ከወራት በፊት በም/ጠ/ሚኒስቴር ደመቀ መኮነን የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው የመቅደላ ዩኒቨርስቲ ግንባታው ሳይጀመር የእርስ በእርስ ግጭት አስነስቷል። በመካነሰላም ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች የዩኒቨርስቲ ግንባታው እድል ለእኛ ወረዳ ሊሰጥ ይገባል፣እኛ ከሁሉም ወረዳዎች ለዞኑ መናገሻ ከተማና ለወሎ ዩኒቨርስቲ በከፍተኛ እርቀት ላይ ስለምንገኝ የዩኒቨርስቲ የመገንባቱ እድል ለእኛ ሊሰጥ ይገባል፣………… ወዘተ የሚሉ መከራከሪያዎችን በመያዝ አቤቱታና ቅሬታቸውን ለመንግስት ሀላፊዎች ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይህን ተከትሎም ዩኒቨርስቲው ሊገነባበት ከታሰበውና የመሰረት ዲንጋይ ከተጣለበት የለጋምቦ (አቃስታ) አካባቢ ወደ መካነ ሰላም (ቦረና) እንዲዛወር መወሰኑን ተከትሎ ሲካረር የነበረው ግጭት በመገንፈል በወረዳዎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት አስነስቷል። በዛሬው እለት የመቅደላ ዩኒቨርስቲ ግንባታ እድል ተሰጥቶ የተነሳቸው የለጋምቦ (አቃስታ) ወረዳና አጎራባች ወረዳዎች እንዲሁም እድሉ ተነጥቆ የተሰጣቸው የመካነሰላም ወረዳ ነዋሪ ህዝቦች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በለጋምቦ ወረዳ ነዋሪዎችና በአስተዳደሩ አካላት በተቀሰቀሰ ግጭት እስከ 12:00 ድረስ ባለኝ መረጃ 1 ሰው ሲገደል ሁለት የፓሊስ አባላት ክፋኛ መቁሰላቸውንና የለጋምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ እስካሁን ያለበት አለመታወቁን የደረሰኝ መረጃ ያመለክታል። ግጭቱን ተከትሎ ተጨማሪ የአድማ በታኝና ልዩ ሀይል ጦር ከደሴ በበርካታ ተሽከርካሪ ተጓጉዞ በአካባቢው መድረሱ ሲታወቅ ከደሴ— መካነሰላም የሚደረገው መደበኛ የህዝብ ትራንስፓርት አገልግሎት መቋረጡንም ከስፍራው ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግጭቱ በየወረዳዎቹ የመንግስት ሀላፊዎች ላይ ያነጣጠረበት ሁኔታ ለድርጊቱ ተጠያቂ ናቸው የሚል አዝማሚያ በመኖሩና የህዝቡ ቁጣ በማየሉ፣ ግጭቱ ከዚህ እየከፋ እንደሚሄድና ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ማምሻውን በደረሰኝ መረጃ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በሚገኙ ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰኑ አጎራባች ወረዳዎች በአፋርና በኦሮሞ ተወላጆቸ መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ያለ ሲሆን የግጭቱን መንስኤና በውጊያው ስለደረሰው ጉዳት መጠን ለማወቅ ያደረኩት ጥረት አልተሳካም። ነዋሪዎች በሽሽት ላይ መሆናቸውንና አንዳንድ አሽከርካሪዎች በግጭቱ አካባቢ ወደአዲስ አበባ የሚያደርጉትን ጉዞ መሰረዛቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ። በሁለቱ ግጭቶች ዙሪያ ሰፊና ዝርዝር መረጃዎች ይዤ እመለሳለሁ።

ዘሪሁን ገሰሰ

Freedom4Ethiopian

Leave a Reply