ሴቶች በአጥፍቶ መጥፋት ሲሳተፉ ማየት እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ ሆኖም በናይጄሪያ መንግሥት አክራሪ ተብሎ የተፈረጀው ቦኮ ሐራም ሴቶችንና ታዳጊ ሕፃናትን በአጥፍቶ መጥፋት እያሳተፈ ይገኛል፡፡ ለድርጊቱ ይረዳው ዘንድም የቦኮ ሐራም የሴቶች ክንፍ ካዋቀረ ሰንብቷል፡፡

የቡድኑ የሴት ክንፍ አብዛኞቹ አባላት ደግሞ በቡድኑ ታጣቂዎች ከየትምህርት ቤቱና ከየመንደሩ የሚጠለፉ ሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች በሚስትነትና በሠራተኝነት ከማገልገላቸው ባለፈም፣ በአጥፍቶ መጥፋት መሳተፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ የአጥፍቶ መጥፋቱን የሚፈጽሙትም በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በቻድ፣ በካሜሩንና በኒጀር ነው፡፡ ቦኮ ሐራም የታገቱ ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት መጠቀሙም በናይጄሪያም ሆነ በአካባቢው አገሮች ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁለት የቦኮ ሐራም አጥፍቶ ጠፊዎች በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ በምትገኘው ደማቱሩ በፈጸሙት ጥቃት አምስት ሲሞቱ 41 ያህል መጎዳታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በተለያየ ሥፍራ ከደረሱ ሁለት ፍንዳታዎች አንዱ የተፈጸመው 14 ዓመት በሚሆናት ታዳጊ መሆኑም ታውቋል፡፡ ሁለተኛውን አጥፍቶ መጥፋት ለመፈጸም የተመለመለው ታዳጊ ወንድ ግን ከታለመለት ሥፍራ ሳይደርስ የታጠቀው ቦምብ በመፈንዳቱ ሌሎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ራሱ ሞቷል፡፡

ቦኮ ሐራም ማክሰኞ ምሽት ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ባይወስድም፣ ከጥቃቱ ጀርባ ያለው ቦኮ ሐራም ሊሆን እንደሚችል ዘገባው ያሳያል፡፡ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቦሃሪ ሥልጣን ላይ ከወጡ ካለፈው መጋቢት 2015 ወዲህ፣ ማክሰኞ ዕለት የተመዘገበውን ጨምሮ ከአንድ ሺሕ በላይ ንፁሐን በቦኮ ሐራም ተገድለዋል፡፡ ቦኮ ሐራምን አሽመደምዳለሁ ብለው የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ከጉድላክ ጆናታን የረከቡት ቦሃሪ፣ ሥልጣን ከያዙ ጥቂት ጊዜያት ቢሆንም ቦኮ ሐራምን መቆጣጠር ተስኗቸዋል፡፡ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ቡድኑ ከአንድ ሺሕ በላይ ሲገድል ቁጥራቸው ያልታወቁ ሴቶችና ሕፃናትን ጠልፏል፡፡ ቡድኑ ከተመሠረተ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ብቻ 20 ሺሕ ዜጎችን ሲገድል፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ከቀያቸው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 መጀመርያ ላይ የቻድና የናይጄሪያ ጥምር ጦር ቦኮ ሐራም የራሱን አስተዳደር ከመሠረተባቸው 25 ሥፍራዎች እንዲለቅ ያደረጉት ቢሆንም፣ የጥቃት ሥልቱን ቀይሮ በአጥፍቶ ጠፊዎች መጠቀም ጀምሯል፡፡ ለዚህም ታዳጊ ወጣቶች በተለይም ሴቶችን ጥቅም ላይ እያዋለ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ ትምህርት ልዩ መልዕክተኛ ጎርደን ብራውን፣ በናይጄሪያ ቺቦክ በአዳሪ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ ሴቶች በቦኮ ሐራም የመጠለፋቸውን ዓመታዊ ፕሮግራም አስመልክተው፣ ቦኮ ሐራም ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት መጠቀሙን አውግዘው ነበር፡፡
ከአምስት ወራት በፊት በሰጡት መግለጫም ቦኮ ሐራምን ማስቆም ካልተቻለ ታዳጊ ሴቶችና ወንዶች ለቦኮ ሐራም አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ሊውሉ እንደሚችሉም ጠቁመው ነበር፡፡

የቺቦክ ሴት ተማሪዎች በተጠለፉበት አንደኛ ዓመት ዋዜማ በሦስት ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች የተጀመረው የቦኮ ሐራም ጥቃት ዛሬ ተስፋፍቷል፡፡ ከዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶች በተቃራኒ፣ ቦኮ ሐራም ሕፃናትን በዕድሜና በፆታ ሳይለይ ለአጥፍቶ መጥፋት እያዋለም ነው፡፡ ‹‹ዓለም ቦኮ ሐራም የሚፈጽመውን ርኩስ ተግባር የሚቃወምበትና የሚያወግዝበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ታዳጊ ሴቶች እየተበዘበዙና ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡ ብዙ ታዳጊ ሕፃናት አስደንጋጭ ወደሆነ ግዳጅ ከመሰማራታቸው በፊት ዓለም አቅሙን ተጠቅሞ ቦኮ ሐራምን ሊያቆመው ይገባል፤›› ብለውም ነበር ብራውን፡፡

ይህ ግን የተሳካ አይመስልም፡፡ በመሆኑም ናይጄሪያውያን በቦኮ ሐራም ሚሊሻዎች ከሚደርስባቸው ግድያ ባለፈ ለሴት አጥፍቶ ጠፊዎች ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ ቦኮ ሐራምም የጠለፋቸውን ታዳጊ ሴቶች አመለካከት በመቀየርና በአጥፍቶ መጥፋት እንዲሳተፉ ማድረጉን ገፍቶበታል፡፡ ታዳጊዎቹ ለግዳጅ ተልዕኮም እየዋሉ ናቸው፡፡

በናይጄሪያ የመጀመርያው የሴት አጥፍቶ መጥፋት ጥቃት የተፈጸመው እ.ኤ.አ. በ2014 ሰኔ ወር በምሥራቅ ናይጄሪያ ጐምቢ ነበር፡፡ በወቅቱ ጥቃቱን የፈጸመችው በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ብትሆንም፣ ከዚህ በኋላ የተከሰቱ ጥቃቶች በታዳጊ ሕፃናት የተፈጸሙ ናቸው፡፡ ሁለተኛው ጥቃት የተፈጸመው የመጀመርያው በተፈጸመ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሌጐስ ደቡባዊ አቅጣጫ በምትገኘው አፖፖ ነበር፡፡ ከዚህ በማስቀጠል በዚሁ ዓመት ነሐሴ ወር በሰሜን ናይጄሪያ እንቅስቃሴ በሚበዛባት ካኖ ከተማ አራት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች የተፈፀሙ ሲሆን፣ ሁሉም በታዳጊ ሴቶች የተፈጸሙ ናቸው፡፡ በዚሁ ወር የአሥር ዓመት ታዳጊ ሴት በ18 ዓመት እህቷና በአንድ ግለሰብ እየተመራች ጥቃት ልትፈጽም ስትል ሁሉም በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የአጥፍቶ ጠፊዎችን በቁጥጥር ሥር መዋል ተከትሎ የአገሪቱ ሚዲያዎች ምንጭ ሳይጠቅሱ፣ ቦኮ ሐራም ከ15 ዓመት በታች ያሉ 177 ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት ወንጀል እያሠለጠነ መሆኑንና ከእነዚህ ውስጥ 75 ያህሉ በናይጄሪያ ጥቃቱን ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ዘግበው ነበር፡፡ በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ ዲፌንስ ዲፓርትመንት የዶክትሬት ተማሪ የሆነችው ኤልዛቤት ፒርሰን እንደምትለው፣ ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት መጠቀም የአንድ ሸማቂ ቡድን መዳከምን የሚያሳይ መሆኑን ነው፡፡ በጦር ግንባር ያሉ ወንዶች ሲመናመኑ ሴቶችን ለሽብር መጠቀም በአልቃይዳ ውስጥም የተለመደ ነበር ብላለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 የተመሠረተው ቦኮ ሐራም 270 የሚሆኑ ሴት ተማሪዎችን ከጠለፈ በኋላ እየተስፋፋ የመጣው የሴት አጥፍቶ ጠፊዎች፣ የሚዲያ ቀልብ ለመሳብ የተደረገ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ ምክንያቱም ቦኮ ሐራም በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅና ሰፊ የዜና ሽፋን እንዲያገኝ የረዳው በቺቦክ የሚማሩ ሴት ተማሪዎችን ከጠለፈ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ቦኮ ሐራም ከተቆጣጠራቸው አካባቢዎች አዛውንቶችን ብቻ አስቀርቶ ወንዶችንና ሴቶችን እየጠለፈ መውሰድ መጀመሩና ለጦርነት ማሳተፉ የቀድሞ ሚሊሻዎቹ እየተመናመኑ መምጣታቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ቦኮ ሐራም ‹‹ሴቶች በቤት መቀመጥ እንጂ ወጥተው መሥራትም ሆነ መዋጋት አይችሉም፤›› ከሚለው ፍልስፍናው ጋር የሚጣረስ ተግባር አያራምድም ነበር፡፡

በቦኮ ሐራም ውስጥ ሴቶች ያለፍላጎታቸው በግዳጅ የወንጀልና የአጥፍቶ መጥፋት ተሳታፊ ሲሆኑ በሌላ በኩል በፍላጎት የሚቀላቀሉም አሉ፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ የሴቶች ክንፍ የመሠረተ ሲሆን፣ ይህንን በመሠረተ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተከታታይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች በሴቶች ተፈጽመዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ሦስት ሴቶች ቦኮ ሐራምን የሚቀላቀሉ ወጣት ሴቶችን፣ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ደግሞ በሰላይነት ሲመለምሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ቦኮ ሐራም በናይጄሪያና በቻድ ጥምር የጦር ኃይል ጥቃት እየደረሰበት ቢሆንም፣ ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት እየተጠቀመ ነው፡፡ የናይጄሪያ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ የቦኮ ሐራምን አካሄድ እያወገዙ ነው፡፡

የሴት አጥፍቶ ጠፊዎች በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን ግጭት ባሉባቸው አገሮች ሁሉ የሚገኙ መሆኑን እ.ኤ.አ. በ2011 የተሠራው የአሜሪካ የደኅንነት መረጃ ትንታኔ ያሳያል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ ሴቶች ካላቸው የእናትነት ባህሪ አንፃር በአጥፍቶ መጥፋት ይሳተፋሉ ተብለው አይጠረጠሩም፡፡ ሆኖም ከወንድ የበለጠ ትልቅ ጥፋት የሚያደርሱት፣ እርጉዝ በመምሰልና ሰፊ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች በመገኘት ነው፡፡ አብዛኞቹ ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች በ20ዎቹ መጨረሻ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው ወንድ አጥፍቶ ጠፊዎች ከሚገኙበት ዕድሜ ከፍ ያለ ነው፡፡

የመጀመሪያው በሴት አጥፍቶ መጥፋት የተፈጸመባት አገር ሊባኖስ ናት፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 የሶሪያ ሶሻል ናሽናሊስት ፓርቲ አባል የሆነች ሴት ቦምብ የተጠመደበት መኪና በማሽከርከር፣ ሁለት የእስራኤል ወታደሮችን ገድላ ሁለት አቁስላለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1991 የቀድሞው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ራጂቭ ጋንዲ የተገደሉትም በሴት አጥፍቶ ጠፊ ነው፡፡ በቺቺኒያ የሚገኙ የሩሲያ ወታደሮችና ሲቪሎች፣ በኩርድ የሚገኙ የቱርክ ወታደሮችም በሴት አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡

ዋፋ ኢድሪስ የመጀመርያዋ የፍልስጤም አጥፍቶ ጠፊ ብትሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2002 በኢየሩሳሌም በፈጸመችው አጥፍቶ መጥፋት ራሷን ብቻ ገድላለች፡፡ በዚሁ ዓመት የ18 ዓመቷ አያት ኣል አክራስ ሁለት የእስራኤል ሲቪሎችን መግደል ችላለች፡፡ ሐማስ እ.ኤ.አ. በ2004 ለቡድኑ የመጀመርያ የሆነችውን ሪም ሪያሺ በአጥፍቶ መጥፋት በማሳተፍ ሰባት ሰዎችን ማስገደል ችሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 የኢራቅ ሁለት ሴት አጥፍቶ ጠፊዎችም በኢራቅ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሰው ሞተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 ደግሞ ሁለት የቺቺኒያ አጥፍቶ ጠፊዎች በሞስኮ ባቡር ጣቢያ በፈጸሙት ጥቃት 38 ሰዎች ሲገድሉ፣ ከ60 በላይ አቁስለዋል፡፡ በዚሁ ዓመት በፓኪስታን የዕርዳታ ማዕከል ውስጥ በሴት አጥፍቶ ጠፊ በተፈጸመ ጥቃት 43 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የሴት አጥፍቶ ጠፊዎች እየበራከቱ መምጣት ለዓለም ሌላው ሥጋት ሆኗል፡፡ ተግባሩ ከ20 ዓመታት በፊት የተጀመረ ቢሆንም ጎልቶ መውጣት የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ በተለይ የናይጄሪያው ቦኮ ሐራም ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሴቶችን ለአጥፍቶ መጥፋት መጠቀሙ ለየት ያደርገዋል፡፡

poted by Aseged Tamene

Leave a Reply