን ድጋፍ ከዚህ በፊት ከቻይና መንግስት ካገኘው ድጋፍ ጋር ደምሮ፣ በእጄ ውስጥ የምዕራቡ እና የምስራቁ ዓለም ድጋፍ ስለገባ መስሚያ የለኝም የሚል ከሆነ፣ ይብላኝ ለባዮቹ።
ኦባማ በቻይና ላይ ምን አሉ?
የቻይና መንግስት ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያለው የኢኮኖሚ ትስስርና መጠን ከአሜሪካ በእጅጉ እንደሚልቅ የአደባባይ እውነት ነው። በቻይና እና በአፍሪካ ሀገሮች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ከ200 ቢሊዮን ዶላር መዝለሉን መረጃዎች ያሳያሉ። ሆኖም ግን ባራክ ኦባማ በአፍሪካ ሕብረት በኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ባደረጉት ንግግር ላይ ቻይና ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ሸንቁጠው ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም።
ኦባማ እንዲህም አሉ፣ የኢኮኖሚ ግንኙነት በቀላሉ የሀገሮችን መሰረተ ልማቶች በውጭ ሰራተኞች በመገንባት ወይም የተፈጥሮ ማዕድኖችን በማውጣት የሚገለጽ አይደለም። እውነተኛ የኢኮኖሚ ሽርክና ለአፍሪካ ጥሩ ስምምነት መሆን አለበት። ይህም ሲባል፣ ስምምነቶቹ ለአፍሪካዊያን የስራ ዕድልና አቅም መጎልበት ፋይዳ ሊኖራቸው ይገባል። “….economic relationships can’t simply be about building countries’ infrastructure with foreign labor or extracting Africa’s natural resources. Real economic partnerships have to be a good deal for Africa — they have to create jobs and capacity for Africans.” ኦባማ አያይዘውም፣ይህን መሰል ስምምነት አሜሪካ ለአፍሪካዊያን ታቀርባለችም ሲሉ በአደባባይ ቆመው ተናግረዋል።
ይህ የፕሬዝደንት ኦባማ ንግግር በግልጽ አሜሪካ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ለመሳተፍ ያነገበችውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያሳያል። በንግግራቸውም በቀጣይ በአፍሪካ ውስጥ በዴሞክራሲ፣ በጤና፣ በኃይል አቅርቦት እንዲሁም በትምህርት ላይ ሀገራቸው እንደምትሳተፍ አትተዋል። በአንፃሩ ኦባማ ከሃምሳ አራት የአፍሪካ ሀገሮች መካከል ከሶስት ሀገሮች ጋር ብቻ የንግድ ልውውጣቸው ከፍተኛ መሆኑ አስታውቀዋል። እነሱም አንጎላ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።
ባራክ ኦባማ አፍሪካ ከመድረሳቸው በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስም ቻይናን ከመሸንቆጥ አልተቆጠቡም። ኦባማ ሃሳባቸውን በዚህ መልክ ነበር የገለጹት፣ ቻይና በሀገሯ ተጠያቂነት የላትም። ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት አለጠያቂ በአፍሪካ እያፈሰሰች ነው። የዚህ የገንዘብ ፍሰት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ ከአፍሪካ ለሚያወጡት ጥሬ እቃ መለወጫ ነው።
በአንፃሩ በግሎባል ታይምስ ላይ የታተመው የሊዩ ዝሁን ጽሁፍ `Vying for influence dilutie Obama’s visit` ባራክ ኦባማ በቻይና ላይ የሰነዘሩት አስተያየት መሰረት የለውም ሲል ያጣጥለዋል። ሊዩ እንደሚለው ላለፉት ስድስት አስርት ዐመታት የአፍሪካና የቻይና ግንኙነት በእኩያነት ላይ የተመሰረተ ነው። ቻይና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ጠንካራ እምነት አላት። ይህም ሲባል ከአፍሪካ ጋር በእርዳታ፣ በንግድ እና በመሰረተ ልማት በትብብር ትሰራለች። ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት የሁለትዮሽ ግንኙነት አድርጋ ትመለከተዋለች። ነገር ግን አሜሪካ ወጥ የሆነ ፖሊሲ በአፍሪካ አትከተልም። ኦባማ አፍሪካ አቅሟን ማሳየት ስትጀምር የአፍሪካ ፖሊሲውን ቀይሯል። ዋሽንግተን የነበራትን ገጽታ ለመቀየር ቻይና በአፍሪካ ላይ ያላትን ፖሊሲ በመኮነን በስታዲዮም ዲፕሎማሲ ለማስተካከል እየሰራች መሆኗን አስረድቷል።
ሊዩ አይይዞም፣ አሜሪካ በአፍሪካ ኃይል ሆና መቀጠል ትፈልጋለች። ከአራት ዓመታት በፊት አሜሪካ 125 ቢሊዮን ዶላር የንግድ መጠን ከአፍሪካ ጋር የነበራት ሲሆን ይህ መጠን በ2014 ወደ 70 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል። ይህ ማለት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ መጠን አንድ ሶስተኛ መሆኑ ነው። ይህ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ የአሜሪካን ነርቭ ነክቶታል “A change of position has touched the nerves of the US.” ብሏል።