ከታሳሪ የህሊና ሰዎች መካከል አብጦ ሊፈነዳ የተቃረበውን የፖለቲካ ድባብ ለማስተንፈስ ሲባል ወዳጄን፣ ጓዴንና የቀድሞ ባልደረባዬን አብርሀ ደስታን፣ የሽዋስ አሰፋን፣ ሐብታሙ አያሌውን፣ ዳኤል ሽበሽንና አብሃም ሰለሞንን «በነፃ» መለቀቅ በሰማሁ ጊዜ ደስታ ቢሰማኝም፤ ንጹሓኑ «በነጻ» መለቀቃቸው ከጠባቡ ጓንታናሞ ወደ ሰፊው ጓንታናሞ መዛወራቸው እንጂ አሁንም ነጻ አለመሆናቸውን፤ እንዴውም አሁን ያለንበት በነጻነት የመናገርና የመጻፍ ሁኔታ እነሱ ከመታሰራቸው በፊት ከነበረው በባሰ ተዳፍኖ መገኘቱን ባሰብሁ ጊዜ ሀዘኔ ይበዛል። በተለይ በተለይ አብርሀ ደስታ ከመታሰሩ በፊት የነበረውን የነጻነት መንፈስና የነበረውን አንጻራዊ «ነጻነት» ዛሬ ካለው የነጻነት ምህዳር አኳያ ለመዘነ፤ ስርዓቱ «በነጻ» ከተለቀቁት ንጹሓን ጋር እንዳይደርስ በህግ የማይታገድ ስርዓት አልበኝነቱ በከፋ ደረጃ ላይ እንደመገኘቱ መጠን ከበፊቱ በባሰ ዛሬ «ነጻ» ናችሁ ተብለው የተለቀቁቱ የነአብርሀ ደስታ ጉዳይ ያሳስበዋል።

የነሐብታሙ አያሌውና አብርሀ ደስታ «መፈታት» የወያኔን «የፍትህ» ሂደት ፍጹም ግፈኛነት ይለውጠዋል የሚል የዋህ ያለ አይመስለኝም። እነ አብርሀ የተፈቱት የፍትህ ስርዓቱ ተሻሽሎ ሳይሆን የተጨማለቀው የፍትህ ስርዓት የወለደው ህዝባዊ እልህና እምቢተኝነት በማየሉ ሳይፈነዳ ለማስተንፈስ ታስቦ ነው። በእውነቱ አሁን ያለው ሁኔታ እነ ሐብታሙ አያሌው ሲታሰሩ ከነበረው የሚካፋ እንጂ የተሻለ አይደለም።

ወያኔዎች ከመለኮት ተዛምዶ ያለውን መንፈሳቸውን ከአራዊት ባህሪ ተዛምዶ ባለው ጡንቻቸው ስልጣን ስር ካዋሉት ብዙ ዘመን ሆኗቸዋል። ንጹሓንን ከሰውና ከእግዚያብሔር ህግጋት በላይ በእስር ሲያሰቃዩ ከርመው ዛሬ «በነጻ» መለቀቃቸውን ማስነገራቸው አገሪቱ ውስጥ የቆመው ስርዓት አይን ያወጣ፤ ጭካኔ የተሞላበትና ህዝብ የማጥቂያ የአውሬዎች መንግስት መሆናቸውን የሚያሳይ እንጅ ፍትህ የሚሰጥበት፤ ህጋዊ ስርዓት የሰፈነበት መንግስታዊ አቅዋም መዘርጋታቸውን የሚያረጋግጥ አይደለም።

በመሰረቱ አገር የምትሻሻለው፤ የጥበብ ፍላጎታቸውን ድካምና ችግር ወይንም ምቾትና ተድላ በማይመልሳቸው ጠቢባን፤ ሰብኣዊ ከፍተኛነታቸውንና ጽኑ ሞራላቸውን የግል ደስታና ድሎት፤ ወይንም መከራና ስቃይ በማይሰብራቸው በነሐብታሙ አያሌው አይነት አዋቂ የሐሳብ ሰዎች እንጂ በእንደ ወያኔዎች አይነት የሰዎችን የማመዛዘኛ አእምሮ በሚያደነዝዘው በዘረኝነት በተደራጁ፤ ካለፉት መንግስታት የከፉ ሆነው ሳለ ባለፉት መሪዎች ላይ የሚያወርዱትን ርግማን ብቻ ለህዝቡ መመገብን እንደ መልካም ስራ በሚቆጥሩ፤ የግል ጥቅም አሳዳጅ ደንቆሮና ጨካኝ አውሬዎች አማካኝነት አይደለም።

እነሐብታሙ ከታሰሩ ከአንድ አመት በኋላ ያለንበት ሁኔታ የፍትህ ስርዓቱና መንግስታዊ መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ በአገዛዙ ቁጥጥር ስር የወደቀበት፤ ያልተሰደደው ገበሬው፣ ነጋዴውና ሌላውም ሰርቶ ኗሪ ህዝብ በኑሮ ውድነት እየተቆላ ግብርና ቀረጥ እየተደራረበበት በአገሩ መኖር ተስኖት እስኪያንገሸግሸው እየተመተረ በባርነት እየኖረ ይገኛል። ወጣቱ ደግሞ በአገሩ ተስፋ አጥቶ ባህር በማቋረጥ እግሬ አውጭኝ እያለ የባህር አሳ ሲሳይና የውስጥ እቃው እየወጣ የአሞራ ቀለብ እየሆነ ነው። ከፊሉ ወጣት ደግሞ ነፍሱን በጥርሱ ይዞ የሰው ጠል አራጆች የጭካኔያቸው ማርኪያ እንዲሆን ሲዳረግ፤ ቀሪው ደግሞ በየጎረቤት አገሮች ኬላ እየተያዘ የባእድ ማጎሪያ ቤቶችን እያጨናነቀ ይገኛል። በተቃራኒው የስርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት ወያኔዎች ግን አገሪቱን አጥንቷ እንኪታይ በመጋጥ በበለጠ ድሎት ሲቀማጠሉ የተረፋቸውን ደግሞ የግፍ ዘመናቸውን ለማራዘም የሚያስችላቸውን የጦር መሳሪያዎች ለማደርጃነትና ለማባዣነት እያዋሉት ይገኛሉ።

የሕዝቡም ጠቅላላ ኑሮ ሰላም ከማጣቱና የፍርሀት መንሰራፈፊያ ከመሆኑ በቀር ከአመት በፊት ከነበረው በምንም አልተሻለም። የግል ጋዜጦች ሁሉ ተዘግተው፤ ስለህዝቡ ኑሮ ጥቂት ማጉረምረም የሚያሳዩ የፖለቲካ ሰዎች ሁሉ እየተያዙ ያለፍርድ ታስረዋል። እነ አብርሀ ከታሰሩ ከአንድ አመት በኋላ አንድ ሰው በጽሁፍም ሆነ በንግግር ወያኔን ከማመስገንና ለዛሬው ችግር የድሮዎችን መሪዎች ከመርገም ያለፈ የተለየ ሐሳብ የመግለጽ መብት የለውም። እነ ሐብታሙ አያሌው ከታሰሩ ከአንድ አመት በኋላ ማንም ሰው ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ መቃወም ቀርቶ የአቤቱታ ድምጽ ማሰማት አይችልም። እነ የሽዋስ ከታሰሩ ከአንድ አመት በኋላ የአገዛዙ ትኩረት የህዝቡን ኑሮ ወደተሻለ መንገድ ለመምራት ቆርጦ መነሳት ሳይሆን የአገዛዙን መሰረት ለማጠንከር አብዝቶ ከመታገል በቀር ሌላ የመሻሻል ሙከራ አላሳየም። በአጠቃላይ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዘጠና ሚሊዮን ሰዎች የታሰሩባት የአለም ሰፊዋ ጓንታናሞ ሆናለች።

አሁን ባለንበት መስቀለኛ መንገድ ያለን ሁለት አማራጭ ብቻ ነው። አንድም ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በአንድነት በምናሰማው የጭንቅ ምጥ በሚወልደው ጣምራ ጩኸት በጋራ ነጻ ወጥተን ከታሪካዊ ችግራችን እንገላገላለን፤ አሊያም በጎሰኛነት ልክፍት አብደን እውር ድንብራችንን እየሄድን ከዘመነ መሳፍንት በባሰ ሁኔታ ርስበርስ እየተከሳከስን ሞትን እናነግሳለን። በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።

በመጨረሻም እንዲህ እላለሁ፤ በነካ እጃችሁ ተመስገን ደሳለኝንም ፍቱት! እውነትን ከመጋፈጥ በስተቀር እሱም ቅዱስ ነው! እስክንድር ነጋንም ፍቱት፤እሱም ፍጽም ንጹህ ነው። እነ አቡበከር አህመድንም ፍቷቸው እነሱም ሰላም ወዳድ ደግ የሐይማኖት መምህሮች ናቸው! ሌሎችን ንጹሓንንም ፍቷቸው። አለበለዚያ የፍትህ ስርዓቱ ልዕልና ተገፍፎና አገር ታስራ፡ አሸባሪ ብላችሁ በግፍ ካጎራችኋቸው አንድ የጭካኔ አመት በኋላ ከምታሰቃዮዋቸው ሚሊዮን ንጹሓን መካከል እነሐብታሙ አያሌውንና አብርሀ ደስታን በጠባብ እስር ቤት ከነበሩበት ወደሰፊው ጓንታናሞ እንዲዘዋወሩ በረጅሙ አስራችሁ «ስለለቀቃችኋቸው»፡ «የፍትህ» ሂደታችሁን ሙሉ በሙሉ ወንጀለኛነትና በቃላት ከሚገለጸው በላይ መጨማለቁን ሊለውጠው አይችልም።

አቻሜለህ ታምሩ

Leave a Reply