Wednesday, 19 August 2015 

አሜሪካ በሱዳን ላይ ማዕቀብ ከጣለች 18 ዓመታት ተቆጠሩ። እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም አሜሪካ በሱዳን ላይ ማዕቀብ ስትጥል ሀገሪቱ በዋነኝነት ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በማለት ነበር። በጊዜው በሱዳን እ.ኤ.አ ከ1991 እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ የቀድሞው የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢላደን ነዋሪነቱ በዚያው በሱዳን ነበር።

 

ከዚህም ባለፈ ሱዳን በግብፅ ይንቀሳቀሱ የነበሩ እስላማዊ ታጣቂ ሀይሎችንም  በስልጠና እና በትጥቅ ከመደገፍ ባለፈ በመጠለያነትም እያገለገለ ነው በሚል ተጨማሪ ክስ ሲሰማበት ቆይቷል። በዚያው በሱዳን የነበሩ የግብፅ ታጣቂ ሀይሎች አዲስ አበባ ሰርገው በመግባት ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ የገቡትን የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ለመግደል ሙከራ ማድረጋቸውም ሱዳን የበለጠ የማዕቀብ ኢላማ ውስጥ እንድትገባ አደርጓታል።

 

በዚህም የሱዳን መንግስት “አካባቢው እንዳይረጋጋ ይሰራል” በሚልና በዋነኝነትም “በሀገር ደረጃ ሽብር ደጋፊ ሀይል ነው” በሚል አሜሪካ በግሏ በሀገሪቱ ላይ ማዕቀብ ከጣለች ሁለት አስርት አመታት ሊቆጠሩ ሁለት አመታት ብቻ ናቸው  የቀሩት። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ በተደጋጋሚ በሰብዓዊ ጥሰት መከሰሷ፣ ከዚህም ባለፈ የሀገሪቱ መሪ ኦማር አልበሽር በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዢያ የተቆረጠባቸው መሆኑም ሌላኛው የሱዳን ውስብስብ ፖለቲካ ሆኖ ቆይቷል። ሱዳን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን የአስተዳደር ዘመን የኢኮኖሚ ማዕቀቡ ከተጣለባት በኋላ የዚሁ ማዕቀብ ቀጣይነት በቡሽ አስተዳደር ከዚያም በኦባማ የስልጣን ዘመን እንዲራዘም ተደርጓል።

 

ሱዳን ከዚህም ባለፈ “ከኢራን ጋር  የሽብር ስራዎች በጋራ ትስራለች” በሚልም ሌላ ክስ ሲሰማባት ቆይቷል። በተለይም በእስራኤል ላይ ጥቃትን የሚሰነዝሩ ታጣቂ ኃይሎችን በግዛቷ ታሰለጥናለች እንደዚሁም ከኢራን ተወንጫፊ መሳሪያዎችን እየተቀበለች አከማችታ ለታጣቂ ሀይሎቹ በተለይም ለሀማስ ታስረክባለች በሚል በእስራኤልና በአሜሪካ ስትወነጀል ቆይታለች። ይህ ውንጀላ ዛሬም እንዳለ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የሀገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም ሳይቀር የእስራኤል አየር ኃይል ነው ተብሎ በሚጠረጠር  ወታደራዊ ሀይል ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶበታል።

 

ይህ በሆነበት ሁኔታ የኦባማ አስተዳደር በኢራን ላይ ያውም በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ አድርጓል። የኦባማ አስተዳደር ከዚህም ባለፈ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በዲፕሎማቲክ እሰጣ አገባ ውስጥ ከነበረችው ኩባ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመቀየር የጀመረውን ጥረትም ዳር ወደ ማድረሱ ላይ ነው። በኩባ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የአሜሪካ ኤምባሲ በቅርቡ በይፋ ተከፍቷል። በአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ የተጎዳው ክፉኛ  የኩባ ኢኮኖሚ በቅርቡ የተሻለ መነቃቃት ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሱዳን ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያት ክፉኛ ጉዳት ደርሶበት ቆይቷል። ፕሬዝዳንት ኦባማ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው የማጠናቀቂያ ጊዜያቸው እየተቃረበ ነው። ለቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻው እጩ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ የሪፐብሊካን እና ዴሞክራት ፓርቲ እጩ  ተወካይ ተወዳዳሪዎች ሰፊ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ናቸው።

 

የኦባማ አስተዳደር ከኢራን ብሎም ከኩባ ጋር የነበረውን የቀደመ ግንኙነት በተወሰነ ደረጃ ለመለወጥ ጥረት ያደረገበት ሁኔታ ቢኖርም ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን የተበላሸ ግንኙነት ለማሻሻል  ግን ያሳየው ምንም አይነት ጥረት የለም። ይሄንንም ተከትሎ ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋ በማዕቀቡ ክፉኛ በመጎዳቱ የኦባማ አስተዳደር ችግሩን እንዲመለከትም በቅርቡ አንዳንድ ጥረቶች ተጀምረዋል። ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት ወቅትም ጉዳዩን አስመልክቶ በሱዳናውያን በኩል የተማፅኖ ደብዳቤም እንዲደርሳቸውም የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከክሊንተን ወደ ቡሽ እንደዚሁም ከቡሽ ወደ ኦባማ እንደተላለፈው ሁሉ በቀጣይም ከፕሬዝዳንት ኦባማ ወደ መጪው የፕሬዝዳንት ዘመን እንዳይተላለፍ ፅኑ ፍላጎት ያደረባቸው ሱዳናውያን የዲፕሎማቲክ ዘመቻቸውን ጀምረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአዲስ ድሪምላይነር ሆቴል የሁለት ቀናት ስብሰባ ተካሄዷል። ከስብሰባው ጋር በተያያዘ በአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል ካውንስል ጋር በጋራ በመሆን ሱዳን ተወካዮች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል። ጋዜጣዊ መግለጫው በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በአንድ መልኩ በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር በተያያዘ በተለይ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር የአለም አቀፉ ወንጀል የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው መሆኑን ተከትሎ የተፈጠረውን ውስብስብ የሀገሪቱን ፖለቲካ ሰፋ ባለ መልኩ ለማስረዳት የሞከሩት  የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል ካውንስል ሊቀመንበር የሆኑትፕሮፌሰር ጆሴፍ ቺሊንጌ ናቸው። ከዚያ በመቀጠል ሱዳን አሜሪካ በተናጠል ከጣለችባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጋር በተያያዘ ምን ያህል በማዕቀቡ ኢኮኖሚዋ እየተሽመደመደ እንደመጣ ሰፋ ባለ መልኩ ያስረዱት ሱዳናዊው የኢኮኖሚ ኤክስፐርት ዶክተር ባንኪር ሞሀመድ ቶም ናቸው። ሱዳን በአሜሪካ ከተጣለባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጋር በተያያዘ ለሁለት አስርት አመታት ያህል የተጎዳው ኢኮኖሚዋ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ወደ መንበርከኩ እየደረሰ ይመስላል። ሀገሪቱ ከማዕቀቡ ጋር በተያያዘ የደረሰባትን ከባድ ክስረት ለመቋቋም ኳታርንና ሳዑዲን በመሰሉ ሀገራት በብዙ መልኩ ስትታገዝ ብትቆይም እገዛው አሁን ካለበት በላይ መቀጠል የቻለ አይመስልም።

 

አሜሪካ ቀደም ሲል በጠላትነት ከፈረጀቻቸው ሀገራት ጋር የነበራትን የከረረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ማለዘብና ወደ ማሻሻሉ ሁኔታ እየገባች ነው። ሱዳንም ቢሆን የቀደመው የሁለቱ ሀገራት የጥላቻ ግንኙነት ተሸሮ ነገሮች ወደ በጎ መስመር እንዲገቡ እጅግ ዘግይታም ቢሆን በቅርቡ አዲስ የዲፕሎማሲ ዘመቻን ጀምራለች።

 

ሱዳናውያኑ በዚሁ በአዲስ አበባው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ማዕቀቡ በሱዳን ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን አሉታዊ ተፅዕኖም በተመለከተም ለጋዜጠኞች ገለፃ  አድርገዋል። ከዚሁም ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ በርካታ ጉዳቶች ደርሰውባታል። ከፍተኛ የእዳ ጫና ያለባቸው ሀገራት የእዳ ጫናቸው የሚሰረዝበት አለም አቀፍ አሰራር አለ። በዚህ ረገድ ተጠቃሚ  ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። በሱዳን የኢኮኖሚ ኤክስፐርት የሆኑት ዶክተር ባንኪር ሞሃመድ ሱዳን 46 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ጫና ያለባት ሀገር መሆኗን ገልፀው ይሁንና በርካታ የእዳ ጫና ያለባቸው ሀገራት በአበዳሪዎቻቸው በኩል እዳቸው እንዲሰረዝ ሲደረግ ሱዳን ግን አሜሪካ ከጣለችባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጋር በተያያዘ የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን አለመቻሏን አመልክተዋል። እዳው እንዲሰረዝ የሚያስፈለጉት ሁሉም መመዘኛዎች ተሟልተው እንደነበርም ባለሙያው ጨምረው ገልፀዋል።

 

ሀገሪቱ የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተለያዩ ጥረቶችን ብታደርግም ማዕቀቡን ተከትሎ እስከዛሬም ድረስ የተገኘው ውጤት ከሚጠበቀው በእጅጉ ያነሰ ነው። የአውሮፓና የእስያ ታላላቅ ባለሀብቶች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በአሜሪካ የገንዘብ ተቋማት በኩል የሚሰሩ መሆናቸው ማዕቀቡን ተላልፈው በሱዳን መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ ያደረጋቸው መሆኑን  ባለሙያው አመልክተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ተከትሎም ከውጪ ወደ ሱዳን ገንዘብን ለማስገባት ገንዘብ አዘዋዋሪ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚጠይቁት የማዘዋወሪያ የገንዘብ መጠንም ከፍተኛ ነው ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ በመርከብም ሆነ በአውሮፕላን እቃዎችን ወደ ሱዳን ለመጓጓዝ የሚጠየቀው የክፍያ መጠንም በዚያው መጠን አበረታች አለመሆኑን ዶክተር ባንኪር ጨምረው አመልክተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታላላቅ አለም አቀፍ ኩባንያዎች የአሜሪካንን ቅጣት በመፍራት በሱዳን መዋዕለ ነዋያቸውን ከማፍሰስ የተቆጠቡ መሆኑን አመልክተዋል።

 

የመንገደኞችና የጭነት አውሮፕላኖች አቅራቢ በመሆን የአለምን ገበያ በስፋት የተቆጣጠረው የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ ነው። ቆየት ብሎ ወደ ገበያው የገባው አውሮፓዊው ኤርባስ የቦይንግ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ገና በመስራት ላይ ነው። ያም ቢሆን የአውሮፕላኑ ኢንዱስትሪ ከሁለቱ ግዙፍ ኩባንያዎች የሚያልፍበት ሁኔታ አይኖርም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ሌሎች ሀገራት አየር መንገዶች ሁሉ የሱዳን አየር መንገድም የቦይንግ ኩባንያ ጥገኛ ነው። አየር መንገዱ በሀገሪቱ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተከትሎ አዳዲስ አውሮፕላኖችን እንደዚሁም መለዋወጫዎችን ማግኘት ባለመቻሉ ከገበያ እየወጣ መሆኑ ነው የተመለከተው። ዶክተር ባንኪር አየር መንገዱ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት በሃያ በመቶ አቅሙ ብቻ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ጉዳቱ የደረሰው በሱዳን አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን በሱዳን መርከብ ድርጅት ላይም ነው ተብሏል።

 

ሱዳን ለግብርና ምቹ የሆነ ሰፊ መሬትና ተስማሚ አየር ያላት ሀገር ናት። በግብርናው ዘርፍ ከጥጥ እስከ ቅባት እህሎች በስፋት ታመርታለች። ከዚህም በተጨማሪም ሰፋፊ በመስኖ የሚሰሩ የሸንኮራ አገዳ እርሻዎችና በማደግ ላይ የነበሩ የታላላቅ የስኳር ኢንዱስትሪዎችም ባለቤት ነበረች። እነዚህ ሁሉ ግን የማዕቀቡ ሰለባ ሆነዋል። ዶክተር ባንኪር የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከማዕቀቡ በፊት ሰባት በመቶ እድገት አስመዝግቦ የነበረ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ሰአት ግን ይህ እድገት ወደ ሁለት በመቶ ያሽቆለቆለ መሆኑን ገልፀዋል።

 

በአባይ ወንዝ ላይ ታላላቅ የኤሌክትሪክና የግብርና የመስኖ ስራዎችን ለመስራት በርካታ ፕሮጀክቶች የተነደፉበት ሁኔታ ቢኖርም ከኢኮኖሚው መድቀቅ ጋር በተያያዘ የገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ፕሮጀክቶቹ የቆሙ መሆኑ ነው የተመለከተው። የግብርናው ዘርፍ እድገትን ማሳየት ባለመቻሉ በርካታ ሱዳናውያን መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ካርቱምን ጨምሮ ወደተ ተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየፈለሱ መሆኑን ሱዳናውያኑ አመልክተዋል። የሀሪቱ የመገበያያ ገንዘብም እየወደቀ ነው፣ ግሽበቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው።

 

ይህ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ኮንግረንስ የትኛውም አለም አቀፍ ባለሀብት ከሱዳን ጋር ምንም አይነት የቢዝነስ ግንኙነት እንዳይኖረው እገዳን የሚጥል ውሳኔን እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም በማስተላለፉ የሱዳንን የውጪ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ክፉኛ ያሽመደመደው መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያው አመልክተዋል። ሱዳን ከዚያ ቀደም ብሎ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት በመሳቡ ረገድ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የውጪ ኢንቬስተሮች የማያዩዋት ሀገር ሆናለች ብለዋል።

ዶክተር ባንኪር የአሜሪካንና የሱዳንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲበላሽ አድርጎታል ካሏቸው መካከል አንዱ በሱዳን በነዳጅ ስራ ተሰማርቶ የነበረው አሜሪካዊው ቼፍሮል ኦይል እንዲወጣ ተደርጎ በምትኩ የቻይና እና የማሌዥያ ኩባንያዎች ቦታውን እንዲይዙ መደረጋቸው ነው።

 

ሱዳን ትሪብዩን በዚህ ሳምንት ባወጣው ዘገባ ሱዳን በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ የገባች መሆኗን አመልክቷል። የሱዳን ፓውንድ ከዶላር አንፃር ያለው የማዕከላዊ ባንኩ ምንዛሬ ጠንካራ ነው ሊባል የሚያስችለው ነው። አንድ ዶላር የባንክ ምንዛሪው በ 6 ነጥብ 1 የሱዳን ፓውንድ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን በጥቁር ገበያው አንድ ዶላር እየተመነዘረ ያለው ግን በ 9 ነጥብ 9 የሱዳን ፓውንድ ነው። የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ ከግለሰቦች ባለፈ መንግስት አንዳንድ ባንኮች ራሳቸው ዶላርን ከጥቁር ገበያ  ለመግዛት ተገደዋል።

 

የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ መንግስት የተፈጠረውን የውጪ ምንዛሪ እጥረት መፍትሄ እንዲያገኝ ለማድረግ ከሳዑዲአረብያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያገኘ መሆኑን ቢገልፅም፤ ተገኘ የተባለው የገንብ መጠን ግን የሱዳንን ፓውንድ ዋጋ ማጣት ሊያቆመው ስላልቻለ የገንዘቡ መገኘት እውነት የመሆኑን ጉዳይ ጥርጣሬ ውስጥ የጣለው መሆኑን ዘገባው ያመለክታል።

 

በሀገሪቱ የተፈጠረውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች የገበያውን ሁኔታ በመከታተል ዶላርን ለገዢዎች የሚያቀርቡና የሚገዙ ሲሆን መንግስት ከሰዑዲ አረብያ አገኘሁ ያለው አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሪ በጥቁር ገበያ እየናረ ያለውን የዶላር ዋጋ ለመቀነስ እንጂ ከዚያ ባለፈ እውነተኝነቱ አጠራጣሪ መሆኑን በርካቶች እየገለፁ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ  አመልክቷል። በሱዳን የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሲሆን አንዳንዶች ከዚህ ቀደም መንግስትን ለመቃወም አደባባይ እስከመውጣት የደረሱበት ሁኔታ ነበር። ሱዳናውያኑ ማዕቀቡ እንዲነሳላቸው ለፕሬዝዳንት ኦባማ ደብዳቤ ከመፃፍ ባለፈ በቀጣይም ሰፊ አለም አቀፍ ዘመቻ የሚያደርጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

Leave a Reply