ይህ አልበቃ ብሎ፣ ቀሪዎቹን ከ222 በላይ የሆኑ አባወራዎች ከእነቤተሰቦቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲገደሉ በአካባቢው ገዢዎች በመወሰኑ፣ ሰዎቹ ሕይዎታቸውን ለመታደግ ጫካ መግባታቸውን እና ይህን ተከትሎም የጉምዝ እና የሽናሻ ነገድ ሚሊሻዎች አድነው እንዲገድሉ ታዝዘው በአደን ላይ መሆናቸውን እማኞች አስረድተዋል። እንደእማኞቹ አገላላጽ «የሞቱት ሞተዋል፣ የሚመልሳቸው የለም። መነሳትና መተባበር ያለብን በእነዚህ በሕይዎት ባሉ ወገኖቻችን ላይ እንዳለፉት እጅግ በከፋ መልኩ ግድያ እንዳይፈጽሙባቸው የዓለም ማኅበረሰብ፣ ከሁሉም በላይ በማለቅ ላይ ያለው የዐማራው ነገድ ወገኖቹን ለመታደግ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ እሪታና ጥሪያቸውን አሰሙ» ነው ያሉት።
ባለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት የትግሬ-ወያኔዎች አገዛዝ ከ፭ ሚሊዮን የማያንሱ ዐማሮችን በተለያዩ ዘዴዎች የዘር ማጥፋት እንደፈጸመባቸው የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና ታዋቂ ምሁራን ከራሳቸው ከወያኔ መረጃዎች ላይ በመነሳት ባደረጉት ጥናት አረጋግጠዋል። ከዚህም በተጨማሪም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዐማሮች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዘር ማጽዳት ዘመቻ መፈናቀላቸው ይታወቃል። በዓለማችን ላይ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሲፈጸሙ መንግሥታትም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድምፃቸውን ያላሰሙበት ጊዜ አለ ለማለት አይቻልም። በአሁኑ ዘመን እንኳን ለሰብዓዊ ፍጡር ይቅርና ለደቂቅ ተሕዋስያን ሣይቀር የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደአሸን የፈሉበት ጊዜ ነው። በሚያሣዝን መልኩ ግን ባለፉት ፳፬(ሃያ አራት) ዓመታት የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ፣ በዐማራው ላይ ይህን ሁሉ የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀሎች ሲፈጽም አንድም የዓለም መንግሥታት አካልም ሆነ የሰብዓዊ መብት ድርጅት በይፋ ድርጊቱን ያወገዘበት ጊዜ የለም።
ይህ ድርጊት እንደተፈጸመ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ለ(ኢትዮጵያ) ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)፣ ለአሜሪካን ድምፅ የአማርኛው ቋንቋ አገልግሎት (ቪኦኤ)፣ ለኢትዮጵያ የሣቴላይት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን (ኢሣት) እንዲሁም ለሌሎች አካሎች እንዳሣወቁ ገልጸዋል። ሆኖም በዐማራው ላይ የሚፈጸመው በደል እኒህ ተቋሞች ለሚያራምዱት አጀንዳ ሚዛን የሚደፋ ጉዳይ ስላልሆነ፣ እንኳን በመቶ የሚቆጠሩ ዐማሮች መገደል ይቅርና፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዐማሮችም ደብዛቸው ጠፍቶ ሲቀር ጉዳይ እንዳላሉት ሁሉ፣ ይህንንም አሣዛኝ እና አሠቃቂ ዜና ትኩረት አልሰጡትም። እኒህ ተቋሞች ምናልባት የዐማራውን ዕልቂት በዝምታ የሚያልፉት የዐማራው ነገድ ተወላጆች ራሣቸው በየጊዜው በወገኖቻቸው ላይ ለሚደርሰው ዕልቂት «ጆሮ ዳባ ልበስ» በማለታቸው «ራሱ ተበደልኩ ሳይል እኛ ምን አግብቶን ተበደልክ እንላለን» ብለው ይሆን? ወይስ ዐማራውን እንደሰብዓዊ ፍጡር ስለማይቆጥሩት? ወይስ የ፲፰፻፹፰ ዓ.ም. የዐድዋ ድል በምዕራባውያን ላይ የፈጠረው የመንፈስ ስብራት «ዐማራውን ካላጠፋን፣ የእኛ የበላይነት ተጠብቆ አይዘልቅም» የሚለው ስጋቻቸው አይሎባቸው እና ይህን ሥጋቻቸውን «እርስ በእርሱ ሥጋን በኩበት ጥበሱ » እንዲሉ፣ ባሰለጠኑዋቸው የትግሬ-ወያኔ ባንዳዎች አማካኝነት ዐማራውን እስከወዲያኛው እንዲያጠፋ ፈልገው?
ለእነዚህ ጥያቄዎች የዐማራው ነገድ አባሎች ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ ቁጭት እና እልክ ውስጥ ገብተው በነገዳቸው ተወላጆች ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ሊቋቋሙት ይገባል። ከሁሉም በላይ በጠላት ተከብበው፣ የሚልሱት እና የሚቀምሱት አጥተው፣ ሞትን ከቅርብ ርቀት በመጠባበቅ ላይ ላሉት ወገኖቻችን ከነፍስ አድን እስከ ነፃነት ድረስ ለሚሹት ጉዳይ ሳናመነታ በድምፃችን፣ በገንዘባችን እና በእውቀታችን እንድንደርስላቸው ሞረሽ ወገኔ በተጎጂ ወገኖቻችን ስም ጥሪውን ያቀርባል።
ዐማራን ከፈፅሞ ጥፋት እንታደጋለን!
ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
ኢትዮጵያ በታማኝ እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!