የኢትዮትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ ሂደትና ያስከተላቸውን ሁኔታዎች የገመገመና የግንባሩንና የአባል ድርጅቶቹ የወደፊት ድርጅታዊ እንቅስቃሴ የትኩረት አቅጣጫ ላይ መመሪያ የሰጠ ልዩና አስቸኳይ ጉባኤ ነሐሴ 2 እና 3 አካሄደ፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የግንባሩ ዋና ጽ/ቤት በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ከ4ቱ የመደረክ አባል ድርጅቶች የተወከሉ 70 ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ከምርጫው ዝግጅት ወቅት ጀምሮ እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ ድርጅቱ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎችና ምርጫው በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዳይከናወን በገዥው ፓርቲ የተፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትና የአፈና ድርግቶችን እንደዚሁም ከምርጫው በኋላ በመድረክ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እተፈጸሙ ያሉትን ግዲያዎች፣ እስራቶች፣ ከሥራ፣ ከእርሻ መሬታቻና መኖሪያቸው የማፈናቀል ተግባራትን በዝርዝር የሚያስረዳ ሪፖርት በወቅቱ የግንባሩ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተካሄዶበታል፡፡

ጉባኤው በመጨረሻም ኢህአዴግ ባለፉት 24 የአገዛዝ ዘመኑ የተካሄዱት 5 ዙር ምርጫዎች ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ታአማኒ እንዳይሆኑና የሕዝባችን የሥልጣን ባለቤትነትም በሕገመንግሥቱ መሠረት እንዳይረጋገጥ ሲፈጽም የቆየውን አምባገነናዊ ተንኮሎችና የአፈና ተግባሮች በጥብቅ አውግዞ መድረክና አባል ድርጅቶቹ ከመላው ሕዝባችን ጋር በመሆን ይህንኑ የኢህአዴግ አገዛዝ የፈጠረውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመቀየር ማተኮር በሚገባቸው ሰላማዊ የትግል አካሄዶችና ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መመሪያ የሰጠ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የአቋም መግላጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት መድረክ
ልዩና አስቸኳይ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

እኛ የዚህ ልዩና አስቸኳይ ጉባዔ ተሳታፊዎች በመድረኩ ሊቀመንበር የቀረበውን ሁሉን ዳሳሽ ሪፖርት በስፋትና በጥልቀት ተወያይተንበት የሀገራችንን የ2007 ዓ.ም ምርጫ በልዩ ሁኔታ ተመልክነዋል፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ የተጠቀሱት ጉዳዮች የመድረኩን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ያመላከቱ መሆናቸውንም ለመገንዘብ ችለናል፡፡ የ2007 ዓ.ም ምርጫን አስመልክቶ ሪፖርቱ ቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴን፣ ለምርጫ የተደረጉ ዝግጅቶችን፣ በድህረ-ምርጫም በአባሎቻችንና በደጋፊዎቻችን በአጠቃላይ በዕጩዎቻችንና ወኪል ታዛቢዎቻችን ላይ በተለይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ እስራት፣ ማሳደድና ወከባ በጥሩ ሁኔታ አብራርቶ ያቀረበ ሪፖርት መሆኑንም አጢነናል፡፡ ከዚህ ሪፖርትና ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳትም በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ብሎም በድርጅቱ የወደፊት የትግል አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ከዚህ የሚከተለውን የአቋም መግለለጫ አውጥተናል፡፡
1. መድረክ ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ታዛቢ በሌለበት ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ተአመኒና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ገና ከጅምሩ ሲያስገነዝብ የቆየ ቢሆንም፣ የዚህ ጉዳይ አስፈጻሚ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማንአለብኝነት ምርጫው እንዲካሔድ አድርጎ፣ ውጤቱም አለም ጉድ እስኪል ድረስ በሚያሳፍር ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ስለሆነም የመድረክ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል ምርጫውን አስመልክቶ ያወጣቸውን መግለጫዎችን በሙሉ የምንቀበል መሆናችንን እየገለጽን፣ የምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ኢ-ዴሞክራሲያዊና ህገመንግስቱን የጣሰ ስለሆነ ጉባዔው የማይቀበል መሆኑን አጥብቆ ያሳውቃል፡፡
2. ከላይ የተመለከተውን ከምርጫው ህግና ህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ውጭ የተከናወነ የምርጫ ውጤት አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም፣ የሚሊዮኖች ድምጽ የተዘረፈበትን ምርጫ በሀቅ ያሸነፉ አስመስለው በፉከራ ያደረጉትን ንግግርም ጉባዔው አጢኖ ከአንድ የሀገር መሪ እንዲህ አይነቱ ድርጊት የማይጠበቅ መሆኑን በማስረገጥ ኮንኖአል፡፡
3. ሕገ-መንግስታዊና ህጋዊ የምርጫ ስርዓት ተጥሶ የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞን፣ ካቢኔና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች በኮማንድ ፖስት እየተመራ ከቀበሌ ታጣቂ እስከ ልዩ ኃይል በተጠቀሙበት ሁኔታ የተካሄደው ምርጫ፣ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጥረታችንን ቀኝ ኋላ ያዞረና ሕገ ወጥ ተግባር ስለሆነ፣ የምርጫውን አፈጻጸም የሚያጣራ በሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አካል ተቋቁሞ ውጤቱ ለህዝባችን በአስቸኳይ ይፋ እንዲደረገ፡፡
4. አስነዋሪው የምርጫ ድራማ ከተጠናቀቀ በኋላ በተለለያዩ መንገዶች ማለትም ማዳበሪያ በግድ ግዙ፣ ማዳበሪያ ከአቅም በላይ ግዙ፣ ማዳበሪያም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን መድረክ ይስጣችሁ በማለት በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባና ማስፈራራት፣ ከዚያም አልፎ የሚፈጸመውን እስራት፣ ግድያ፣ ቤት ማፈረስ እንዲሁም ከቤትና ከስራ ማበረር መንግስት በአስቸኳይ እንዲያስቆም፡፡
5. መድረክ በሰላማዊ መንገድ መታገልን ለዚህ ሀገር ፖለቲካ የሚበጅ መንገድ ነው ብሎ ይህንኑ በመምረጥ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ዕለት ጀምሮ ለችግሮቻችን መፈታት ዙሪያ መደራደር መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለጽ ቢጠይቅም ኢህአዴግ አሻፈረኝ ብሎ የድርድር ዕድሉን ዘግቶ ስለቆየ ጉባዔው ይህንን የኢህአዴግን ግትር አቋም በጥብቅ እያወገዘ በዚህ ረገድ ህዝባችን አስፈላጊውን ጫና በኢህአዴግ ላይ ፈጥሮ ለሰላማዊ ድርድር እንዲቀርብ እንዲያደርግ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
6. ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ድህነትና ስቆቃ በህዝባችን ላይ እየደረሰ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ሀገራችን ከምንጊዜውም የባሰ ሙስና ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች፡፡ ይህም ከውጭ ሀገር ለልማት ተብሎ በብድር የሚመጣውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ውጭ በማሸሽ ጭምር ለቀጣይ ትውልድ ከፍተኛ እዳ ስርዓቱ እያረወሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህንን በሚመለከት ተጨባጭ እርምጃዎች እስከአሁን ድረስ አለመወሰዳቸውን ጉባዔው በጥብቅ ያወግዛል፡፡
7. የዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ፕሬዝዳንት የሆኑት ባራክ ሁሴን ኦባማ በቅርቡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወቃል፡፡ በዚሁ ጉብኝታቸው ወቅት የመድረክን አመራር በመገናኘት የኢህአዴግን ገለጻ ብቻ ሳይሆነ የተቃዋሚውን ወገን እንዲያዳሚጡ በኤምባሲያቸው በኩል ተጠይቀው ሳይቀበሉ በመቅረት የኢህአዴግ ወገን እራሱን እንከን የለሽ አድረጎ ባቀረበው ገለጻ ላይ ተመስረተው የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በተለይም ኢህአዴግን “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግስት” የተባለው ሙገሳ የተሳሳተና አምባገነኖችን ያበረታታ ሊሆን ችለአል፡፡ ይህ የመድረክ ልዩና አስቸኳይ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ በስፋት እና በጥልቀት ተወያይቶ ማዘኑን በግልጽ ደብዳቤ ለኤምባሲው አንዲደርስ ወስኖአል፡፡
8. ለዲሞክራሲ እና ለሰላም መስፈን ታላቁ ነጻነት እና የህግ የበላይነት መከበርና በተግባር መዋል ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን ይህ አብይ ጉዳይ ባለመተግበሩ የመልካም አስተዳደር ፣ፍትሕና ነጻ ዳኝነት እጦት ህዝባችንን ለከፋ እንግልትና ወከባ፣ እስራት፣ ግድያ እና ስደት ዳርጎታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባገራችን የሰፈነው አምባገነናዊ የፖለቲካ የበለላይነት እንጂ የህግ የበላይነት አይደለም፡፡ ስለዚህም ዜጎች በሀገራቸው በሰላም ሰርተው የመኖር መብታቸው በተግባር ተከበሮ እንዲኖሩ ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለወጥ በጽናት እንታገላለን፡፡
9. የኢህአዴግ መንግስት ሁሉንም የመቆጣጠር አባዜ ለሀገራችን ሰላም መስፈን ጠንቅ እየሆነ ነው፡፡ በሕገ-መንግስቱ በተደነገገው መሰረት ዜጎች የፈለጉትን ሀይማኖት ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የመከተል መብት አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ አገዛዝ ሀይማኖትን የፖለቲካ መሣሪያ ለማድረግ ጣልቃ መግባቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በዚሁ አድራጎቱ በቅርቡ የሙስልሙ ማህበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሚዕመናኑን በመወከል በሰላማዊ አግባብ ላቀረቡት ህጋዊ ጥያቄ በአሸባርነት ተወንጅለው ከ7 እስከ 22 ዓመታት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይህንኑ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ አድራጎት ጉባዔው በጥብቅ ያወግዛል፡፡
10. ህዝባችን ዛሬ አደገ ከሚባለው ኢኮኖሚ ተካፍሎ መብላት ቀርቶ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ረሃብ ድህነትና ስራ አጥነት የእለት ጉርሱን እያጣ የስቃይ ኑሮ እየገፋ ባለበት ሁኔታ ኢህአዴግ ህዝቡ በምግብ እራሱን ችሎአል እያለ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሰበብ አስባቡ ለተለያዩ ፖለቲካዊ ጥቅሞች የሚውሉ ድግሶችና ፈንጠዚያዎች የሀገርቷን ሀብት እያባከነ ይገኛል፡፡ ጉባዔው ይህንን የኢህአዴግ ድርጊት በጥብቅ እያወገዘ በተለይም በድርቅ ለተጎዱት ወገኖቻችን አስቸኳይ እርዳታ እንዲደርስ እንዲደረግ እና የሀገር ሀብት ከማባከኑ ተግባር እንዲቀጠብ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
11. በምርጫው ምክንያት የተገደሉና የተፈናቀሉ ወገኖች በመንግስት ካሳ እንዲከፈላቸው ሆኖ ገዳዮቹም ለህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ፣ ከስራቸው የተፈናቀሉት ወደ ስራቸው እንዲመለሱና ለእስራት የተዳረጉትም በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጉባዔው አበክሮ ይጠይቃል፡፡
12. መድረክ የወቅቱ ሁኔታ የሚጠይቀውን ትግል በበቃት ለማካሄድ አሁን ያለውን አደረጃጀቱን አጠንክሮ እንዲንቀሳቀስና አባል ድርጅቶቹም የውሕደት ጥያቄን ትኩረት ሰተው እየሰሩ እንዲቆዩ ጉባዔው ወስኖአል፡፡
13. እስከ አሁን በሀገራችን በአምሰቱም ዙሮች የተደረጉት ምርጫዎች ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ታዓማኒ እንዳልነበሩ ጉባዔው አረጋግጦ ለወደፊትም በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ተገቢነት እንደሌለው በማመን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከ አሁን ከጎናችን ተሰልፎ ላበረከተው አስተዋጽኦ ጉባዔው እያመሰገነ ለወደፊቱም በሰላማዊና ህጋዊ የትግል አማራጮች መድረክ ሁኔታውን ለመቀየር በሚያደርገው ትግል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጉባዔው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ነሐሴ 3/2007ዓ.ም፣አዲስ አበባ

Leave a Reply