በጥበቡ በለጠ
እኚሁ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ አመራር ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ከኔ መፅሐፍ ታገኙታላችሁ፤ የመፅሐፌን ሕትመት ጠብቁ አሉን። የበዓሉ ግርማ ሞት፣ ስቃይ፣ መከራው፣ እንዲሁም ደግሞ የባለቤቱን እና የልጆቹን ከ30 ዓመታት በላይ የቆየ መራር ሐዘን እናስበው። በጣም ከባድ ነው! ግን ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ ይህን የግድያ እና የመሪር ሃዘን ታሪክ መጽሐፋቸውን ማሻሻጫ አድርገው ሊጠቀሙበት መዘጋጀታቸውን ሳስበው በእጅጉ አዝናለሁ።ኢትዮጵያን ከ1966- 1983 ዓ.ም ለአስራ ሰባት ዓመታት በመራት የደርግ መንግሥት ውስጥ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ በቅርቡ አንድ መግለጫ የሚመስል ጉዳይ ተናግረው ነበር። የተናገሩት በጓደኛቸው የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ነው። ጥያቄው በዘመነ ደርግ ውስጥ አድራሻው ስለጠፋው ድንቅዬ የኢትዮጵያ ደራሲ ስለ በዓሉ ግርማ ነበር። በዓሉ ግርማ እንደተገደለ ቢጠረጠርም ማን ገደለው? በምን ምክንያት? የት ተገደለ? የት ተቀበረ? የሚሉትና በርካታ ጥያቄዎች ቢቀርቡም እስከ አሁን ድረስ ምላሽ የሰጠ የደርግ ባለስልጣን አልነበረም። ግን ይህ የበዓሉን የሞት ምስጢር ይፋ አወጣለሁ ያሉት እኚሁ የደርግ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ ናቸው። በሐምሌ ወር ውስጥ ታትሞ የሚወጣ መጽሐፍ አለኝ፤ በዚያ መፅሐፍ ውስጥ ምስጢሩን ታገኙታላችሁ ብለው ልባችንን ሰቅለውን ቆይተው ይኸው ሐምሌ ወር አለፈ። መፅሐፋቸውም አልወጣም!

በዓሉ ግርማ የተገደለው ወይም ደብዛው የጠፋው ኮ/ል ፍሰሃ እና ጓደኞቻቸው በሚመሩት መንግሥት ውስጥ ነው። ግድያውም የመንግሥት እጅ እንዳለበት በርካታ አመላካች ነገሮች አሉ። ከነዚህም ውስጥ በዓሉ ግርማ ከስራው መታገዱ፣ ከዚያም ደግሞ ደብዛው ሲጠፋ መንግሥት ይፋ መግለጫ አለማውጣቱ እና ጉዳዩን በዝምታ ማለፉ ዋነኛ ማስረጃዎች ናቸው።

በዓሉ ግርማ ኦሮማይ የተሰኘው ረጅም የልቦለድ መፅሐፉ በ1975 ዓ.ም ታትሞ ከወጣ በኋላ የመንግሥትን ገመና ዘክዝኮ አወጣው በሚል ሰበብ መፅሐፉ ከገበያ ላይ ተለቅሞ ተወስዷል። መፅሐፉን በእጁ የያዘ፣ ሲያነብ የተገኘ ሰው የሚወስድበት እርምጃም ዘግናኝ ነበር። ስለዚህ ለበዓሉ ግርማ ሞት፣ የደርግ መንግሥት እጁ እንዳለበት የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን እየጨመርን መናገር እንችላለን።

በጣም የሚገርመው ነገር እስከ አሁን ድረስ በዓሉ ግርማን የበሉት ጨካኞች መናገር አልቻሉም ነበር። ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ ደግሞ ጥሩ የመፅሐፍ ማሻሻጫ ርዕስ አድርገውት ሊጠቀሙበት ተዘጋጅተዋል። የደርጉ መሪ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም “ትግላችን” ብለው መፅሐፍ አሳትመው ብዙ ተወቅሰውበታል። የዚያው መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሻምበል ፍቅረሥላሴ የወግደረስ ደግሞ እኛ እና አብዮቱ ብለው ግዙፍ መጽሐፍ ቢያሳትሙም መፅሐፋቸውን “ንሰሃ አልገቡበትም” በሚል ከግራና ከቀኝ ከፍተኛ ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። መንግሥቱ ኃይለማርያም እና ፍቅረስላሴ የወግደረስ የበዓሉ ግርማን ግድያ በተመለከተ የሰጡን መረጃ የለም። እነዚህ ሁለት ሰዎች ዋነኞቹ የደርግ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ናቸው። ምናልባት በመፅሐፋቸው ውስጥ ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ጽፈው ቢሆን ኖሮ ወይም ተናዘው ቢሆን የመፅሐፎቻቸው ተቀባይነት በተወሰነ ደረጃ ከፍ ይል ነበር።

የመንግሥቱንና የፍቅረስላሴን ደካማነት ያስተዋሉ የሚመስሉት ፍሰሃ ደስታ በመፅሐፌ ውስጥ የምትወዱት፣ ከ30 ዓመታት በላይ ስለ በዓሉ መረጃ ስትፈልጉ ለባዘናችሁት ሁሉ መፅሐፌ መልስ አለው ብለውን ድፍን አንድ ወር በጭንቅ ስንጠባበቅ ቆየን። መፅሐፉ አልወጣም፤ ቢወጣስ ምን ይነግሩን ይሆን?

“በዓሉን የገደልነው እኛ ነን” ይሉን ይሆን? “ቁጭ ብለን ተነጋግረንበት፣ እከሌ ይህን አስተያየት ሰጥቶ፣ እከሌ ደግሞ ይህን ብሎ፣ ከዚያም ግድያው ተፈፃሚ ሆነ” ብለው የንሰሃ ፅሁፍ ያቀርቡልን ይሆን? ያንን ካደረጉ የሚደነቁበት ነጥብ ሊያዝላቸው ግድ ይላል።

ገነት አየለ በፃፈችው “የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” በተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ መንግሥቱ ኃይለማርያም ስለ በዓሉ ግርማ አሟሟት ጥያቄ ተነስቶላቸው ሰፊ ነገር ተርከዋል። ትረካቸው እሳቸውና በዓሉ የት እንደሚተዋወቁ፣ ከዚያም የቀረበ ወዳጅነት እንደገነቡ፣ በዓሉም ስለ እርሳቸው አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው ኮ/ል መንግሥቱ ተናግረዋል። በግድያው ውስጥ ግን እጃቸው እንደሌለ ገልፀዋል።

ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ

በርግጥ የበዓሉ ግርማ እና የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም የቅርብ ግንኙነት እንደነበራቸው በሰፊው ይነገራል። በዓሉ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ንግግር ሁሉ ይፅፍ ነበር ይባላል። ቤተ-መንግስት እንደ ልቡ መውጣትና መግባት የሚችል ሰው ነበር እያሉ የሚተርኩ አሉ። ሻዕቢያን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ “የቀይ ኮከብ ዘመቻ” በተካሄደበት ወቅትም መንግሥቱ ኃይለማርያም የቅርብ ሰው አድርገውት በዓሉ ግርማን ወደ አስመራ ይዘውት እንደሄዱ ይተረካል። ለበዓሉ ግድያ ምክንያት ነው ተብሎ የሚጠቀሰው ኦሮማይ በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥም ስለ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም የፃፈው ሃሳብ የአድናቆት በመሆኑ እርሳቸው የግድያ ምላጫቸውን በዓሉ ላይ አይስቡትም የሚሉ ሰዎች አሉ።

 

የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ሞልቬር Black Lions ወይም ወደ አማርኛ ስንመልሰው “ጥቋቁር አናብስት” በሚል ርዕስ ግሩም የሚባል መፅሐፍ አለው። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን የሕይወት ታሪክ ነው የፃፈው። ከነዚህ ታላቅ ደራሲያን ውስጥ በዓሉ ግርማ በመፅሐፉ ውስጥ ፎቶውም ታሪኩም ጎልቶ ነው የተፃፈለት። ታዲያ ሞልቬር የበዓሉን አሟሟት በተመለከተ የተቻለውን ያህል  መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። ሞልቬር አንዳንድ የስርዓቱን ከፍተኛ አመራር የነበሩትን ሰዎች ጠይቆ እንደተረዳው በዓሉ ግርማን ባለው የፖለቲካ አመለካከት እና በግል ጥላቻም ጭምር አብረውት ይሰሩ የነበሩ ጓደኞቹ በጠላትነት ተሰልፈውበት እንደነበር መፅሐፉ ይተርካል። እነዚህ ሰዎችም እነማን እንደነበሩ ስማቸውን ሁሉ ጽፎ ዘርዝሯል። በነገራችን ላይ መንግሥቱ ኃይለማርያምም የበዓሉ ግርማ ጠላቶች ጓደኞቹ ናቸው በማለት ስማቸውን ከጠቀሷቸው ውስጥ አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ይገኙበታል።  ሙሉጌታ ሉሌ “ጦቢያ” በተሰኘው መፅሔት “ፀጋዬ ገ/መድህን አርአያ” በሚል የብዕር ስም ፖለቲካዊ ፅሁፎችን በተከታታይ የሚያቀርቡ ነበሩ። ዛሬ ኑሯቸውን ሰሜን አሜሪካ አድርገዋል።

ገነት አየለ “የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች” በሚለው መፅሐፏ ውስጥ የበዓሉ ጠላቶች ተብለው ስማቸው ከተጠራው ውስጥ ሙሉጌታ ሉሌ መሆናቸውን በመግለጿ በ“ጦቢያ” መፅሔት ላይ ሙሉጌታ ሉሌ ራሳቸው ነበልባል የሆነ የተቃውሞ ምላሽ ለገነት አየለ ሰጥተዋል። እንደውም መንግሥቱ ይህን አይሉም፣ ይህ የገነት አየለ የራሷ ሴራ ነው የሚል ሃሳብ ያለው ምላሽ ሰጥተዋታል።

የበዓሉ ግርማ ጠላቶች (ገዳዮች) አንድ ግዜ መንግሥት ነው፣ ሌላ ጊዜ የቅርብ ጓደኞቹ እጅ አለበት ሲባል ቆይቷል። ሌላ ሶስተኛም ጥርጣሬ ሲሰነዘር ቆይቷል። በዓሉን የገደሉት (ያፈኑት) የኤርትራ ተገንጣዮች (ሻዕቢያ) ነው የሚል አስተያየትም ነበር።  ምክንያቱ ደግሞ በዓሉ “ኦሮማይ” በተሰኘው መፅሐፉ ሻዕቢያን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ስትራቴጂ ነድፎ ያሳየበት በመሆኑ የድርጅቱ ዘላለማዊ ጠላት ነው በሚል ተፈርጆ ነው በማለት ግድያውን ወደ ሻዕቢያን የሚያላክኩ አሉ።

ደመ ከልብ ሆኖ 31 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢትዮጵያዊው ድንቅዬ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የሕይወት ፍፃሜ ባለመታወቁ ሁሌም እንደጠየቅን በመኖር ላይ ነን። አንድ ጊዜ ደግሞ ይህን ጉዳይ በሬዲዮ ፋና አዲስ ጣዕም ተብሎ በሚታወቀው ፕሮግራማችን ላይ ስናቀርበው የሰማ የደርግ መንግሥት መኮንን የነበረ ሰው አንድ እሱ የሚያውቀውን ምስጢር ነገረን።

ይህ የደርግ መኮንን ያጫወተን ታሪክ የበዓሉ ግርማ ገዳይ አንድ የእርሱ ጓደኛ የነበረ የደርግ ደህንነት አባል እንደሆነ ጠቆመን። ይህ የደርግ ደህንነት መጠጥ ሲጠጣ፣ ሞቅ ሲለው “በዓሉን የገደልኩት እኔ ነኝ!” እያለ በሀዘንና በለቅሶ ይነግረኝ ነበር ብሎናል። ታዲያ ይህን የሚለው ሲሰክር ነው። ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንደሚባለው ነው። ያ የደርግ ደህንነት ዛሬ በሕይወት የለም። ነገር ግን ድርጊቱን የፈፀመው በትዕዛዝ እንደሚሆን ሰውየው አጫውቶናል። ይህን ሰው ስሙንና ማንነቱን መግለፅ ያልፈለኩት ጉዳዩን ከሌላ ወገን ማጣራት ስላልቻልኩ ነው። ግን የበዓሉ ግርማ ገዳይ ነው ተብሎ በዋናነት የሚጠረጠረው የደርግ መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች ምስጢሩን አፍነው ቢይዙትም ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ ደግሞ የመፅሐፋቸው አውራ ታሪክ አድርገው ምን ሊነግሩን እንደፈለጉ አላውቅም።

በዓሉ ግርማ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ አለም ውስጥ ዘመን የማይሽራቸውን ስድስት ተአምረኛ መፃሕፍትን አሳትሞ የሞትን ጽዋ የተጎነጨ ድንቅ ደራሲ ነው። መፅሐፎቹም በቋንቋም፣ በሃሳብ፣ በይዘት. . . ወደር የማይገኝላቸው የዘመናዊ ሥነ-ፅሁፍ ቅርስ ናቸው። እነዚህ መፅሐፎቹ

1.  ከአድማስ ባሻገር

2.  የህሊና ደወል

3.  የቀይ ኮከብ ጥሪ

4.  ደራሲው

5.  ሀዲስ

6.  ኦሮማይ የሚሰኙ ናቸው።

በዓሉ ግርማ ከቤት እንደወጣ ሳይመለስ የቀረው ልክ በነሐሴ ወር 1976 ዓ.ም ነበር። የዛሬ 31 ዓመት ማለት ነው። ይህን ደራሲ ዛሬ ያስታወስኩት በሁለት ነገሮች ነው። አንደኛው ኮ/ል ፍሰሃ ደስታ የበዓሉ ግርማን ጉዳይ በሐምሌ ወር ጠብቁ፤ እኔ በማሳትመው መጽሐፍ ውስጥ ሁሉንም ነገር ታገኛላችሁ ብለውን ስለነበር ስጠብቅ ቆይቼ ወሩ ስላለቀብኝ ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ በዓሉ ከሚወዳቸው ልጆቹ፣ ከሚወዳት ባለቤቱ፣ እንደ ብርቅ ከሚሳሱለት እናቱ እና ከኢትዮጵያ የሥነ-ጽሐፍ ዓለም በአፀደ ስጋ የተለየው በዚህ በነሐሴ ወር 1976 ዓ.ም ስለሆነ፣ በጨረፍታም ቢሆን ልዘክረው ፈልጌ ነው።

በ1920ዎቹ መጨረሻ ላይ በቀድሞው የኢሊባቡር ክፍለ ሀገር ሱጴ ቦሩ በምትባል ትንሽዬ ከተማ የተወለደው በዓሉ ግርማ፣ አባቱ ከሕንድ ሀገር ከጉጅራት ግዛት መጥተው፣ እናቱ ደግሞ ሱጴ ቦሩ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ ናቸው። ከሕንድ እና ከኢትዮጵያ ዘር የተገኘው በዓሉ ግርማ አባቱን በስርዓት አያውቀውም። ገና በዓሉ ህጻን ሳለ ነው አባቱ ባቡ ወደ ሕንድ ሀገር የሄደው። ከዚያም ተያይተውም ሆነ ተገናኝተው አያውቁም።

በ10 ዓመቱ አዲስ አበባ መጥቶ ት/ቤት የገባው በዓሉ አፉን የፈታው በኦሮምኛ ቋንቋ ነበር። ቄስ ት/ቤት ገብቶ ከፊደል ጀምሮ ያሉትን የቤተክህነት ትምህርቶች እሳት የላሰ ተማሪ ሆኖ ወደ ዘመናዊ ት/ት ተቀላቀለ። በልዕልት ዘነበወርቅ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እና በጀነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሮ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ በማህበራዊ ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት በድግሪ ከተመረቀ በኋላ ወደ አሜሪካ ሀገር ሔዶ በፖለቲካ ሳይንስ እና በጋዜጠኝነት የማስተርስ ድግሪውን ተቀብሏል።

ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያም ተመልሶ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በመነን መጽሔት፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርቷል። ውብ መጣጥፎችንም ፅፏል። በኋላም የማስታወቂያ ሚኒስቴር መሰረታዊ ድርጅት ፀሐፊ ሆኖ ሰርቷል።

በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ እጅግ በርካታ የድግሪ፣ የማስትሬት፣ የዶክትሬት መመረቂያ እና የተለያዩ ጥናቶች የተሰሩበት ደራሲ ለመሆን የበቃም ሰው ነው።  የበዓሉ ስብዕና ኃያል ነው። ከኢትዮጵያዊያን አልፎ “ከአድማስ ባሻገር” የተሰኘው መፅሐፉ ሳይቀር ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተተርጉሞለታል። ቴአትር ተሰርቶበታል። ስለዚህ ይህ ሰው ተራ መፅሐፍ ማሻሻጫ ታሪክ እንዳይፃፍበት ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል ነኝ። ደርጎች ከገደሉት በኋላም፣ ታሪኩን መፅሐፍ አድርገውት ሲጠቀሙበት ማየት ሕሊና ላለው ሰው የሚቀፍ ይመስለኛል። ለማንኛውም ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ አበራ፣ በነሐሴ ወር 1983 ዓ.ም ለሞት ያበቃውን ኦሮማይ የተሰኘውን መፅሐፉን በድጋሚ ስታሳትመው በፃፈችለት መግቢያ የዛሬውን ፅሐፌን ልደምድመው።

ማስታወሻ

“ሐቅን ለማሳወቅ ራሱን አሳልፎ ለመታሰር፣ ለመሰቃየት፣ ለሞት የበቃ፣ ልጆቼን፣ ቤተሰቤን ሳይል ታፍኖ ወጥቶ የቀረውን ተወዳጅ ደራሲ ባለቤቴን በጣም አከብረዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ።

“በሚወዳቸው ልጆቹና በእኔም በባለቤቱ ላይ ከፍተኛ ሀዘንና ጭንቀት ቢደርስብንም አንማረርበትም፤ ለእውነት መቆምን በተግባር ያስተማረን ነውና።

“. . . እውነት ጊዜዋን ጠብቃ እነሆ ዛሬ የህይወት መስዋዕት የተከፈለበት ይህ መፅሐፍ ለመታተም በቅቷል።

“እኔም ሆንኩ ልጆቼ እያስታወስነው፣ እያከበርነው እንኖራለን፤ ከሱ የሚበልጥብን የለምና። ፍርዱን ግን ለሰፊው ሕዝብ እተወዋለሁ”

አልማዝ አበራ

ነሐሴ 1983 ዓ.ም

Mereja.com

Leave a Reply