23 AUGUST 2015 ተጻፈ በ 

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ ሐምሌ 11 እና 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የተባሉ ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ በሁለቱ ቀናት ውይይት ላይ በተለይ በመጀመርያው የዕቅድ ዘመን የነበሩ ችግሮች ተነስተዋል፡፡

በቀጣይ ምን ይደረግ? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ተሰብሳቢዎች በርካታ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ አሉ ያሉዋቸውን ጉለቶችና ማነቆዎችንም በተለየ መልክ ሰንዝረዋል፡፡ በሁለቱ ቀናቶች የታሰቡትን ጥያቄችና ሐሳቦች በመያዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ረቡዕ ነሐሴ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. የማጠቃለያ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መድረክ የመንግሥት ቀጣይ ዕቅዶች የሚያመለክቱ አዳዲስ ሐሳቦችንም የጠቆመ ነበር፡፡ በተለይ በማኑፋክቸሪንግና የወጪ ንግድ ዘርፍ የተገኘው ውጤት አናሳ መሆን የተለያዩ ምክንያቶች የነበሩበት ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፉን አካቶ የነበረው የሰኞና የማክሰኞ ውይይት ላይ የመልካም አስተዳደርና ቢሮክራሲ አንዱ ችግር ለመሆኑ በተለያዩ መንገዶች ተገልጿል፡፡ እንዲህ ያሉ አስተያቶች ጥያቄዎችን በመያዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መንግሥት ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን አንዳንድ ተግባራትንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ ውስጥ የተወሰነው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ማኑፋክቸሪንግ ያልተሳካው ዘርፍ

በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ዘመን ከታቀደላቸው ግብ ብዙ ርቀት ላይ ከቆሙት ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ዘርፉ እጅግ ደካማ አፈጻጸም የታየበት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ዙሪያ ከዚህ በኋላ ወሳኝ ሥራ መሠራት አለበት የሚሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ጉዳዩ የሞት ሽረት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በ10.6 በመቶ ሲያድግ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ግን 13 በመቶ ብቻ ማደጉ ከተቀመጠው ዕቅድ አንፃር አፈጻጸሙ አናሳ መሆኑን እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡ የረባ ሽግግር ያልታየበት ዘርፍ መሆኑን ጭምር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንደ አጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ቢያንስ ከ20 እና ከ20 በመቶ በላይ ማደግ ነበረበት ብለዋል፡፡

ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተከፋፍሎ ሲታይም ደግሞ የትላልቅ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱትሪዎች ዕድገት 18 በመቶ በመድረሱ ከ20 በመቶ የቀረበ ውጤት የታየበት ሆኗል፡፡ ስለዚህ በጥቅል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተመዘገበው አናሳ ውጤት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሲፈተሽ ደግሞ ጉድለት የታየው በጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱን ማረጋገጥ ተችሏል ተብሏል፡፡ እነዚህ ዘርፎች የታየባቸው ዕድገት አራትና አምስት በመቶ አካባቢ ብቻ በመሆኑ ጥቅል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ዕድገት ጎድቷል፡፡ መንግሥት ግን ከፍተኛ የሆነ ለውጥና ዕድገት ይመዘገብባቸዋል ብሎ አቅዶ የነበረው በነዚህ ዘርፎች ላይ ነበር፡፡ በነዚህ ዘርፎች የተሠራው ሥራ ዘግይቶ መጀመሩም የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ስለዚህ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አወቃቀር በጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን መሠረት በማስፋት ዙሪያ የነበረ ጉድለት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ቢሮክራሲና መልካም አስተዳደር

‹‹ይህ አምስት ዓመት አጠቃላይ ሥር ነቀል ለውጥ የምናመጣበት ጉዞ ነው፡፡ ጉዞው የባህል ለውጥን ጭምር የምናመጣበት እንጂ ትንሽ ችግሮችን በመለወጥ ብቻ አጠቃላይ ለውጥን ማምጣት አይችልም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የመንግሥት ቢሮክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ምን ታስቧል? ለሚለው ጥያቄ ‹‹ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት›› በሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ተቋማዊ ለውጥ  ሊመጣ ካልቻለ ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክና ባለሥልጣንና ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አራትና አምስት ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶች ታስገባላችሁ፡፡ በገቡ በዓመታቸው የቀድሞ የተቋሙን ሠራተኞች ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ ለምድን ነው እነዚህ አዲስ ተመራቂ ወጣቶች ወደ ሥራ በገቡ በዓመታቸው ጉቦ መብላት የሚጀምሩት? አገልግሎት የሚያጓትቱት? ማጨናነቅ የሚጀምሩት? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ የሚሆነው ችግሩ የልጆቹ ሳይሆን የተቋሙ ባህል የፈጠረው ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ እንዳመጡ አፈፍ አድርጎ ስለሚወጣላቸው ነው በማለት በዚያ አካባቢ ያለውን ችግር ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም ተቋማዊ ለውጡ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል በማለት፣ ይህንንም ማሳካት የሚቻል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ጭምር የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ በመጠቆም፣ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው ችግር ምናልባትም ውጭ ካሉ ተቋማት የባሰና የማይስተናነስ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የባህል ለውጥ እንዲመጣ ከተባለ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፤ በመንግሥት ብቻን የባህል ለውጡን አይመጣም፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ልማታዊ መንግሥት ያለሕዝብ ተሳትፎ ውጤት አያመጣም፡፡ በዚህ ረገድ የሚፈለገውን ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ታጋይ ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለመብቱ የሚታገል ዜጋ ከተፈጠረ የመንግሥት ቢሮክራሲም ሆነ የመንግሥት የፖለቲካ አመራር መንቀሳቀሻ አይኖረውም በማለት ገልጸዋል፡፡

የታክስ ጉዳይ

የአገሪቱ ዓመታዊ የታክስ ገቢ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢኮኖሚ ከምንልቃቸው አገሮች ሳይቀር የግብር ገቢው አናሳ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? የሚለው ተገምግሞ ከተደረሰባቸው ድምዳሜዎች ውስጥ አንዱ የታክስ መሠረቱ አናሳ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ታክስ መክፈል የሚገባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያለመግባታቸው ጭምር የፈጠረው ክፍተት በመሆኑ እነዚህን ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ታክስ ሥርዓቱ እንዲገቡ ሲደረግም ወሳኝ ተደርጎ የሚወሰደው የታክስ መጠኑ ሳይሆን የታክስ መሠረቱን ማስፋት ይሆናል፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ዘመናዊና ልማታዊ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡

ዘመናዊ አሠራርን ከማስፈን አንፃር የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች አሉ፡፡ ይህም ለውጥ እያመጣ በመሆኑ ይህ ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ የታክስ መሠረቱን ከማስፋፋት አንፃር ግን በቀጣይ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ውስጥ መደበኛ ያልሆኑ (ኢንፎርማል) ዘርፎችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማስገባት አንዱ የመንግሥት ዕርምጃ ይሆናል፡፡

አንዳንድ ትልልቅ የታክስ ከፋዮችም ጭምር ታክስ ላለማስከፈል ኪሳራ የሚያስመዘግቡትን ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ በማድረግ፣ ጭምር ለውጥ እየመጣ በመሆኑ ከዚህም በኋላ ሁሉን አቀፍ የሆነ መፍትሔ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በታክስ ዙሪያ የቀረቡ አንዳንድ ሐሳቦችን የሚቀበሉትና በታክስ ዙሪያ ያለውን ችግር አማራሪ ነው መባሉን የሚቀበሉ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ምሬቱ መቆም ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ምሬቱ ሁለት ዓይነት ነው ይላሉ፡፡ አንዱ በትክክል በደረሰበት ችግር የሚያማርር ነው፡፡ ሁለተኛው ግን በደሉንና የሠራውን ሥራ ለመሸሸግ በማስመሰል የሚያማርር ነው ብለዋል፡፡ ችግሩ የመንግሥት አስፈጻሚዎና የባለሀብቱም ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ትልልቅ እርሻዎችና ለግል ባለሀብቱ የተሰጠው 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት

ሰፋፊ እርሻዎችን ከማስፋፋት አንፃር ውጤት ያላመጣው ትኩረት ስላልተሰጠው ነው፡፡ የወረዳና የዞን አስተዳደሮችም የሚያሳርፉት ተፅዕኖዎች ትላልቅ እርሻዎች ልማት አዝጋሚ እንዳደረገው ባለሀብቶች ተናግረው ነበር፡፡ የመሬት አቅርቦት ችግርም እንዳለ ተጠቅሷል፡፡ ትላልቅ እርሻዎች ላይ ለመግባት ሌሎች በርካታ ማነቆዎች ስለመኖሩ በሰኞውና በማክሰኞው ውይይት ላይ ተነስቷል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በትላልቅ እርሻዎች ዙሪያ አሉ የተባሉትን ማነቆዎች መፍታት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ትልቁ ችግር ግን የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ክፍተት መኖሩ ነው ብለው፣ ይህ ችግር አርሶ አደሩ ላይ ብቻ ሳይሆን እጅግ የበዛው የግል ባለሀብት ጭምር ላይ የሚስተዋል ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ አገራዊ ባለሀብቶች ሳይቀሩ ከቴክኖሎጂ ሽግግር አንፃር ኋላ ቀር ስለመሆናቸው ለማሳየትም አኅዛዊ በሆነ መረጃ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በእርሻ ሥራ ለመሰማራት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወስደዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ለእርሻ የወሰዱት 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በደቡብና በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻ መሬት የሚስተካከል ነው፡፡ ባለሀብቶቹ የሁለት ክልሎች አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበትን ያህል መሬት ቢወስዱም፣ እነዚህ ባለሀብቶች ለግብርናው ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አሁንም ለግብርና ዘርፍ ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉት በአነስተኛ ማሳ የሚያርሱ አርሶ አደሮች በመሆናቸው በእርሻቸው ዘርፍ የባለሀብቶች ተሳትፎ አናሳ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡

የግብርና ዘርፍ ውስጥ አሉ ያሉዋቸውን ሌሎች ምክንያቶችም የጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን በተለይ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ ዙሪያ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ከቀድሞ የተለየ ዕቅድ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የአቶ ኃይለ ማርያም ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ባለሀብቶች የእርሻ መሬት ወስደው ከአርሶ አደሩ ባልተሻለ የቴክኖሎጂ ደረጃ እያመረቱ ስለሆነ መንግሥትም እስካሁን ድረስ ራሳቸውን ችለው ለውጥ ያመጣሉ የሚለው ግምት ባለመሳካቱ፣ ከዚህ በኋላ ራሱን የቻለ የግል ባለሀብቶችን የቴክኖሎጂ ሥርጭትን የሚደግፍ ተቋማዊ ሥራ ተሠርቶ ከመሠረቱ ለመቀየር መታሰቡን ገልጸዋል፡፡

መንገድ ግንባታና ፈታኝ የተባለው ወሰን ማስከበር

መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ እየታየ ነው ያሉት ችግርና ማስጠንቀቂያ ጭምር የሰጡበት ነበር፡፡ መንገድ ለመገንባት የሚነሱ ግንባታዎች እየተጠየቀባቸው ያለው ካሳ ክፍያ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መንገድ ለመገንባት ሲገባ ሕዝቡን የማሳመን ችግር መታየቱንም ጠቅሰዋል፡፡ ችግሩ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዘም ነው ይላሉ፡፡ ይህ ካልተስተካከለ ልማቱ መደናቀፉ ጥርጥር አይኖረውም በማለት በካሳ ክፍያ ጉዳይ አለ ያሉትን ችግርን ሰፋ አድርገው አብራርተዋል፡፡

ከጎሳ መሪ ጀምሮ እስከ ቀበሌ አስተዳዳሪ ድረስ በካሳ ክፍያ የራሳችንን ድርሻ ይሰጠን እስከማለት ተደርሷል፡፡ ይህም መንግሥት ለልማቱ ከሚያስፈልገው በጀት በላይ ለካሳ ክፍያ እንዲያውል የሚገደድበት ሁኔታ እየፈጠረ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው ክፍተት ካልተስተካከለ በቀር የአካባቢውም ሆነ አገራዊ ልማቱ ገደል መግባቱ አይቀርም በማለት ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ በየአካባቢው የተፈጠረውን ችግር መንግሥት የሚያውቀው ሲሆን፣ ችግሩ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ሱማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ክልሎችም ይታያል፡፡ ሌላው ቀርቶ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ዝርጋታውን ታደናቅፋለች የተባለ አንድ ዛፍ ይቆረጥ ሲባል አንድ ሚሊዮን ብር ካልተከለፈኝ እየተባለ ስለመሆኑ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ለአንድ ዛፍ አንድ ሚሊዮን ብር ካሳ እንዴት ተደርጎ ይከፈላል?›› በማለት ችግሩን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ አካባቢዎችም መንገድ ለመሥራት የገቡ ቻይናዎችን ዝናብ ያጠፉብ ቻይናዎች ናቸው ብለው ሥራ አላሠራ የተባለበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለመሠረተ ልማት ከሆነ ዛፉን ቆርጠው ልማቱን ቀጥል መባል ሲገባው እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል፡፡ እንደውም በአንዳንድ ቦታዎች አንዳንዶች ከወረዳ አመራሮች ጋር ተመሳጥረው በአካባቢው መሠረተ ልማት የሚያልፈው በየቱ ጋር ነው? ተብሎ መስመሩ በሚያልፍበት ቦታ ላይ ትንሽሽ ጎጆ በመቀለስ ካሳ እየተጠየቀበት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ በመሠረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ያለውን ችግር ለማሳየት በምሳሌነት የተጠቀሱትና ባለፈው ሳምንት ገጠመን ያሉትንም ጭምር ነበር፡፡

ከወልዲያ አዋሽ ድረስ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ኮንትራክተሩ በአማራና አፋር ክልል ድንበር ላይ ካምፕ ለመሥራት ይዘጋጃል፡፡ የአፋር አመራሮችና ወጣቶች ይህ ካምፕ ወደኛ ድንበር ገብቶ ካልተሠራ እናፈርሳለን ይላሉ፡፡ የአማራ አመራሮችና ወጣቶች ወደኛ ክልል ገብቶ ካልተሠራ እናፈርሳለን በሚል ሙግት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ኮንትራክተሩና ሠራተኞች ግራ ይጋባሉ፡፡ እኛ ጋር ጭምር ደውለው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት አለፈ በማለት ያሉ እንቅፋቶችን ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ አዳማ ድረስ ያለውን የባቡር መስመር ለመዘርጋትም ወሰን ለማስከበር ብቻ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ፈጅቷል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍም ይረዳል የተባለ አሠራር እንደሚዘረጋ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ኮንትራክተሮችን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለማስገባት የተያዘው ውጥን

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በጉልህ መታየት የሚኖሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያድግ ማነቆ ናቸው የተባሉትን ጉዳዮች አንድ በአንድ በመፍታት አገራዊ ባለሀብቶች በስፋት የሚሳተፉበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

አገራዊ ባለሀብቱን በማኑፍክቸሪንግ ዘርፍ ለማሳተፍ መንግሥት የሚወስዳቸው የተለያዩ ዕርምጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የኮንስትራክሽን ባለሀብቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ባለሀብቶች ለራሳቸው የሚሆን ግብዓት በራሳቸው አቅም እንዲያመርቱ የሚያስችል ነው፡፡

በዚህ ዙሪያ ኮንትራክተሮች ጋር የሚመክሩ መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ግን ኮንትራክተሮች ለራሳቸው የሚሆነውን ግብዓት እንዲያመርቱ ፍላጎት ያለውና ይህንንም ለማስፈጸም የተዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡

ኮንትራክተሮች በሪል ስቴት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ የኪራይ ሰብሳቢነቱ በር ተዘግቶ ወደ ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረት ሥራ ጭምር መግባት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አንድ ሁለት የሚሆኑ ኮንትክተሮች በሲሚንቶና በሌላ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርት ውስጥ ቢገቡም ሌሎችም እንደግንባታ ማጠናቀቂያ ያሉ ምርቶችን፣ ለምሳሌ የሴራሚክ ውጤቶችና የመሳሰሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን ምርቶች ሌሎች ባለሀብቶችም ማምረት የሚችሉ ቢሆንም፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉት ለሥራው ስለሚቀርቡ ለኮንስትራክሽን ግብዓት ምርት ውስጥ እንዲገቡ ትኩረት ይደረጋል፡፡

‹‹አንድ በአንድ ቆጥረንና መልምለን በጋራ ተወያይተን ወደዚህ ግባ የምንል ከሆነ በጥቅል መምጣት ያለበትን ማምጣት አይቻልም፤›› በማለት በጉዳዩ ላይ መንግሥት ያለውን ዕቅድና አቋም አስተድተዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ይህንን የመንግሥት ውጥን ለማስፈጸም ከባንኮች ጋር የሚመክሩና ዕቅዱ ሥራ ላይ መዋል ስላለበትም መንግሥት ከፕሮጀክት ቀረፃ ጀምሮ እንደሚደግፍ ተናግረው፣ እንዲህ ካልተደረገ በቀር አሁን ባለው አዝጋሚ አካሄድ መቀጠል እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡

አስመጪዎችና ላኪዎች ዕጣ ፈንታ 

እንደ ኮንትራክተሮች ሁሉ አስመጪዎችና ላኪዎችም በቀጣይ ዓመታት ሊከወኑ ይገባል የተባለ የመንግሥት ዕቅድ ስለመኖሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ‹‹ሳሙና የሚያስመጣ አስመጪ ከዚህ በኋላ ሳሙና ማምረቻ እንዲከፈት፣ ቡና የሚልክ ባለሀብት ቡናን ቆልቶና አሽጎ መላክ ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል፡፡

በአገልግሎትና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ደረጃ በደረጃ የሚካሄድበትና አስመጪዎች ራሳቸው ከሚያውቁት ምርት በመነሳት አገር ውስጥ እንዲያመርቱና የገቢ ዕቃዎችን የመተካት ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይም ከባለሀብቶች ጋር በመነጋገር መሥራት ካልተቻለ፣ ልማታዊ ባለሀብቶች ቁጥር ባነሰበት ሁኔታ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትና ሥርዓት መገንባት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን የተወሰኑ ነገሮች እየተሠሩ ቢሆንም በጣም አነስተኛ ስለመሆናቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ያስመጡ የነበሩትን ምርት በአገር ውስጥ ለማምረት የተንቀሳቀሱትን ባለሀብቶች ‹‹በጣም እናከብራቸዋለን›› ብለዋል፡፡ ‹‹የእኛ ባለሀብቶች ትልቅ ክብር ልማታዊ ሆነው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሠማራታቸው ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህን ማድረግ ካልተቻለ የዚህ አገር ትራንስፎርሜሽን ከዘገየ ደግሞ ትልቅ ጥፋት ስለሚከተል ሁላችንም ችግር ውስጥ እንገባለን፤›› ብለዋል፡፡

በትግበራውም በተዘጋጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው እንዲሠሩ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ‹‹የኢኮኖሚው አወቃቀር በመሠረቱ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚያደላበት ሁኔታ ማመቻቸት አለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በመጪው አምስት ዓመት ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡

‹‹በዚህ መሠረታዊ ጉዳይ ውጤት የሚያመጣ ከሆነና ትራንስፎርሜሽኑ በሚቀጥሉት አምስት ዓመት ማምጣት ካልቻለ አደጋ አለው፤›› ስለዚህ ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ

የመኖሪያ ቤት ችግር ጉዳይ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባው ስለመሆኑ ተወያዮች አንስተው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የተጀመረው የቤቶች ልማትን ያስተወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የመኖሪያ ቤት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መንግሥት ብቻ ያቀርባል ተብሎ ከታሰበ መንግሥት ማቅረብ አይችልም፡፡ ዜጎችም ቤት ማግኘት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ክፍተት አለ ማለት ነው፤›› ይላሉ፡፡

ወሳኙ ጉዳይ የቤት ባለቤትነትን ለማምጣት ሁሉም አካላት በሚያደርጉት ርብርብ ነውም ይላሉ፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት በሚካሄዱባቸው በተመረጡ ከተሞች የኢንዱስትሪ ሠራተኞች የሚያርፉበት ቤት ለመሥራት ታቅዷል፡፡ ነገር ግን የቤት ልማት ለማሳደግ ዜጎች በማኅበር ተደራጅተው ቦታ የሚያገኙበት፣ የግል ባለሀብቱም የሚያለማበት ሁኔታ የሚመቻች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በላይ ግን በቤት ልማት ዙሪያ እንደክፍት የታየው እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊስተናገዱበት የሚችሉበት መንገድ በመሆኑ፣ ይህ የቤት ችግር ሁሉን አቀፍ በሆነ ደረጃ መታየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

እየተሠራም ያልተደረሰበት መሠረተ ልማት

ሐምሌ 11 እና 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች ተደጋግሞ ከተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ውስጥ መሠረተ ልማትን የሚመለከት ነበር፡፡ የመሠረተ ልማት ችግር መኖሩ ብቻ ሳይሆን በተለይ የመንገድ ግንባታዎች የጥራት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው ተብሏል፡፡ ይገነባሉ የተባሉ መንገዶች ያለመገንባታቸው ጉዳይም በጥያቄ መልክ ቀርቧል፡፡ በዚህ ዙሪያ የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መሠረታዊ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የታሰበውን ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት አንዱ እንቅፋት የሚሆነውም የመሠረተ ልማት ተሟልቶ አለመገኘት መሆኑንም አክለዋል፡፡

በዚህ ዘርፍ መንግሥት ብዙ መሥራቱንና በዓለም ደረጃ በመሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ እመርታ አሳይተዋል ከተባሉ ሦስት አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንድዋ ምናልባትም ቀዳሚ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አገሪቱ ከተነሳችበት ደረጃ አንፃር አሁንም በተፈለገው ልክ ማሟላት አለመቻሉን ነው፡፡ አሁንም ግን ከፍተኛ በጀት የሚበጀትለት መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ያለው ችግር የመሠረተ ልማት ግንባታ ወይም አቅርቦት ክፍተት ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን በጥራት የማቅረቡ ጉዳይ ነው፡፡

‹‹ብዙ ተለፍቶ የመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በሚፈለገው ደረጃ በጥራት ካልቀረበ ከእጅ አይሻል ዶማ›› ይሆናል በማለት፣ ከዚህ አኳያ ያሉትን ችግሮች አንድ በአንድ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲነደፍ መካከለኛ ገቢ በምንደርስበት ጊዜ የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት በዚህኛው አምስት ዓመት ማጠናቀቅ አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት ከፍተኛ ጫና አለበት፡፡ የሚያስፈልገው ገንዘብም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመሠረተ ልማት ጥራት ላይ ለቀረበው ጥያቄም የጥራት ችግር ብዙ ጊዜ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሚፈጥሩት ነው የሚለውን ብዙም የማይስማሙበትና የቻይና ኮንትራክተሮች ጭምር የገነቡዋቸው አንዳንድ መንገዶችም የአገልግሎት ዘመናቸው ሳይደርስ ሲፈርሱ እየታየ ነው ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ችግር ከዲዛይን ሥራና ከግንባታ ቁጥጥር ጉድለት የመነጩ ጭምር ናቸው ብለው፣ በግንባታ ቁጥጥር ላይ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚታይ በመሆኑ በጥራት መጓደል አንድ ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎችም ምክንያቶች እንዳሉ በመጠቆም፣ በዚህ ረገድ የተነሳው ጥያቄ ትክክል ነው በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ አስምረውበታል፡፡ …..ኢትዮጵያን ሪፖርተር

ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የጎሳ ፖለቲካን በማውገዝ ያደረጉት ንግግር

Ethiopian PM Hailemariam Desalegn gives unusual speech where he condemns ethnic politics

 

 

Leave a Reply