የመንግስት ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች ለእኛም ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች መኖር አስፈላጊነት አመላካች ናቸው! (ድምፃችን ይሰማ)
ቅዳሜ ነሐሴ 23/2007

ፕሮግራም አንድ ድርጅት ወይም መንግስት በረጅም ጊዜ ውስጥ ሊያሳካ የሚፈልገው እቅድ ነው፡፡ በስሩ ተዛማጅነት ያላቸውና የሚቀናጁ ፕሮጀክቶችን የሚያካተት ነው፡፡ ፕሮጀክት በአንፃሩ በጊዜ እጅጉን የተገደበ፣ ሊያመጣው የሚፈለገው ውጤትም ከወዲሁ ሊለካ የሚችልና የተወሰነ ነው፡፡

የመንግስት ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች

የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ትግል ሲጀምር በ3 ቁልጭ ያሉ ጥያቄዎች የታጠረ ነበር፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ለሁሉም ሰው አግባብነት ያላቸው መሆናቸው ባያጠራጥርም ለመንግስት ግን መመለሱ ጭራሽ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ ለመመለስ ያልተፈለገው እነዚህ ፕሮጀክቶች መንግስት ተሳስቶ ወይም በደንብ ሳያሰላስል የገባባቸው ስራዎች ሳይሆኑ ሊያስፈፅሙት የሚፈለግባቸው ሌላ ትልቅ ፕሮግራም ከጀርባ በመኖሩ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የአህባሽ ስልጠና፣ የመጅሊስ በመንግስት ስር መሆንና አወሊያን በመንግስት መጅሊስ መያዝ ተዛማጅነት ያላቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

መንግስት ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ባሻገርም ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን በመፈፀም ላይ ነው፡፡ በወኪሎቻችንና በወንድሞቻችን ላይ የፈረደው የ22 ዓመታት ፍርድም ‹‹ሙስሊሙን ያለ መሪ ማስቀረት›› የታሰበበት ፕሮጀክት ሲሆን ለፕሮግራሙ ማሳኪያ የሚባሉት ፕሮጀክቶች አካል እንደሆነም ማየት እንችላለን፡፡ እነዚህ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በአንድ ላይ ሲሆኑ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የያዘው ሰፊ ፕሮግራም እንዳለ አመላካች ናቸው፡፡ የመንግስት ፕሮግራም በአጭሩ በሃይማኖቱ ሳቢያ ሙስሊሙን ጨቁኖና ረግጦ መያዝ ነው፤ ይህ ደግሞ ብሄራዊ ጭቆና ይባላል፡፡ መንግስት ይህ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የያዘው ፕሮግራም ዳር አልደርስ እስካለው ድረስ ከዚህ በፊት ያልተጠናቀቁትንም ይሁን ያልተገበራቸውን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከመፈፀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ‹‹አቅጣጫችን ብሄራዊ ጭቆናን ለመግታት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ይሆናል›› ስንልም ከዚህ አንፃር ነው፡፡

የምንይዘው ፕሮግራም በአጭሩ የሃይማኖት መብቶቻችንን በሙሉ ማስከበር ነው፡፡ ፕሮግራማችን መንግስት እየፈፀማቸው ያሉትን የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች በመታገል ብቻ ሳይወሰን የመንግስትን ዋናውን ፕሮግራም ወደመታገል ማምራት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ፕሮግራም ስንነሳ በጣም ሰፊና በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፈን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ሂደትም ሁሉም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ እይታ ሲኖረን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመመልከት ‹‹ይህ ስራ (ፕሮጀክት) ለውጥ አላመጣልንም›› የምንልበት አግባብ አይኖርም፡፡ የያዝነው ፕሮግራም የሚሳካው (ከአላህ እርዳታ ጋር) በተለያዩ የፕሮጀክቶች ግብዓት ድምር ውጤት ነውና!

ብሄራዊ የሃይማኖት ጭቆናን አንሸከምም!
በጋራ ተሳትፎ እና በአንድነት ዲናችንን እንጠብቃለን!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

Ayda Fuad Ayda Fuad's photo.

Leave a Reply