AUGUST 21, 2015
‹‹እንሰሳት በዋሉበት እየቀሩ ነው›› ነዋሪዎች
በሀገሪቱ በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ምክንያት በተለይ በአፋር፣ በሶማሊና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ጎጃም ውስጥም በመከሰቱ በርካታ እንሰሳት እየሞቱ መሆኑንና ሰውም ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡ በተለይ ድርቁ በሶማ፣ አራራ፣ እነገ እና ሰንጠርጌ ቀበሌዎች ለበርካታ እንሰሳት ሞት ምክንያት ከመሆኑም ባሻገር ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ችጋር ተጋልጠዋል ተብሏል፡፡
ድርቁ አስከፊ ደረጃ እንደደረሰ መንግስትም ማመኑን የገለፁት ነዋሪዎች ነሃሴ 7/2007 ዓ.ም የእናርጅ እናውጋ የንግድና ኢንዱስትሪ ፅ/ቤት እንዲሁም የደብረወርቅ 01 ቀበሌ ሊቀመንበር የድርቁን አስከፊነት በመግለፅ ከህዝቡ እንዳታ ማሰባሰባቸውን ስብሰባው ላይ የተገኙት ነዋሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከእናርጅ መስቀለ፣ አረጋሚትና ሌሎችም ቀበሌዎች ገለባና ሌሎች ለከብቶች በምግብነት የሚውሉ መኖዎች ተሰባስበው በድርቅ ወደተጠቁት ቀበሌዎች መላኩን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
መንግስት እርዳታ ለማሰባሰብ የተገደደውና እርዳታ ማሰባሰብ የጀመረው በድርቁ የተጠቁት ቀበሌዎች ነዋሪዎች በዝናብ እጥረት የደረቀውን ሰብላቸውን በመያዝ፣ እንዲሁም በእንሰሳትና ሰው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመግለፅ ደብረወርቅ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣታቸውና በተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረባቸው ነው ተብሏል፡፡ በድርቁ የተጠቁት ነዋሪዎች ስለ ድርቁ ለመንግስት ሪፖርት ለማድረግ ወደ አካባቢው ያቀኑ የግብርና ሰራተኞችንና መኪናዎቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ በመያዝም መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው በቶሎ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደጠየቁም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ እስተዳደር ለድርቁ ሁለት መቶ ሽህ ብር መመደቡንና በስብሰባው ወቅትም 28 ሺህ ብር ተዋጥቶ በቆሎ ተገዝቶ እንዲላክላቸው ቢወሰንም እስካሁን እርዳታው ለድርቁ ተጠቂዎች እንዳልደረሰላቸው የገለፁት ምንጮች ሰው የሚበላው አጥቶ፣ እንሰሳትም በዋሉበት እየቀሩ ነው ብለዋል፡፡ አንድ የደብረወርቅ ነዋሪ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለፁት በዝናብ እጥረት ምክንያት በድርቅ ከተጠቁት ባሻገር ሌሎች የእናርጅ እናውጋ አጎራባች ቀበሌዎች ላይም ድርቁ በመከሰቱ በሰውና በእንሰሳት ላይ ጉዳት እንደረሰ ነው ብለዋል፡፡
posted by Aseged Tamene