Wednesday, 05 August 2015 14:24

በይርጋ አበበ

የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ የቀድሞውን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ወይዘሮ ሐቢባ መሀመድን ጨምሮ 31 ግለሰቦች ከዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው፤ የእስልምና መንግስት ለመመስረት እቅድ አላቸው በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ። ሴትየዋ ከሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በአንድ መዝገብ መከሰሳቸው የታወቀው ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ሲቀርብ ነው። እነዚህ የኮሚቴ አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት መንግስት በሙስሊሙ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያቁም፣ ገለልተኛ መጅሊስ ይቋቋም፣ የአህባሽ አስተምህሮ በሙስሊሙ ላይ በተለይም በአወሊያ ተማሪዎች ላይ በግዳጅ አይጫን እና ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ጥያቄዎች በማንሳት እሰከ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የዘለቀ አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው።
ለግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር መዋልም ሆነ በሽብር ወንጀል እንዲጠረጠሩ ምክንያት የሆነው ክስተት የተፈጠረው በ2004 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የእስልምና አስተምህሮትን በአወሊያ ትምህርት ቤት ይማሩ በነበሩ ተማሪዎች የተነሳ ጥያቄ ነው። የተማሪዎቹ ጥያቄ ቀደም ሲል የገለጽኩት ሲሆን መንግስትም ጥያቄያቸውን እንዲፈታላቸው በህጋዊ መንገድ አቤቱታቸውን እንዲያቀርቡላቸው አንድ ኮሚቴ አቋቋሙ። ይህ ኮሚቴ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በተለይ በመጅሊስ ምርጫ ላይ መንግስት እጁን እንዲሰበስብና ሙስሊሙ ህብረተሰብም በነጻነት የሀይማኖቱን መሪዎች እንዲመርጥ እድሉ ይሰጠው ሲል ጥያቄዎቹን ገፍቶ ማቅረብ ጀመረ።
መንግስት እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ውይይት እያደረጉ በነበረበት ሰዓት በተለይ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን “በሙስሊሙ ማህበረሰብ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በሰላም ተፈቷል” የሚል ዘገባ መሰራጨቱ ኮሚቴውን አስቆጥቶታል። ለኮሚቴው መቆጣት ምክንያቱ ደግሞ ምንም የተጨበጠ ነገር ሳይኖር ችግሩ እንደተፈታ ተደርጎ በመገናኛ ብዙሃን መዘገቡ ህዝበ ሙስሊሙን የሚያስቆጣ ድርጊት ነው። በእኛ ላይም (በመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላቱ) እምነት እንዳይኖረው ያደርጋል በሚል ነበር።
በዚህ ምክንያት መስማማት ያልቻሉት ሁለቱ ወገኖች ጉዳያቸው እየተካረረ በመሄዱ አንዳቸው አሳሪ ሌላኛቸው ደግሞ ታሳሪ በመሆን ተደመደመ። አቃቢ ህግ የሙስሊሙን መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በሙሉ ወደ እስር ቤት እንዲያወርዳቸው ያቀረበባቸው ክስ ደግሞ “በዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት” የተጠረጠሩ መሆናቸውን የሚያትት ሲሆን በተለይም በበርማ እና በታይላንድ የተፈጠረውን አይነት የሽብር ጥቃት በአገሪቱ ላይ ለማነሳሳት ሲያሴሩ ነበር የሚል ክስ ማቅረቡን የኮሚቴው ጠበቃ የነበሩት አቶ ተማም አባቡልጉ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ምንም እንኳ ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት ወንጀል እና ግለሰቦቹ የማይገናኙ እንደሆነ ቢያምኑም።
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ የወንጀል ችሎት ቦሌ ምድብ በዋለው ችሎት አቶ አቡበከር አህመድ መሐመድን ጨምሮ በ18ቱ ተከሳሾች ላይ ከሰባት ዓመት እስከ 22 ዓመት (በድምሩ ለ281 ዓመታት) እስራት እና ለአምስት ዓመታት ደግሞ ከማንኛውም ማህበራዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲታቀቡ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ። ውሳኔው እንደተላለፈም ታራሚዎቹ ይግባኝ ከመጠየቅ እና የፍርድ ማቅለያ ከማቅረብ ይልቅ “አላህ አክብር” ብለው ውሳኔውን መቀበላቸውን የፍርዱን ሂደት ሲከታተሉ የነበሩ የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከላይ የተጠቀሰው ችሎት የሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹን በከሰሰበት የሽብርተኝነት ወንጀል ውሳኔ ሲያስተላልፍ ከዐቃቤ ህግ የቀረበለትን የቅጣት ማክበጃ በማዳመጥ መሆኑም ተነግሯል። አቶ ተማም ግን “አቃቢ ህግ የበርማን እና የታይላንድን ጉዳይ በመጥቀስ ነው በእነ አቡበከር ላይ ክስ ያቀረበው። በርማ እኮ ሙስሊም ዜጎች የሉኝም ከባንግላዴሽ ነው የመጡት ብላ የምታምን አገር ናት” የሚሉት የቀድሞው የእነ አቡበከር ጠበቃ አክለውም የእሳቸው ደንበኞች ግን መንግስት በሀይማኖት ላይ ጣልቃ ገብቷል ብለው መክሰሳቸውን የሚደግፉ እና ደንበኞቻቸው ነጻ መሆናቸውን የሚመሰክሩ ከ300 ሺህ በላይ ምስክሮች እያሉ ነው በበርማ እና ታይላንድ ጉዳይ የተከሰሱት በማለት ደንበኞቻቸው የተከሰሱትም ሆነ የተፈረደባቸው ባልዋሉበት ድርጊት እንደሆነና መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን ያቁም ብለው በመግለጻቸው ብቻ መሆኑን ይናገራሉ።
የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ በበኩላቸው በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በአገራችን የሃይማኖት እኩልነት በህግና በተግባር የተከበረ ሆኗል። ይህም በመሆኑ ከአሉባልታ እና መሰረተቢስ ስሜት ቀስቃሽ ውንጀላዎች በስተቀር ሃይማኖታዊ አድሎ እንዲፈጸም የሚያደርግ ህግ አለ ብሎ በማስረጃ የተደገፈ ወቀሳ እና ትችት ለማቅረብ አንዳችም ተጨባጭ መሰረት የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ እንደተጠበቁ ሆኖ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነት በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚፈታተን ሆኗል” በማለት የገለጹ ሲሆን አያይዘውም “እነዚህን ስንመረምር የምናገኛቸው እውነታዎች በሃይማኖት ሽፋን ለመነገድ የሚሞክሩት ወገኖች ምን ያህል መሰረተ ቢስ በሆነ አጀንዳ ሁከትና ትርምስ ለመፍጠር እንደሞከሩ ለመገንዘብ እንችላለን” ብለዋል።
“ደንበኞቼ የተከሰሱት በሽብር ወንጀል ነው፤ ተቀባይነት የሌለው ውሳኔ ነው። ምክንያቱም ከመጀመሪያም ሊነሳ የማይገባው ክስ ነበር” የሚሉት አቶ ተማም ግን “ክሱን በደንብ አይተህ እንደሆነ መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይግባ የሚል ጥያቄ ነው የተነሳው። ከዚያ የተነሳ ሊከሰሱም ሆነ ሊታሰሩ አይገባም ነው የምለው” ሲሉ ይናገራሉ። የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም ማቅለያ እንዳላቀረቡ ይነገራል። የፍርድ ማቅለያ ለማቅረብ ያልፈለጉበት ምክንያት ምንድ ነው? ወደ ፊትስ ይግባኝ ሊጠይቁ ይችላሉ ወይ? ብለን አቶ ተማምን ጠይቀናቸው ነበር። “ይግባኝ መጠየቃቸው የሚቀር አይመስለኝም። የቅጣት ማቅለያውን በተመለከተ ግን አቀረቡ አላቀረቡ በእንደዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ብዙም ለውጥ ያለው አይመስለኝም” በማለት የቅጣት ማቅለያ ያላቀረቡበትን ምክንያት ገልጸዋል።
ከውሳኔ በፊት የኮሚቴው የፍርድ ሒደት
በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በዐቃቤ ህግ ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ሲከታተሉ ከቆዩ ወደ ሶስት ዓመት ጊዜ ሆኗቸዋል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ለማሳለፍም ሆነ ከጥፋት ነጻ መሆናቸውን ለመግለጽ የወሰደው ጊዜ የተጓተተ መሆኑን የተከሳሾቹ ጠበቃ የነበሩት አቶ ተማም አባቡልጉ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገሩ ቆይተዋል። የተከሳሾቹ ቤተሰቦችም የፍርድ ሂደቱ የተጓተተ በመሆኑ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተው ነበር። ተከሳሾቹ የተከሳሽነት ቃል ከሰጡ በኋላ በህጉ መሰረት ምስክር መሰማት ሲገባው ችሎቱ በርካታ መዝገቦችን ያያል በሚል ምክንያት ቀጠሮው መራዘሙ ተገቢ እንዳልሆነ በአንድ ወቅት የተናገሩት አቶ ተማም “ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ናት። ይህንን ጉዳይ የሚመለከቱ ሌሎች በርካታ ችሎቶች እንዲኖሩ ማድረግ ይገባ ነበር። በተለይ በዚህ ምክንያት የሰዎች በፍጥነት የመዳኘት መብታቸው ሊጣስ አይገባም። ደንበኞቼ ነጻ ቢባሉም ጥፋተኛ ቢባሉም በምንም የማይተካ እና ሊካስ የማይችል ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽ
የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የኮሚቴው አባላት ጥፋት የለባቸውም ሲሉ ተቃውሟቸውን በማሰማት በመንግስት ላይ ትችት ካቀረቡት ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የአፍሪካ ኮሚሽን አንዱ ነው። ኮሚሽኑ መቀመጫውን ጋምቢያ ባንጁል ላደረገው የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አቤቱታ ማቅረቡ ተነግሯል። አቤቱታው የቀረበው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አቶ ተማምን ጠይቀናቸው ነበር። አቶ ተማም የኮሚሽኑ ክስ እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 3 ቀን 2013 ያቀረበው አቤቱታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት እና ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኮሚቴው አባላት ከዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው፤ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ተልዕኮ አላቸው በማለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ ማቅረባቸውና የኮሚቴው አባላትም ሰብአዊ መብታቸው ሳይጠበቅ በእስር ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ ነበር።
ከፍርድ በኋላስ?
መንግስት በሙስሊሙ ህብረተሰብ የመጅሊስ አመራረጥ እና የአህባሽ አስተምህሮ ጣልቃ መግባትን በተመለከተ እጁን እንዲሰበስብና እድሉን ለሀይማኖቱ ተከታዮች እንዲተውለት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄ ያቀረቡት የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹ “በመጅሊሱ ሳይሆን እሱን በሚመሩ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ምክንያት ከሀይማኖቱ መርሆዎች ውጭ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሚጫንበት ተደጋጋሚ በደል የሚፈጥረው ቁጣ እና ተቃውሞ በሂደት በአገራችን ሰላም ደህንነትና ጸረ ድህነት ትግል ላይ እንቅፋት ስለሚሆን መንግስት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የተጋረጠውን ችግር እንዲፈታ” ሲሉ ከመታሰራቸው በፊት ሃሳባቸውን አቅርበው ነበር።
ከዓመታት በፊት ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚንስትሩ አቅርቦት የነበረው አቤቱታ “ሳይቃጠል በቅጠል” የሚሉት አይነት ማሳሰቢያ እንደሆነ ያመለክታል። አሁን መንግስት የወሰደው እርምጃ ኮሚቴው ቀደም ሲል አድሮበት የነበረው ስጋት እንደማይነሳ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? “ነጻነት የሌለው ፍርድ ቤት ነጻ ሆኖ ፍርድ ይሰጣል ብለን አንጠብቅም” የሚሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉ “ዜጎችን በማሰር ይህችን ሀገር ወደሰላምና ማግባባት ማምጣት አይቻልም። የሙስሊሞችን ጥያቄ በአግባቡ መልስ መስጠት እንጅ የተመረጡ ሰዎችን (መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን) በውይይት ማሳመን ሲያቅት ማስፈራራትና አሸባሪ ብሎ ማሰር መፍትሔ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
የሙስሊሙን ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ለመክሰስ መንግስት የተጓዘበት መንገድ “ፍትህን የማስፈን እና ህግን የማስከበር ሳይሆን የፍትህ ተቋማት ዜጎችን እንደ ማጥቂያ መሳሪያ ለመጠቀም የታለመ መሆኑን” ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች ይናገራሉ።

Leave a Reply