Wednesday, 12 August 2015 12:17
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ አሎ ቀበሌ ውስጥ በፖሊስ ባለስልጣናትና አባሎች መሪነት በበርካታ የአማራ ተወላጆች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰ መሆኑን ሰመጉ (ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ) በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። “ብሔር ተኮር ማፈናቀልና እንግልት በአስቸኳይ ይቁም!” ሲል በ136ኛ ልዩ መግለጫው ሰመጉ እንዳተተው ከሆነ፤ በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ በርካታ ሰዎች “የአካባቢው ተወላጆች አይደላችሁም” በሚል መነሻ ብቻ በአካባቢው በሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች እና ባለስልጣናት አስተባባሪነት የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጥፋት እየደረሰባቸው ነው ብሏል።
እንደ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ መግለጫ ከሆነ፤ በተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በሚገኙ ዜጐች ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል አለመሆኑን አመልክቷል። ጉዳቱን በቁጥር ሲያስቀምጠውም በዚህ ዓመት ብቻ ከመጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ፤ 10 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል። 99 የሣር ክዳን ቤቶች በእሣት የወደሙ ሲሆን፤ በተያያዘም 25 የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤቶች በእሣት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ያትታል። በዚህም የቃጠሎ ጥቃት ሳቢያ ከ71 ሰዎች በላይ ከቤት ንብረታቸውና ከእርሻ መሬታቸው እንደተፈናቀሉ ይፋ አድርጓል።
ዜጐች በሀገራቸው ተንቀሳቅሰው የመስራትና ሀብት የማፍራት ሕገመንግስታዊ መብት እንዳላቸው የሚሞግተው የሰመጉ መግለጫ፤ የተፈፀመው ድርጊት ግን ከሀገሪቱ ሕግና አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም ጋር በፍፁም የሚጣረስ ነው ሲል እምነቱን ይገልፃል።
መግለጫው አክሎም በውድመቱ ቤት ንብረታቸውን አጥተው ለጉዳት ለተዳረጉ ዜጐች በአካባቢው የኦሮሞ ተወላጆች በግል ተነሳሽነት የገንዘብና የእህል እርዳታ ተደርጐላቸው ተረጋግተው እንዲኖሩ ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን የሰመጉ ባለሙያዎች ከወረዳው አስተዳዳሪ በተሰጣቸው ማብራሪያ የተነገራቸው ቢሆንም፤ ይህ መግለጫ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እርዳታው ለተጐጂዎቹ አለመደረሱን አረጋግጫለሁ ብሏል።
አሁንም ድረስ በርካቶች ብሔር ተኮር ለሆነው ችግር መፍትሄ በማጣታቸውና በደረሰባቸውም ጉዳት ድጋፍ ሳያገኙ በመቅረታቸው ለጐዳና ህይወት መዳረጋቸውን ያተተው መግለጫው፤ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰት ለክልልና ፌዴራል ተቋማት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ አስተዳደራዊ ጫና፣ ዛቻና ሕገወጥ እስራት ጭምር እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ሰመጉ ገልፀውልኛል ሲል በልዩ መግለጫው ያትታል።