ዛሬ እንደወትሮዬ አብርሀ ደስታን ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ አምርቼ ነበር። ታዲያ አብርሀን ሆነ መሰሎቹን ለመጠየቅ እንዲህ በቀላሉ የሚቻል አይደለም። በጥብቅ ከሚጠበቀው ቃሊቲ ውስጥ ለመጠየቅ የሚፈቀደው ከ 6:00 – 6:30 ያለችን 30 ደቂቃ ብቻ ስትሆን እሱም በር ላይ ቆመው የአይንህ ቀለም አላማረንም እያሉ የሚመልሱ ደህንነቶችን ማለፍ ከተቻለ ብቻ ነው። እናም ከብዙ ንትርኮች(እምባ ቀረሽ ልመና) በኃላ የያዝኩትን የፆም መፍቻ ምግብ ይዤ ወደ ውስጥ ዘለኩ። ከዛም ከአብርሀ ጋር በሽቦ በተከለለው መጠየቂያ ጣታችንን አሾልከን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ በቀጥታ ስለ ፍርድ ቤቱ ውሳኔና ስለ ቀጣይ ሁኔታ ማውራት ጀመርን። አብርሀ ተፈቶ ከሚተነፍሰው አየር በላይ እየታየው ያለው – ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ነው። እኔም ከዚህ በኋላ ለመውጣት ስንት ጊዜ እንደሚቀረው ፍርድ ቤቱን ደፍራቹሀል የተባለውን የፍርድ ውሳኔ በማንሳት በጥያቄ መልክ አስከተልኩ። እሱም “አስቀድሞ በተከሰስንበት ፍርድ ነፃ ናችሁ ስለተባልን ፍርድ ቤቱን በመድፈር በሚል የተላለፈብን የቅጣት ውሳኔ እስከዛሬ በእስር ላይ በቆየንበት ጊዜ የሚጣፋ ይሆናል። ይህም በእኔ የተላለፈው የ 16 ወር የቅጣት ጊዜ አመክሮ የማይታሰብ ከሆነ ጥቅምት 24 የእስር ጊዜዬን ጨርሼ የምፈታ ሲሆን አመክሮዬን በህጉ መሰረት ተፈፃሚ ከተደረገ በሚቀጥሉት ቀናት የምወጣ ይሆናል። የሽዋስ እና ዳንኤል ደግሞ የ14 ወር ጊዜ የተፈረደባቸው ስለሆነ በህጉ መሰረት አመክሮ የሚታሰብላቸው ከሆነ በሚቀጥሉት ቀናት የሚፈቱ ይሆናል፤ ይህን መብት ከከለከሏቸው ግን ነሀሴ 30 የሚፈቱ ይሆናል።” ሲል ተስፋውን ገለፀልኝ።” እኔም ሲቪል የለበሰው አዛዥ(ደህንነት) ዛሬ የመጨረሻ እንደምጠይቀውና ከዚህ በኋላ መጠየቅ እንደማልችል ስለነገረኝ የአብርሀን ከእስር የመውጣት ዜና በጉጉት እየጠበኩ እገኛለሁ።
በመጨረሻም
★አብርሀ ደስታ ዋጋውን እስከ ሞት የተመነለትን ነፃነት በኢትዮጵያ አብቦ እና ፈክቶ አየው ዘንድ እናፍቃለሁ★ ROBEL AYALEW