እንደሚታወቀው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ “የመቀሌ እና የአዲስ አበባ ቡድን” በመባል ለሁለት ተከፍሎ ቆይቶ ነበር። የመቀሌ ወይም የትግራዩን ቡድን የሚመራው አባይ ወልዱ ሲሆን፤ የአዲስ አበባዎቹ ደግሞ በነ ደብረጽዮን እና በጌታቸው አሰፋ ሲመሩ ቆይተዋል። ከአዲስ አበባዎቹ መካከል እነ አርከበ እና ጌታቸው አሰፋ፤ ከአዜብ መስፍን ጋር ቅራኔ ቢኖራቸውም፤ ለዚህ ጉባዔ ግን ከትግራዩ ቡድን ተቃራኒ በመሆን ቆመዋል። አርከበ እቁባይ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የተሰረዘ ቢሆንም፤ ከአዲስ አበባው ቡድን ጋር አብሮ በመስራት ይታወቃል። ከአዲስ አበባ የሄዱት አባላት በዚህ መልክ ራሳቸውን ሲያቧድኑ…የትግራዩ ፕሬዘዳንት እና የህወሃቱ ሊቀ መንበር አባይ ወልዱም፤ በተቻለ መጠን ደጋፊዎቻቸው በጉባዔው ላይ ተገኝተው የአዲስ አበባውን ቡድን እንዲያወግዙ ያልተሳካ ሙከራ አድርገው ነበር። እንግዲህ በዚህ የክፍፍል ስሜት ውስጥ ሆነው ነው ህወሓቶች ጉባኤያቸውን የጀመሩት።
ገና ጉባዔው ከመጀመሩ፤ ስልክ በመጥለፍ ስለላ የሚታወቁት ዶ/ር ደብረ ጽዮን፤ ማንም ተሰብሳቢ ምንም አይነት የሞባይል ስልክ ይዞ እንዳይገባ አግደዋል። የፌዴራል ፖሊስን የሚያዘው ጌታቸው አሰፋም… አካባቢው በፌዴራል ፖሊስ ልዩ ጥበቃ ስር እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ የውስጥ እና የውጭ ውጥረት መካከል… ከህወሃት ተሰናብተው የነበሩት እነአርከበ እቁባይ፣ ስብሃት ነጋ፣ ስዩም መስፍን እና አባይ ጸሃዬ የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ተጠይቆ፤ ህዝቡ በጭብጨባ ስለደገፈው ብቻ፤ ስብሰባውን የሚመራው አባይ ወልዱ ይህንኑ ሃሳብ ተቀብሎ፤ ተቀናቃኞቹ እነአርከበ እቁባይ እንዲናገሩ እድል ለመስጠት የተገደደበት ሁኔታ ተፈጠረ። በተለይ አርከበ እቁባይ የተሰጠውን የመናገር እድል በመጠቀም፤ የትግራይ ህዝብ የአስተዳደር በደል እንደደረሰበትና ፍትህ ማጣቱን ሲናገር፤ ተሰብሳቢው በጭብጨባ ነበር የደገፈው። ይህንኑ ተከትሎ እንዲናገሩ እድል የተሰጣቸው ሰዎች በመቀሌ እየደረሰ ያለውን በደል ዘርዝረዋል። ይህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የትግራዩን ፕሬዘዳንት አባይ ወልዱን የሚነካ ከመሆን አልፎ፤ አባይ ወልዱ ላይ ውግዘትን አስከትሎበታል።
የአርከበ እቁባይን ፈለግ በመከተል… ተሰብሳቢው በትግራይ እየተዛመተ ያለውን ሙስና ሲዘረዝር፣ መልካም አስተዳደር አለመኖሩን እያማረረ ሲናገር የነአባይ ወልዱ ቡድን እያነሰ እያነሰ ሄደ። እንዲያውም አንድ የሃይማኖት አባት… “እሳት ያልፈራ ህዝብ፤ እናንተንም አይፈራችሁም።” በማለት ማስፈራሪያ አዘል ማሳሰቢያ ሰጡ። በተቃራኒው ደግሞ እነደብረጽዮንም ሆኑ አዜብ መስፍን ከትግራይ ህዝብ ጋር በእለት ተ’ዕለት ጉዳይ ስለማይገናኙ የሚወቀሱበት እና የሚከሰሱበት ዝርዝር ጉዳይ አልነበረም። በመሆኑም በመጨረሻው የጉባዔ ቀን 45 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሲመረጡ፤ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት የአዲስ አበባዎቹ ህወሓቶ ሆኑ።
በዚህም መሰረት ዶ/ር ደብረጽዮንን ጨምሮ፣ አዜብ መስፍን፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር፣ ጌታቸው አሰፋ ከፍተኛ ድምጽ ካገኙት መካከል ሆነዋል። እነዚህ የአዲስ አበባ ህወሓት ቡድን አባላት የፓርላማ ምርጫ ሲደረግ ጭምር፤ በተለይ ካለፈው ምርጫ ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር በትግራይ ውስጥ እንኳን መወዳደር ትተዋል። የቀድሞ የአባይ ጸሃዬ ሚስት የነበረችው ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር (ሞንጆሪኖ) ጭምር ሰልፏን ከአዲስ አበባዎች ጋር አስተካክላ ዳግም ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ለመመረጥ በቅታለች።
ኢህአዴግ ደጋግሞ እንደሚናገረው ሳይሆን፤ ነባሮቹን በአዲሶች የመተካት አቅም እያጣ ነው። ከሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይልቅ ደግሞ በተለይ በህወሓት ውስጥ መተካካት አይታይም። በዚህ ጉባዔ እንኳን 32ኛ ሆኖ ከተመረጠው ጌታቸው ሬዳ በስተቀር ሌሎቹ የቀድሞ ታጋይ የነበሩ ህወሓቶች ናቸው። በመሆኑም ይህ ጉባዔ… መተካካት አልታየበትም በማለት መናገር ይቻላል። በአጠቃላይ የህወሓት አባላት በማዕከላዊ ኮሚቴው ምርጫ ላይ፤ ከፍተኛ ድምጽ የሰጡት ለአዲስ አበባው ቡድን ነው። ሆኖም ተቀማጭነቱን ትግራይ ላይ ያደረገ ድርጅት በመሆኑ አዲስ የሚመረጠን መሪ ከዚያው አካባቢ ማድረግ የግድ ሆነ። ስለሆነም የተመረጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ደግሞ፤ ስራ አስፈጻሚያቸውን ሲመርጡ የትግራዩን ህወሓት ቡድን ሲመራ የነበረውን አባይ ወልዱን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርገው በመምረጥ፤ የሃይል ሚዛኑን ለማስተካከል ሞክረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ ተመርጧል። ይህ ውጥረት የነገሰበት የህወሃት ጉባዔ ሲካሄድ፤ ከጉባኤ አዳራሹ እስከ አክሱም ሆቴል ድረስ፤ ለተከታታይ ቀናት ህዝብ እንዳይዘዋወር በፌዴራል እና በአካባቢው ፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ ሲደረግ ነበር።
አዲስ የተመረጡት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በከፊል የሚያሳየው ዝርዝር ከዚህ በታች ቀርቧል። ከስማቸው ጎን ከአባላቱ ያገኙት የድምጽ ብዛት ሰፍሯል።
1/ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (1107)
2/ አዜብ መስፍን (1089)
3/ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር (1085)
4/ ጌታቸው አሰፋ (1084)
5/ አባይ ነብሶ (1082)
6/ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም (1070)
7/ አረጋሽ በየነ
8/ ዶ/ር አዲሳለም ባሌማ
9/ በየነ ምክሩ
10/ ኪሮስ ቢተው
11/ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ
12/ ያለም ጸጋዬ
13/ ኬርያ ኢብራሂም
14/ ሃዱሽ ዘነበ
15/ ተወልደብርሃን ተስፋለም
16/ ሚካኤል አብርሃ
17/ ተወልደ ገብረጻድቅ
18/ ጎይቶም ይብራህ
19/ ገበዛይ ወልደአረጋይ
20/ አባይ ወልዱ (973)
http://ethioforum.org/amharic