በማደራጀት በማስተባበር እና በመቀስቀስ ተግባራዊ ስራ ላይ እንዋል::(ምንሊክ ሳልሳዊ)
በሃገራችን የድህረገጾች ተደራሽነት እጅግ አናሳ ነው::ከጽሁፍ ስራ በተጨማሪ በትብብር ወደ መሬት መውረድ ያለብን ጊዜ ላይ መሆናችንን አንዘንጋ::የግድ በተቃዋሚ ድርጅት ስር መታቀፍ አሊያም በበርካታ ሰዎች በተከበበ ማህበር ስር መጠለል ሳያስፈልግ ሁለት ሶስት እና አራት ሆኖ ሰፍቶ በማደግ በመደራጀት በማስተባበር በመቀስቀስ ለለውጥ ወደ ተግባራዊ ስራዎች መግባት እንችላለን::የፖለቲካ ድርጅቶች መተው እንዲያደራጁን ከመጠበቅ አሊያም በአገዛዙ በተፈጠረ ሽብር ፍርሃት አድሮብን ራሳችንን ከመደበቅ በአጠገባችን ካሉ ቤተሰቦቻችን አሊያም የልብ ወዳጆቻችን/ጓደኞቻችን ጀምረን ከምናምናቸው ሰዎች ጋር በመሆን ራሳችንን በማደራጀት በማስተባበር እና በውስጥ ቅስቀሳ ላይ በመሰማራት ራሳቸውን መስዋእት አድርገው ለውጥ ሊያመጡ የተነሱ የነጻነት ሃይሎችን በሕዝባዊ ማእቀፍ መርዳት እንችላለን::ልብ ያለው ልብ ይበል::
ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል::ተነሳሽነት መፍጠር የለውጥ ፈላጊ ዜጎች እያንዳንዱ ድርሻ ነው::በመሃል አገር ይሁን በዳር አገር የለውጥ እና ነጻነት ናፋቂ ሃይሎች የጀመሩትን ትግል መርዳት የምንችለው ከራሳችን ስንጀምር መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም እያንዳንዳችን ከአንድ ራሳችን ጀምረን ለገዛ ነጻነታችን እና መብታችን ተቆርቋሪ ስንሆን ልሌላውም ተርፈን ሌላውንም እናተርፋለን::መደራጀት ማስተባበር እና መቀስቀስ የሚጀመረው ከሁለት ሶስት አራት እየተባለ ወደ ተግባራዊ ስራ በመግባት ሕዝባዊ መነሳሳቶችን በመፍጠር ለለውጥ የሚደረገውን ጉዞ ልናግዝ ይገባል::ጊዜ በየተገኘበት የሰዎችን ስም የምንበክልበት የተነሳሽነትን እቅል የምናደቅበት አሊያም በለውጥ ሃይሎች መካከል መተማመን የለም ተብሎ ትዝብት ውስጥ የምንወድቅበት ሲልም አንዱን እያነሳን አንዱን እየጣልን በነፈሰበት የምንነፍስበት ጊዜ አይደለም::እንንቃ::
ሕዝብን ማስተማር የሚጠበቀው ከነቃው ሕብረተሰብ አካል በወጡ የለውጥ ሃይሎች መሆኑ አይካድም::የለውጥ ሃይሎችም ሌላውን ማስተማር ስለነጻነት እና መብቱ መናገር ከቻልን ማንም ነጻነቱን እና መብቱን ማስከበር የሚጠላ አካል ስለሌለ አምባገነኖችን መዋጋት እምቢ የሚል ሕብረተሰብ የለም::አምባገነኖች በድራቸው የሚፈጥሩትን የፍርሃት እና የሽብር ተንኮል መበጣጠስ የምንችለው ለለውጥ ያለን ፍላጎት ይዘን በመነሳት ሕዝብን በማስተማር እና ተነሳሽነትን በመፍጠር ተግባራዊ ስራ ላይ ስንውል ብቻ ነው::በማደራጀት በማስተባበር እና በመቀስቀስ ተግባራዊ ስራ ላይ እንዋል::በጋራ እንቁም