ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ
ይድረስ ለተከበሩ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር አባል አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል ። ሰላምታየ እንዲደርስዎ ምኞቴ ነው። ሰሞኑን በዋሽንግቶን ዲሲና እኔ በምኖርበት በላስ ቬጋስ ከተማ ድርጅትዎ በጠራው ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር በጥሞና አዳመጥኩ ። ስለ እርስዎ ንግግርም በቀረበው ዜና ላይ ፤ ከአስር አመት በፊት በቅንጅት አባልነትዎ ታስረው ሳለ ፤ ይወጡ ከነበሩት ፎቶውች አንዱ የሆነውን ፤ ከቅንጅት V ምልክት ጋር ሳየው ሃሳቤ ወደኋላ ይዞኝ ነጎደ።
እኔ ያኔ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ሁለት የራዲዮ ፕሮግራሞችን አዘጋጅ ነበር ። “ንጋትና” “አቡጊዳ” ራዲዮ። “ንጋት” በራዲዮ ሞገድና፤ በኢንተርኔትም ይተላለፍ ስለነበር በሳምንት የስምንት ሰአታት ዝግጅት ነበረው ። አለማቀፍ ይዘትም ነበረው ። “አቡጊዳ” ግን ለዋሽንግተን ዲሲ በራዲዮ ሞገድ ብቻ ትተላለፍ የነበረች ራዲዮ ነበረች ። እናም እርስዎ እስር ላይ እያሉ ፤ መብትዎ ይከበር ዘንድ እኔና ብዙ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለናንተ መፈታት ታግለናል ። እንደናንተ እስር ቤት በአካል ባንገኝም ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤት መንግስት White House ፊትለፊት ለወራት በየቀኑ “የሻማ ማብራት” ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ብርድ ፤ ዝናብ ፤ ቁር ሳንመርጥ ፤ ሻማ አብርተንላችኋል ። ብዙ ኢትዮጵያውያን እህቶች ለናንተ መፈታት ሱባኤ ገብተው ፤ ካልጋቸው ወርደው መሬት ላይ ይተኙ ነበር ። እናንተ ሲሚንቶ ላይ ትተኛላችሁ በሚል ህሳቤ ተጋድሏችሁን ለመዘከር ያደርጉት እንደነበርም አስታውሳለሁ ።ታዲያ እኔም ለአካላዊ ፤ መንፈሳዊና የሃሳብ ነጻነታችሁ ብሎም ሙሉዕ መብታችሁ መከበር ፤ በሙያዬ ታግያለሁ ። ይህን ለማድረግ ደግሞ በሳምንት ለሶስት ቀናት ፤ በየቀኑ ከምኖርበት የሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ ፤ የመጨረሻ ጥግ ተነስቼ ፤ የራዲዮ ጣቢያው እስከ ሚገኝበት ሊዝበርግ ፓይክ ቨርጂኒያ ድረስ ፤ 70 ማይል እነዳ ነበር ። በንፁህ ህሊና ያለምንም ጥቅምና ክፍያ በናንተ በወገኖቼ ላይ ለደረሰው ግፍ እታገል ዘንድ ነበር ይህን ሳደርግ የነበረው ።
እንዲያውም አንድ ትዝታዬን ላጫውትዎ ። እናንተ ከታሰራችሁ በኋላ ተቃውሟችንን ለማሰማት እኔና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ባደረግነው ጥሪ መሰረት አንድ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሽንግቶን ዲሲ ተደርጎ ነበር ። ኖቨምበር 14 ቀን 2005 እ.ኤ.አ. ።
ኖቬምበር 14 የመፀው አጋማሽ ነው ። የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ዛፎች የበረዶውን ወቅት መቃረብ ለማሳበቅ ቅጠሎቻቸው ረግፈዋል ። ዛፎቹም ላይ የቀሩት ወይበዋል ወይም ወደ ወርቃማ አለያም ቡናማ ወይም ቢጫ ቀለም ተቀይረዋል። እንዲህ ያለው ወቅት ነፋሻማና ብርዳማ እንደሚሆን ይታወቃል ። የሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጆቹ ሁሉ በብርዱ ምክንያት ሰዎች ላይመጡ ይችላሉ ብለን ሰግተናል ። አጋጣሚ ሆኖ በእግዚአብሄር ፈቃድ የተረጋጋና ፀሃያማ ቀን ሆኖ ዋለ ። ቀኑ ፅሀያማ ቢሆንም ሞቃት ግን አልነበረም ። ይህም በትግላችን ላይ እግዚአብሄር ከኛ ጋር ነው ብለን እንድናስብ ምክንያት ሆነን ። ዝርዝር አላበዛም ። ሰልፉ ግን ከጠበቅነው በላይ ነበር ። በዲሲና በአካባቢዋ አንድ ሰው በቤቱ የቀረ አይመስልም ነበር ። በዋሽንግቶን ዲሲ ፖሊስ ዲፓርትመንት መረጃ መሰረት ወደ 30 ሺህ ሰው ሰልፉ ላይ ተገኝቶ ነበር ። አሜሪካንን በምስራቃዊ ዳርቻዋን በዋሽንግተን ዲሲ በኩል አልፎ ፤ ከሰሜን እስከደቡብ የሚያገናኘው Route 95 ለሰአታት ተዘግቶ ነበር ። ቨርጂኒያ ዲሲና ሜሪላንድ በቤልት ዌይ ካልሆነ በዲሲ በኩል ለማለፍ የማይቻል ሆነ ። 14 ኛውና 15ኛው መንገድ ላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን መንገዶቹን ለመዝጋት አስፋልቱ ላይ ተደርድረው ተኙባቸው ። የዋሽንግቶን ሞል ፈረሰኛ ፖሊሳችም ሆኑ መደበኛዎቹ ፤ ያልጠበቁት ሁኔታ በመፈጠሩ ሃይል እንዲጨመር ጠየቁ ። ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ የነበረውን ሁኔታ ባይናቸው ያዩት ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝና ረዳታቸው ግሪጎሪ ስምኪንስም ሰላማዊ ሰልፋችንን ደማቅ ካደረጉት ሰዎች ይመደቡ ነበር ። በአሜሪካ ከተደረጉ እኔ ከማውቃቸው ሰላማዊ ሰልፎች ፤ እንደዚያ አይነት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ፤ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ ተደርጎ አላየሁም ። ሰላማዊ ሰልፍ ድሮ ቀረ ብየ ልቀልድ ይሆን ? ወደቁም ነገሩ ።
አጋጣሚ ሆኖ መፈክሮችና ፖስተሮች ሲታደሉ የእርስዎ ፎቶ ያለበት ፖስተር ደርሶኝ ያን አንግቤ እንደነበር ትዝ ይለኛል ። ከዚያም አልፎ በናንተ መፈታት እርግጠኛ ስላልነበርኩ በግሌ አስከ ኤርትራ የጠመንጃውን ትግል ለማየት ከሄዱት ጋዜጠኞች ቀዳሚው እኔ ነኝ ብል ጉራ አይሆንብኝም ። ከዛ ትግል በኋላ ፤ እርስዎ ነፃነትዎን አግኝተው በአሜሪካ ከተሞች እየዞሩ በነጻነት ንግግር ሲያደርጉ ስሰማ ፤ ሰው ነኝና ይኸው የትግል ፍሬዬ ጎመራ ብዬ መኩራራቴን በይሉኝታ መደበቅ አልፈለኩም ። እጅግ ደስ አለኝ ። እግዚአብሄር ይመስገን ።
ደስታዬ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በነጻነት ባሰሙት ንግግር ላይ ግን የማንግባባባቸው ጉዳዮች እንዳሉ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ ። ኤርትራን አይቼ ሻእቢያን አውቄ ከመጣሁ በኋላ ሻእቢያ ዛሬ የመለያያ ነጥባችን ሆኗል።
“I don’t agree with what you say, but I will fight to the death to defend your right to say it” .
ትርጉሙ፡- “ከምትለው ጋር ባልስማማም፤የመናገር መብትህን ለማስከበር ግን እስከ ህይወቴ ፍፃሜ ድረስ እታገልልሃለሁ” ፤ የሚለውን የሰለጠነው አለም መርህ ይቀበሉታል የሚል እምነትም አለኝ ።
ውድ አቶ ሙሉነህ ! በዚህ ከተግባባን አንድ ለማናችንም ግልፅ እንዲሆንልን የምፈልገው ጉዳይ አለ ። ድርጅታችሁ ይመቸኛል ባለው መንገድና በመረጠው የትግል አቅጣጫ ቢጓዝ ተቃውሞ እንደሌለኝ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ ። እርስዎ እንዳሉት ከሰይጣን ተስማምቶ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ የማምን ሰው ግን አይደለሁም ። ሆኖም ግን የእምነት ነጻነት በሚከበርባት ሐገር የምኖር ሰው ነኝና የድርጅትና የግል መብትዎ ይከበር ዘንድ ፤ እታገላለሁ ። ታዲያ አንባቢዎቼ እርስዎ የተናገሩትን ይሰሙ ዘንድ ይህን ሊንክ ብጋብዛቸው ቅር እንደማይልዎ አምናለሁ ።
አንዳንድ ጉዳዮች እየተጠላለፉ ከኢትዮጵያ ጉዳይ ጋር ስለሚነካኩም ፤ በነዚህ ጉዳዮች ላይ የማንንም ፈቃድ ሳልጠይቅ በዜግነት መብቴ ብቻ የሚያገባኝ ሰው እንደሆንኩ እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ ። ይህ የኔ አስተሳሰብ ብቻ እንዳይመስልዎ ፤ የብዙ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንጂ ።
ስለኤርትራም ስናገር እዚያው ድረስ ሄጄ ፤ በእጄ ዳስሼ ፤ በጆሮዬ ሰምቼ ፤ በአይኔ አይቼ እንጂ ፤ ለፕሮፓጋንዳ በሻእቢያ የተለቀቁ የዩትዩብ ፊልሞችን መነሻ አድርጌ እንዳልሆነ ይገንዘቡልኝ ። ከንግግርዎ ላይ የሸተተኝ ነገር ስላለ ነው ይህን ያልኩት ። የንግግርዎን ቅኝት ከእዚህ በታች ባለው የዘውዴ አርአያ የፊልም ክምችት ፤ የሻእቢያ የፕሮፓጋንዳ ፊልም ላይ ስላገኘሁት አንባቢዎቼን ጋብዣለሁ ። ሊንኩን ይጫኑ ።
አንዳንድ ከርስዎ የምለይባቸውን ጉዳዮች ላንሳ ።
አርበኞች ግንቦት 7እና ኤርትራ በሚል ርእስ የተናገሩትን ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ እቃወመዋለሁ ። የምቃወምበትን ምክንያት “በኤርትራ በኩል ለምን” በሚለው ፅሁፌ ላይ በሚገባ ያብራራሁት ስለሆነ እንዲያነቡት እጋብዛለሁ ። ሻእቢያ የቀየሰው የተቃዋሚዎች አደረጃጀት ስልት ለኢትዮጵያ አደጋ አለው ። እርስዎ እንደገመቱት ይህን ጥያቄ ወያኔዎች ከስብሰባቸው በኋላ ሊያነሱት ይችሉ ይሆናል ። እኔም እንደርስዎ በተቃዋሚ ጎራ የምገኝ ስሆን ፤ ወያኔዎቹ ሳያነሱት በፊት አንስቼዋለሁና የኔ ጥያቄ ነው ። ኢትዮጵያ ለምትባለው ውድ ሃገራችን ሻእቢያ እንቅልፍ አጥቶ ይጨነቅላታል ቢሉኝ ፤ ለምን ? ብየ እጠይቅዎታለሁ ። ኢትዮጵያን ይወዳልታል ቢሉኝ ፤ ለምን ? ለመልካም ጉርብትና ቢሉኝ ፤ ለምን? ለምን? አሁንም ለምን ?
የኢትዮጵያን አንድነት የምናስብ ሰዎች ለ30 አመታት በኤርትራ የተደረገውን የጦርነት ታሪክ የምንመለከተው የኢትዮጵያ ሰራዊት የአገሪቱን አንድነት ለማስከበር ያደረገው ተጋድሎ አድርገን ነው ። በኤርትራውያን ቤት ሰማእትነቱ ከኛ በላይ መሆኑን ግን በንግግርዎ ላይ እስክሰማ ድረስ አላውቅም ነበር ። አዎ ! የማንም አገር ሰራዊት የመጀመሪያ ግዴታው የአገር አንድንድትን መጠበቅ ነውና ሰራዊታችን የሃገሪቱን አንድነት ለማስከበር ጠመንጃ አንግቦ ነበር ። ሲተኮስበት ፤ ተኩሷል ። በኤርትራውያን በኩልም እቅፍ አበባ ይዘው ፤ ለአንድነት መጣ ብለው ፤ አልተቀበሉትም ፤ እነሱም ብረት አንስተው ነበር ። ሰራዊቱ የተዋጋው የአለም አቀፉ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ፤ የግዛት አንድነቱን ለመጠበቅ ነበር ። የሻእቢያን መስዋእት ፤ በየቤቱ ሶስትና አራት ሙታን ለማድረግም አልነበረም ። ከዚህኛው ቤት ሶስት ከዛኛው ቤት አራት እያለም አልገደለም ። በንግግርዎ ላይ እርስዎ ለኤርትራ ሰማእታት ፤ ቤተሰቦች ፤ ስሜት ጭምር ተከራከሩ ። በሳል ፖለቲከኛ ፤ ሌላው ወገን ያልጠየቀውን ፤ ከፊት ከፊት እየቀደመ ፤ ይህንን ልናገርልህ ተዘጋጅቻለሁ ። መስዋእትነትህን አጎላልሃለሁ ማለት ምን አመጣው ?
አሜሪካ ያለምንም በቂ ማስረጃ ኢራቅን ወረረች ። ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿ መስዋእትነት ከፈሉ። አንድ ሚሊዮን የኢራቅ ሰው ደሞ በዚህ ወረራ ምክንያት አለቀ ። አንድም የአሜሪካ ፖለቲከኛም ሆነ ሚዲያ ፤ ይህን ያህል የገዘፈ እልቂት መናገር አይፈልግም ። ስለሞቱትና ስለቆሰሉት ዜጎች ወታደሮቹ ግን በየቀኑ ጀግንነታቸውን ያወሳል ። የሃገሩ ጥቅም ቀዳሚነት አለውና ። መስዋእትነት የከፈሉ ዜጎቹን አንገትም አያስደፋም ፤አያሳፍርምም ።
አንድ የማውቀውን ነገር ልንገርዎ ። ሻእቢያን ስለተለማመጡት የቆዳ ቀለሙን ቀይሮ እርስዎን ለመምሰል ጥረት አያደርግም ። የሻእቢያን መስዋእትነት ከኢትዮጵያ የአንድነት ተጋድሎ በላይ ስላጎሉለትም ሻእቢያ ነጥብ አይዝልዎትም ። እንዲህ እንደ እርስዎ ሲናገሩ የነበሩ ሰዎችን ፤ እኔ ራሴ ልመሰክር በምችልበት ሁኔታ ፤ በብዛት አስተናግዷልና ይታዘብዎታል ወይም “አልሰሜን ግባ በለው” ሲል ይሳለቅብዎታል ።
ንግግርዎ ላይ አንድ የተምታታ ነገርም ሰማሁ ። አቶ ስብኃት ነጋ አይናቸውን አጥበው ለኤርትራውያን ተከራክረዋል ብለው ከሰሷቸው ። አቶ ስብኃት ነጋ ኤርትራዊ ደም እንዳላቸው ለማናችንም ምስጢር አይደለም። አዎ ኤርትራዊ ደም አላቸዋና ይከራከሩላቸዋል ። እርስዎ ራስዎ ፤ የኤርትራዊ ደም የሌለዎት ሰው ፤ ከኛ መስዋእትነት በላይ ፤ ኤርትራውያን የበለጠ ሰማእትነት ከፍለዋል ብለው ሲናገሩ ፤ የአቶ ስብኃትን ስህተት አልደገሙትም ? ወይስ እርስዎና ድርጅትዎ ስትናገሩት ትክክል ነው ፤ አቶ ስብሐት ሲናገሩት ግን ስህተት ነው ።
አንድ የገረመኝ ጉዳይ ደግሞ ፤ የጃፓንና የአሜሪካ የዛሬ ወዳጅነት ብለው ያቀረቡት ተምሳሌት ነው ። ለዚህም ማስረጃው ቶዮታ መኪና በአሜሪካ ገበያ መሸጡ ነው ። ጃፓን ከጦርነቱ በኋላ ወታደራዊ አቅሟ ሙሉ በሙሉ ተንዶ ፤ ሱሪዋን እንድታወልቅና ቀሚስ እንድታጠልቅ የተደረገች ሐገር ናት ። ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳታደረግ የሚጠብቁ የአሜሪካ ወታደሮች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሰፈሩባት ሃገር ነች ።
ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲባል በድብቅ የሚያዙ ስምምነቶችና ጉዳዮች አሉ ። ለዚህም ሲባል በሚስጥር ተይዟል እንጂ ፤ አሜሪካ በጦርነቱ ጊዜ በጃፓን ምክንያት ያወጣችው ወጪና የጦር ካሳ በየአመቱ እስከዛሬ ድረስ እየተከፈለ ነው ። ገና ተከፍሎ አላለቀም ። በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ የነበሩ ፤ የግዛት ይዞታዎቿን ሁሉ ፤ ለተባበሩት የጦር ቃል ኪዳን አገራት (Allies Power) አስረክባለች ። በሰሜን በኩል እዚያው አፍንጫዋ ስር ያሉት አራቱ ትላልቅ “የኩሪል” ደሴቶቿ ያኔ በሶቭየት ህብረት የተወረሱ ፤ እስካሁን ድረስ የራሺያ ግዛት ሆነው እንዳሉ ናቸው። ጃፓን ትነግዳለች እንጂ እስካሁን በውርደት ላይ ያለች አገር ናት ። በቶዮታም ውስጥ ሆነ በሌሎች የጃፓን ኢንዱስትሪ ውስጥ ምን ያህል የአሜሪካ ካፒታል እንዳለስ ያውቃሉን ? የአሜሪካና የጃፓን ግንኙነት ፤ እንዳሉት በፍቅር ላይ ይተመሰረተ ሳይሆን ፤ በፍራቻና “ማግኘት የምችለው ፤ የተሰጠኝን ብቻ ነው” በሚል መርህ ላይ የተገነባ ግንኙነት ነው ። ጃፓን Full Capitulation የተፈፀመባት ሃገር ነች ። ውርደቷን ባጭሩ ይመልከቱ ። ለግንዛቤ ይረዳዎ ዘንድ ይህን ሊንክ ይጫኑ ።
በዚህ መሰረት ወደኛ ስንመለስ ፤ ማነው አሜሪካ ማነውስ ጃፓን ? ኤርትራ ዛሬ አርበኞች ግንቦት 7ን ያስጠጋች፤ ለድርጅታችሁ ለክፉ ቀን ደራሽ ስለሆነችና ፤ በኤርትራ ትግል ጊዜ (እንደርስዎ አባባል) ከየቤቷ ሶስትና አራት ሰዎች የሞተባት አገር ስለሆነችም የአንበሳው ድርሻ ይገባታል ። ስለዚህ ኤርትራ አሜሪካ ነች ። ኢትዮጵያ ደግሞ ጃፓን ነች ። አጥፊ ናትና ። ለአንድነት የተዋጋው ወታደሯም ተሸንፏልና Full Capitulation ሊፈፀምባት ይገባል ነው የሚሉን ?
ኢትዮጵያ ልጆቿ እያለን ይህ ሊሆን አይችልም ። ሻእቢያ ሲያምረው ይቅር ! ኢትዮጵያ ለአንድነቷ የተዋጉ ወታደሮቿ በሕይወት እያሉ ፤ በ98 በእብሪት የደረሰውን የሻእቢያ ወረራ የመከቱ ኢትዮጵያውያን እያሉ አገራችን ለሻእቢያ እጇን አትሰጥም ። (የራስዎን ቃል ልጠቀምና) ይህን ጠላትም ወዳጅም ሊያውቀው ይገባል ።
በዚሁ ንግግርዎ ላይ አቶ እፍሬም ማዴቦን ጠቅሰው ፤ “ይህን አሉ ያን አሉ እየተባለ ተፅፏል” ። ዛሬ ግን ኤፍሬምና ኢሳኢያስ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እየተነጋገሩ ነው ብለው ደጋፊዎችችሁን አስጨበጨቡና አንድ ነገር እንድጠይቅ ገፋፋኝ ። ይህን ዜና አልሰማሁም ነበር ። ኢሳትም አልነገረንም ። ስለምን ነበር የተነጋገሩት ? ስለኢትዮጵያ ከሆነ ልናውቅ ይገባናል ። ስለድርጅታችሁ ከሆነ አያገባኝምና የምለው አይኖርም ። ሁሌም ግን በድብቅ የሚደረጉ ውሎች ፤ (የራሳቸውን የኤፍሬም ማዴቦን አባባል ልዋስና) የሚያስከፍሉት ዋጋዎች ከፍተኛ ናቸው ። (ይህን ጉዳይ በሌላ ፅሁፌ እመጣበታለሁ ።)
ከወደብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የድርጅታችሁን አቋም አስመልክተውም ፤ ንግግርዎ ላይ “የህዝቡን ውክልና ያገኘ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ አንደራደርም” ብለዋል ። ይህን አቋማችሁን ብዙ ጊዜ ላነሳው ያሰብኩት ጥያቄ ነበርና እርስዎ ስላነሱልኝ አመሰግንዎታለሁ ። የወደብ ወይም የአሰብ ጉዳይ የመላው ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው ። ካልተደራደራችሁ አትንገሩን ጥያቄው የድርጅታችሁ ስላልሆነ ። በኢትዮጵያውያን ጥያቄስ ላይ ይህን አቋም እንድትይዙ ማን ማንዴት ሰጣችሁ ? ሻእቢያም ቢሆን በአሰብ ጥያቄ የዋህ አይደለም ። ግልፅ ያለ የፖለቲካም ሆነ የመንግስት ፖሊሲ ስላለው ፤ ፖሊሲውን እንዲያሳያችሁ ጠይቁትና ወይ ከአቋሙ ትስማማላችሁ ፤ አለያም ቀጣዩን እርምጃችሁን ታስተካክላላችሁ ።
በዚህ ጊዜ ሰላማዊ ትግል ማንሳት ቅንጦት አይደለም ? ሲሉም በዚሁ በንግግርዎ ላይ ይጠይቃሉ ። እንዴት ብሎ ነው ሰላማዊ ትግል ቅንጦት የሚሆነው ። በማህተማ ጋንዲ ፤ ማርቲን ሉተርና፤ በማንዴላም ጭምር የተፈተነ ትግል አይደለም እንዴ ?
ድርጅትዎ እንደመረጠው ሁሉ ፤ ሌሎች የመረጡትን የትግል መንገድ ቅንጦት ነው ብሎ ማጣጣል ምን ይጠቅማል ? ለድርጅትዎ የሚያመጣው የፖለቲካ ትርፍስ ምንድነው?
ከዚያም ወያኔ ለአልሻባብ ገንዘብ አልመደበም ወይ ብሎ አለመጠራጠር የዋህነት ይሆናል ሲሉ ጠረጠሩና ፤ እኔንም እንድጠረጥር ገፋፍተው አንድ ነገር ጠረጠርኩ ። ጥርጣሬዬን ከማጋራቴ በፊት ግን አንድ ነገር ትዝ አለኝ ።
ነገሩ እንዲህ ነው ። ምርቱ በጎተራው የሞላ ፤ ከብቶቹ በደንብ የተያዙ ዶሮዎቹ የበዙ ፤ ቀፎዎቹ የተሰቀሉ ፤ ሁሉ የተትረፈረፈው ገበሬ ፤ ጎንደር ወስጥ ይኖር ነበር ። አንድ ወንድ ልጅ ነበረው ። ልጁ አድጎ ይረዳኛል ብሎ ሲያስበው ዋልጌ ሆነበት ። እድሜው እየጨመረ ቢመጣም በየኮረፌና መሸታ ቤቱ ከማውደልደል በቀር ፤ ችግር የሚሞላ ሆኖ አልተገኘም ። አባትየው ልጁን ጠራውና ይህን ጠባይህን የማታሻሽል ከሆነ ከቤቴ አባርርኻለሁ አለው ። ልጁም መሻሻል አልቻለም ፤ አባትም መጨርሻው ደርሶ አባረረው ። ጓዙን በከረጢት ከቶም ሰጠው ። ለመንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ ቸረውና ከቤቱ አሰናበተው ። የገበያ ቀን ነበርና ጓዙን ተሸክሞ ሲሄድ የመደሩ ሰዎች ያገኙታል ። ጓዝህን ጠቅልለህ ወዴት እየሄድክ ነው ሲሉም ጠየቁት ። ኩሩው ጎንደሬ ሲመልስም “ሸዋን ላቀና እየሄድኩ” ነው ነበር ያላቸው ። አባቱ እንዳባረረው ግን ትንፍሽ አላለም ።
የጎንደሬው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ እንግዲህ ጥርጣሬዬን ልጠረጥረው ነው ። የግንቦት ሰባት ስራ አስፈፃሚ አባላት የሚኖሩት በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ነው ። አቶ አንዳርጋቸው እስር ቤት ነው ያለው ። ሶስቱም በአሜሪካ ይኖሩ የነበሩት ፤ የስራ አስፈጻሚ አባላት ከአሜሪካ ወደአስመራ (ወደ ትግል) ሙልጭ ብለው ፤ ሲገቡ ምነው አንድ እንኳ የአውሮፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ከአውሮፓ ወደአስመራ (ወደ ትግል) አልገባ ? ብዬ ጠረጠርኩ ። ታዲያ ይህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት Executive Body ስልጣኑን ተጠቅሞ የወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ ይሆን ብዬም ጠርጥሬአለሁ። እርስዎ እየጠርጠሩ እኔንም አስጠረጠሩኝ ። ለአውሮፓዎቹ የግንቦት 7 ስራ አስፈፃሚ አባላት የአሜሪካ መግቢያ ቪዛ እንዳይሰጥ መታገዱን መረጃ ስላለኝ ጥርጣሬዬ ውስጥ አልከተውም ። እርስዎ ሲጠረጥሩ እኔም ልጠርጥር ያልኩት ፤ ባለፉት 24 አመታት በተደረጉ የተቃዋሚ ታጋዮች እንቅስቃሴ ላይ ፤ አሜሪካ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳባቸው የነበሩ ሰዎች ትዝ ብለውኝ ነው ። የሚቀጥለውን አባባልዎንም አብረው ያያይዙልኝ ። “አሜሪካኖች የምናደርገውን ትግል በተሳሳተ መንገድ ቢፈርጁ አሁን ትግላችንን እናቆማለን ?” ብለው ጠይቀዋል ። ይሕንን አባባልዎን ከላይኛው ጋር ሳያይዘው ጥርጣሬየን የበለጠ አደመቀልኝ ።
መጨረሻም ላይ እንዲህ አሉ ።”አሁን ካለንበት ውርደት ለመውጣት ፡ ከምናደርገው ትግል አይደለም ምድራዊ ሃይል ሰማያዊ ሃይልም ሊያስቆመን እንደማይችል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል ።”
እውነት ነው ከውርደት ነፃነት ይመረጣል ። ለነፃነት ደግሞ መከፈል የሚገባውን መክፈል ተገቢ ነው ብዬም አምናለሁ ።
ኮለኔል መንግስቱ በስልጣን ዘመናቸው “አድሐርያንንና ተፈጥሮን (እግዚአብሄርን) በቁጥጥር ስር እናደርጋለን ብለው ፈክረው” አድሃርያንንም ሆነ ተፈጥሮን ሳይቆጣጠሩ ዚምባብዌ ገብተው ቀሩ ።
ፕሬዚደንት ኢሳኢያስ የእግዚአብሄርን ስራ ተገዳድረው ፀሓይ አትጠልቅም ፍካሬ ካሰሙን በኋላ ፤ ይኸው ፀሓይ ኡደቷ ሳይለወጥ ስትጠልቅ ስትወጣ ፤ ስትጠልቅ ስትወጣ 17 አመታት አለፏ ። እቡይነት ጥሩ አይደለም ።
ጠንካራ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ለሰማያዊው ሐያል ሙሉ እምነታቸውን ሰጥተው ፤ በህይወታቸውና በኑሯቸው ላይ ሁሉ ፤ ፈሪኃ እግዚአብሄርና ፈሪሃ አላሕን ለብሰው ፀጋውን እንዲሞላላቸው በሚፀለይባት ኢትዮጵያ ፤ ሌላው ቀርቶ ፤ የቀድሞ ማርክሲስት ሁሉ ዛሬ የእግዚአብሄርን ሃያልነት ተረድቶ ፤ ምህረት ለማግኘት ቤተ-ክርስትያን ባጣበበበት ዘመን ፤ ይህን የመሰለ የትእቢት ንግግር ለማንም አይጠቅምም ። ወሬም አያደምቅም ፤ አያጣፍጥምም ። ያለ የሰማዩ ጌታ ፈቃድ ማንም የትም አይደርስም ። ሰማያዊው ኃይል ፤ ኃያል ነው ።
የአገሬ ባላገር ነገር አልጥም ሲለው እንዲህ ይላል ።
“እግዜር ሲጣላ በትር አይቆርጥም ፤
ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም ።”
ቸር ይግጠመን
ኦገስት 29/2015
ላስ ቬጋስ ኒቫዳ ።